9 February 2020
ማክሰኞ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 24 ከቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በስተጀርባ፣ ሁለት ወጣቶች መገደላቸውን በመቃወም ቁጣቸውን የገለጹ ነዋሪዎች ፍትሕ እንሻለን ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ በምንም ዓይነት ሁኔታ በፖሊስ መገደል እንደሌለባቸው የተናገሩት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱን ከመጠን በላይ የሆነ ምሬት እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡
ወጣቶቹ የተገደሉት በአካባቢው ለረዥም ጊዜ ታጥሮ በነበረ ባዶ ቦታ ላይ ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ አንድ መነኩሴ (ባህታዊ) የቅድስት አርሴማን ጽላት ይዘው በመምጣታቸው፣ መቃኞ (ቤተ ክርስቲያን እስከሚሠራ ድረስ ጽላት የሚቆይበት) በመሠራቱና የአካባቢው ሕዝብ የአምልኮ ሥርዓት በመጀመሩ መሆኑ ታውቋል፡፡ መቃኞው በተሠራ በሦስተኛው ቀን ከክፍለ ከተማው የተላኩ ሰዎች መቃኞው እንዲነሳ ላቀረቡት ጥያቄ የሚመለከታቸው ሰዎች የሰጡት ምላሽ ቢኖርም፣ ፖሊሶች በአካባቢው በመሰማራታቸው ከነዋሪዎች ጋር ግጭት መፈጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊቱን የአካባቢው ወጣቶች መቃኞውን ሲጠብቁ ያደሩ ቢሆንም፣ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ የደንብ ልብስ የለበሱ በርካታ የፖሊስ አባላት ወደ ሥፍራው በመሄድ፣ በቦታው የነበሩ የአካባቢውን ወጣቶች ለማስወጣትና መቃኞውን ለማፍረስ በተደረገ ‹‹አፈርሳለሁ፣ አታፈርስም›› ውዝግብ ፖሊስ መተኮስ በመጀመሩ፣ ሁለት ወጣቶች መሞታቸውንና ለጊዜው ቁጥራቸው የማይታወቁ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በሥፍራው የነበሩ አካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረው ግጭት እስከ ንጋት ቀጥሎ ወደ 22 ማዞሪያ የሚወስድ መንገድ እስከ ረፋድ ለሰዓታት ዝግ ሆኖም ቆይቶ ነበር፡፡
‹‹ታቦተ ሕጉ ያረፈበት ቦታ በሕገወጥ መንገድ የተያዘ ቢሆን እንኳን፣ ሕገወጥ ድርጊትን እንዴት በሕገወጥ መንገድ ማስተካከል ይቻላል?›› በማለት የሚጠይቁት ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ኃላፊ መላከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ ናቸው፡፡
ኃላፊው ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ቦታው ሕገወጥ አይደለም፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ጀምሮ ጥያቄ አቅርበው ደብዳቤ ሲለዋወጡበት እንደነበር፣ የሚመለከተው አካል ስላለ በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ‹‹አስነሱልን›› ማለት ይቻል እንደነበር፣ ሕገወጥ ነው ተብሎ የሰው ሕይወት በማጥፋትና በሕገወጥ መንገድ ለማስለቀቅ መሞከር ተገቢ አለመሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ግድያውን በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ፣ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ የግራ ቀኝ ወገኖች በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ችግሩን በውይይት መፍታት ሲችሉ ወደ ኃይል ዕርምጃ በመግባት የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ በመደረጉ ቤተ ክህነትን አሳዝኗታል ብለዋል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በማጣራት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ችግሩ በተፈጠረበት ቦታ በሟቾች ቤተሰቦች ቤት በመገኘት ሐዘናቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ስለድርጊቱም ሆነ ድርጊቱን ስለፈጸሙ አካላት አስተዳደሩ ምንም እንደማያውቅ ገልጸው፣ ‹‹ወጣቶቹን ለሞት ያበቁ ማናቸውም ወገኖች ወይም አካላት ለሕግ ይቀርባሉ፤›› ብለዋል፡፡ ለጊዜው በርካታ ተጠርጣሪ ወጣቶችና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ቢሆንም፣ ይመለከታቸዋል የተባሉ ሰባት ተጠርጣሪዎችን በማስቀረት ሌሎቹ እንዲፈቱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ከይዞታ ጋር የተያያዙ የሃይማኖት ተቋማት የሚያነሷቸው ጥያቄዎችን ሲመልስ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው፣ ድርጊቱ በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት የደረሰ አደጋ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቦታው ሕጋዊ ባይሆንም እንኳን ‹‹በምሽት እንዲፈርስ ትዕዛዝ መተላለፉ ልክ አይደለም፤›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ትዕዛዙን ያስተላለፈውንም አካል ለሕግ እንደሚያቀርቡም አስታውቀዋል፡፡
ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያኗንና መንግሥትን የማይወክልና ፖሊስም ትኩረት ሰጥቶ እየመረመረ መሆኑንም አክለዋል፡፡ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት ተባብረው እየሠሩ ከመሆኑ አንፃር፣ ምንም ዓይነት እኩይ ተግባራት ቢፈጸሙ ያለውን ግንኙነት ሊሸረሽር እንደማይችልም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ ደግሞ፣ ‹‹ቦታው ለአረንጓዴ ሥፍራ የተተወ ነው፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ጽላት ሳይገባ ቦታውን ለመያዝ የተደረገ ተግባር ነው፡፡ በቅርቡ በተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ የተደረጉ ድራማዎች ናቸው፡፡ በጉዳዩ ወረዳውም ፖሊስም ከካህናት ጋር ሲወያዩ ነበር፡፡ እንደሚያነሱ የተስማሙ ቢሆንም ሊያነሱ ባለመቻላቸው፣ የከተማው ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ሕግ እንዲያስከብሩ ተደርጓል፤›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት አልተፈቀደም፡፡ ዕርምጃውም ሌሊት የተደረገው እንደ እነዚህ ዓይነት ሥራዎች መሠራት ያለባቸው በምሽት ነው፡፡ ቀን ላይ ከሆነ ቀውስ እንደሚበዛ ሁለት ጊዜ ተሞክሮ በመረጋገጡ ነው፡፡ ሌላ ተዓምር የለውም፤›› ብለዋል፡፡
ሕግ አስከባሪዎች መቼና በስንት ሰዓት ሕግ የማስከበር ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው በሕገ መንግሥቱም ሆነ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መደንገጉን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሕግ ጠበቃው አቶ ዮሐንስ መላከ ሕይወት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 33 (5) ላይ እንደተደነገገው፣ ከፍርድ ቤት ‹‹በተለይ ካልታዘዘ›› በስተቀር ብርበራ የሚደረገው ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 12፡00 ሰዓት ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ በ22 ማዞሪያ አካባቢ በሌሊት ተፈጸመ የተባለው የግድያ ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን ከሕጉ አንፃር መመልከት እንደሚቻል ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ታቦቱ ተቀምጦበታል የተባለው ቦታ በሕገወጥ መንገድ በወረራ የተያዘ ቢሆን እንኳን፣ የደንብ አስከባሪዎች በሚመሩበት መመርያና ደንብ መሠረት ማስጠንቀቂያ ሊሰጥ ይገባ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ወይም የሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ‹‹ሁከት ይወገድልኝ›› በማለትም ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ይችልም እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በተፈጠረው ግጭት ሕይወታቸው ያለፈው ወጣት ሚካኤል ፋኖስና ወጣት ሚሊዮን ድንበሩ ሲሆኑ፣ የወጣት ሚካኤል ፋኖስ የቅርብ ዘመድ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹አያቱን የሚጦርና ምንም የማያውቅ ቅን ልጅ ነበር፡፡ ይህንን የአካባቢው ኅብረተሰብ ሊመሰክር ይችላል፡፡ ፍርዱን አምላክ ይክፈለን እንጂ ሌላ ፍርድ እንኳን እናገኛን ብለን አንጠብቅም፤›› ብለዋል፡፡
የወጣቶቹ አስከሬን ሐሙስ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ጥቁር ቲሸርት በለበሱና የቤተ ክርስቲያን ዓርማ ያለው ረዥም ሰንደቅ ዓላማ የያዙ በርካታ ወጣቶች እየተመራ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ታጅቦ ለፍትሐተ ፀሎት ተወስዷል፡፡ መዘምራን ግራ ቀኝ ቆመው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በሚመሯቸው ጳጳሳትና በበርካታ ቀሳውስት ፍትሐተ ፀሎት ተደርጎላቸዋል፡፡ በወቅቱ በርካታ እናቶች፣ ወጣቶች፣ አባቶችና የሃይማኖት መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ሁሉም ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡ ወጣቶቹ አስከሬኑን ከፊትና ከኋላ በማጀብ ‹‹አንመካም በጉልበታችን፣ እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን›› እና ሌሎች ዝማሬዎችን እያሰሙ ወደ ቀብሩ ሥፍራ ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አምርቶ የቀብር ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሚመለከተው መንግሥት አካል በፍጥነት ፍትሕ እንዲያሰፍን፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊትም ደግሞ እንዳፈጸም ጠይቀዋል፡፡
ሪፖርተር