የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ከሚሰጡት ቃለ ምልልስ አንዱ በሆነውና የመጀመሪያው ክፍል ትናንት አርብ ምሽት በሰጡት ማብራሪያ ላይ በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክተው ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ ንግግራቸው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መበላሸት ምክንያት ስለሆነው የድንበር ጥያቄ አንስተው በተለይ በባድመ ጉዳይ ስምምነቱ እንዳይፈጸም ህወሓት እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በወረራ የተያዘው የኤርትራ ሉዓላዊ መሬት ያልተመለሰው ህወሓት እምቢ በማለቱ ነውብለዋል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ።

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የተደረገው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት እልባት ይሰጣል የተባለውን የድንበር ጉዳይ በማስመልከት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ትናንት ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሓት በድንበሩ ጉዳይ የወሰደውን አቋም ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተናገሩት የስምምነት ሃሳብ ሳይተገበር የባድመ የድንበር ሁኔታ እንደምናየው ድሮ ከነበረበት ደረጃም በላይ በከፋ ሁኔታ ነው ያለው።

ሕጋዊ ውሳኔ ተሰጥቷል፤ በዚሁ መሰረት ውሳኔው ተከብሮ የተወረረው ሉዓላዊ መሬት ወደ ኤርትራ መካለል ነበረበት። አሁን ግን አልተቻለም።

ለምን አልተመለሰም ያልን እንደሆነ፤ የከሰረው ስብስብ [ህወሓት] የድንበርን ጉዳይ በአንድ በኩል እንደ ማስፈራሪያና በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መቋመሪያ ስለያዘው በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በባድመ ጉዳይ ምን ሰራን ካልን፤ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ሳንገባ በአጭሩ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷልብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለጦርነቱ መነሻ በነበረችው ባድመ መሬት እየተሸነሸነ እየታደለ ነውያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ደግሞ የድንበሩን ጉዳይ እልባት ላለመስጠት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኤርትራ በተወሰነው መሬት ላይ መሬት ለማን እየታደለ እንደሆነ መረጃ አለን።

ከህወሓት በበኩሉ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የተወሰነውን የድንበር ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እንደሚቀበሉ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ውሳኔውን በተመለከተ ግልጽ ምላሽ አልሰጠም።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ካሳወቁ ከአንድ ዓመት በኋላ የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት የተሰራ የሚታይ ነገር የለም። ለኤርትራ የተወሰነው የባድመ መሬት አሁንም በኢትዮጵያ እጅ ነው የሚገኘው።

እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም

ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በባድመ ድንበር ብቻ ሳንታጠር፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በሁሉም አቅማችን እንደግፋለንብለዋል።

ሰላም ሰርተህ የምታመጣው እንጂ እንደመና ከሰማይ የሚወርድ አይደለምያሉት ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን የሰላም ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ስምምነት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በመጠቆም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥም ኤርትራን እንደጎረቤት ሳይሆን ራሷን በቀጥታ ስለሚጎዳት እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልምብለዋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሦስት ትውልድ የተደረገው ጦርነት ትርጉም አልባ ነበርበማለት ጦርነቱም የውጭ ኃይሎች ጉዳዩን ስላወሳሰቡት የመጣ ጣጣ እንደነበርም ገልጸዋል።