በትናንትናው (3/6/2012) ዕለት በጅማና አጋሮ ከተሞች ‘ለብልጽግና እንሩጥ‘ በሚል መሪ ቃል በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል የተባለ የድጋፍ ሰልፍ ተደረገ።
የሠልፉ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን መደገፍ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ሠልፉ የተደረገው በትናንትናው ዕለት (3/6/2012) ኦፌኮ በጅማ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ሊያደርገው የነበረውን የትውውቅ መድረክ ከተሰማ በኋላ እንደነበር ተነግሯል።
የኦፌኮ የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዑመር ጣሂር እንዳሉት በጅማ ስታዲየም ሊያደርጉት የነበረው ይህ ፕሮግራም በከተማው አስተዳደር ተከልክሏል።
የኦፌኮ ህዝባዊ መድረክ ቢከለከልም በጅማ ከተማ አስተዳደርና በከተማዋ ወጣቶች የተዘጋጀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገ የድጋፍ ሠልፍ ግን ተካሂዷል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል የታተመባቸው ቲሸርቶችና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልፁና የሚያወድሱ ጽሑፎች በሰልፉ ላይ ታይተዋል።
የሠልፉ ተሳታፊና አስተባባሪ የሆነው የጅማ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ድማሙ ንጋቱ “ለውጡ መቀጠል አለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ መከፋፈል፤ መሰደብም የለበትም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር የተወከሉ መሪዎች መከበር አለባቸው በሚል ሃሳብ ሠልፉ ተዘጋጅቷል” ሲል ያብራራል።
የሠልፉ መነሻ ሃሳብ የኦፌኮ አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ በተለያየ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲወረፉ መሰማታቸውን ቅሬታ በመፍጠሩ እንደሆነም ጨምሮ ይናገራል።
በሠልፉ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማስመልከት በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች የሚናገሩት ንግግር ያልተገባ መሆኑንና ሕዝቡንም እንዳስከፋ ይገልጻሉ።
ወጣት ድማሙ አክሎም “ሕዝቡ የወከላቸው መሪዎችን መስደብና ማንኳሰስ ሕዝቡን ራሱ እንደመስደብ ነው የሚቆጠረው” ካለ በኋላ በፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት ያለ ቢሆንም ይህ የሃሳብ ልዩነት ሕዝቡን መከፋፈል የለበትም ሲል ያስረዳል።
በጅማ በተደረገው የድጋፍ ሠልፍ ላይ አለመሳተፉን የሚናገረው ወጣት አሕመድ አባ መጫ ደግሞ “የኦሮሞ ህዝብ ዓላማ፣ ዋጋ ከፍሎ እዚህ ያደረሰውን ትግል የቀረውን ነገር አሟልቶ ከዳር ማድረስ ነው” በማለት የጅማ ወጣቶችና ሕዝቡ ፍላጎትም ይኸው ነው ሲል በሚኖርበት ከተማ ስለተደረገው ሠልፍ ዓላማ ይናገራል።
“ጃዋር ተምሳሌታችን ነው” የሚለው ወጣት አሕመድ፣ ኦፌኮን ከተቀላቀለ በኋላ የሚናገራቸው አንዳንድ ንግግሮች እንዳስከፉት ይገልፃል።
“ስሜታዊ ሆኜ የምናገራቸው ንግግሮች መጥፎ ነገር ያስከትላሉ፤ ስለዚህ ተከባብረን እየተደማመጥን በፕሮግራምና በፖሊሲ ላይም ቢሆን ክርክር ማድረግ እንጂ ጣት መቀሳርና መወራረፍ ጠቃሚ አይደለም” ሲል ይናገራል።
የጅማ ሕዝብ ጥያቄና ሠልፉን ያደረገበት ምክንያትም ይኸው ነው ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል።
በትናንትናው ዕለት በጅማና በአጋሮ የተካሄዱትን የድጋፍ ሠልፎች በሚመለከት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት አበል ከፍሎ ማስተባበሩን የሚገልጹ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር።
ይህንን በተመለከተ የሰልፉ አስተባባሪ ወጣት ድማሙ ግን ” አበል መክፈል ይቅርና ቲሸርቶቹንና መፈክሮችን ለማሳተም እንኳ መንግሥት ምንም ዓይነት ገንዘብ አላወጣም” ይላል።
OFC/FACEBOOK
የኦፌኮ ስብሰባ ለምን ተከለከለ?
በትናንትናው ዕለት ኦፌኮ በጅማ ስታዲየም ከደጋፊዎቹ ጋር ሊያካሄድ የነበረው ስብሰባ ለምን እንደተከለከለ የድርጅቱ የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሲናገሩ ከዞኑ አመራሮች ጋር በመግባባት ሲሰሩ እንደቆዩ በማስታወስ ነገር ግን ጃዋር ፓርቲያቸውን ከተቀላቀለ በኋላ አለመግባባቶች መከሰታቸውን ያስረዳሉ።
“ጃዋር ከመጣ በኋላ ጥሩ አልነበረም። የኦፌኮ ልዑክ ወደ ጅማ ለመምጣት ከወሰነ በኋላ ደግሞ እንደ ጠላት ማሳደድ ጀመሩ” ይላሉ።
ትልቅ ጫና እየደረሰብን ነው ያሉት አቶ ዑመር አባላቶቻቸው እየታሰሩ መሆኑንና ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የተከለከሉት የምርጫ ቅስቀሳ ታካሂዳላችሁ ተብለው እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው “እኛ የጠየቅነው የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሳይሆን የሕዝብ ትውውቅ መድረክ ለማካሄድ ነው” ብለዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ መኪዩ መሐመድ ቢቢሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ሕጉን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው “ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዲያደርጉ አልፈቀደም፤ ኦፌኮ በሌሎች ዞኖች የሚያደርጋቸው እንቅስቀሴዎች የትውውቅ ሳይሆን የምርጫ ቅስቀሳ ነው” ይላሉ።
በዚህም ምክንያት ስብሰባውን አለመፍቀዳቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከተማው አስተዳደር ሳያውቅ ለሕዝብ ጥሪ መተላለፉንና ፀጥታን በተመለከተ በቂ ዝግጅት ባለመደረጉ ስታዲየሙ ውስጥ ስብሰባ እንዳይደረግ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከንቲባው አክለው ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ እንዳልተከለከለ አስተረድተው የትውውቅ መድረካቸውን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉት ለፓርቲው አመራሮች እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
BBC