12 February 2020
የኢትዮጵያ መንግሥት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ እየተካሄደ የሚገኘውን ድርድር ለሚታዘቡት የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም አስመልክቶ የተነሱ ጉዳዮች በረቂቅ የስምምነት ሰነድ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚገባ አሳሰበ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመሥገን ዑመር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለአሜሪካ የገንዘብ ተቋም በጻፉት ደብዳቤ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር እስካሁን መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን በተመለከተው የስምምነት ሰነድ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን የተነሱ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉና ዓውዱን ጠብቀው ሊካተቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይኼንን ደብዳቤ ለመጻፍ መነሻ የሆነው ድርድሩን የሚታዘበው የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም እስካሁን ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ያመላከተ ሰነድ፣ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 3 ቀን 2020 ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መላኩ ነው።
በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የተነሱት ጉዳዮች የኢትዮጵያ ፅኑ አቋሞች እንደሆኑና በስምምነት ሰነዱ ውስጥ በተገቢው መንገድ ሊካተቱ እንደሚገባ የሚገልጸው ደብዳቤው፣ በጉዳዮቹ ላይ የሚነሳ ጥያቄ ካለ በቀጣይ መድረኮች ተጨማሪ ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚችልና ለዚህም ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ያመለክታል።
ሊካተቱ ይገባቸዋል በማለት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የውኃ ትነትን የሚመለከት ሲሆን፣ በከባድ የድርቅ ወቅት ከህዳሴ ግድቡ የሚለቀቀው ውኃ ጉዳትን በመቀነስ መርህ (Release-Based Mitigation) ሊሆን ይገባል የሚለው ደግሞ ሌላኛው ነጥብ ነው።
እስካሁን በተካሄደው ድርድር ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ለድርቅ ወቅትና ለከባድ የድርቅ ወቅት የተሰጡት ትርጓሜዎች ይገኙበታል። ለእነዚህ ጉዳዮች የተሰጠው ትርጓሜ ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚመጣውን የውኃ መጠን መሠረት ያደረገ ነው።
በዚህም መሠረት ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሆነ የድርቅ ወቅት አመላካች እንደሚሆን፣ ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ደግሞ የከባድ ድርቅ ወቅት አመላካች እንደሆነ ስምምነት መደረሱን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የሰጧቸው መግለጫዎች ያመለክታሉ።
ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ በአሜሪካ በተካሄደው የመጨረሻ ድርድር ወቅት ወሳኝ ነጥቦችን በማንሳት፣ ሰፊ ክርክር ተደርጎባቸው ተቀባይነት እንዳገኙ ገልጸው ነበር።
በዚህ መግለጫቸው ወቅት፣ ‹‹ዛሬ የድርቅ ወቅት ነው ብለን የተስማማንበት ጉዳይ ወደፊት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ ባለው የተፋሰሱ አካባቢ በምታካሂደው ልማት ምክንያት ቢቀንስ፣ ይኼንኑ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት የሚል ነጥብ በማንሳት ረዥም ጊዜን የወሰደ ክርክር ተካሂዶበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፤›› ብለው ነበር።
ወደ ህዳሴ ግድብ የሚመጣው የውኃ መጠን በትነትና በሥርገት አማካይነት የሚባክነውን ተቀናሽ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ በኢትዮጵያ በኩል በተነሳው አዲስ የድርድር ነጥብ ላይ ውይይት ተደርጎ፣ በዚህ ምክንያት የሚባክነው የውኃ መጠን በአገሮቹ መካከል በእኩል ተካፍሎ ሊሰላ እንደሚገባ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል። በድርቅ ምክንያት ሳይሆን ኢትዮጵያ ከግድብ በላይ በምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ምክንያት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን የቀነሰ እንደሆነ፣ ይኸው ጉዳይ ከግምት እንዲገባ ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ ባለሙያ ረቂቅ የስምምነት ሰነዱን እንደተመለከቱት በመጥቀስ፣ ድርቅና ከባድ ድርቅን በተመለከተ ስምምነት የተደረሰው ኢትዮጵያ ወደ ግድቡ የሚመጣውን ውኃ በቀጥታ እንድታሳልፍና ክስተቱም ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ በግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይ እንድትለቅ የሚያስገድድ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱም ሆነ በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢ አዲስ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ምክንያት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሆነ፣ እንደ ድርቅ ወቅት ተቆጥሮ የመጣው ውኃ በሙሉ እንዲለቀቅ ስምምነት መደረሱ በመጪው ትውልድ የልማት ፍላጎት ላይ እንደ መወሰን ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በስምምነቱ መሠረት የመጣውን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በቀጥታ እንድታሳልፍ፣ የድርቅ ሁኔታው ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ ደግሞ በግድቡ ከተያዘው ውኃ ላይ በመልቀቅ ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በዓመት እስከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ኢትዮጵያ እንድትለቅ ግዴታን እንደሚጥል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ካላደረገች ቅጣት የሚጣልባት፣ ቅጣቱም በግድቡ የያዘችውን ውኃ በአምስት ዓመት ውስጥ የመልቀቅ ግዴታን የሚጥል እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም ግድቡ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን፣ በድርቅ ወቅት ለግብፅ አገልግሎት የሚሰጥ መጠባበቂያ ነው ሲሉ ተችተዋል።
አሁን ወደ ግድቡ የሚደርሰው ዓመታዊ አማካይ የውኃ መጠን 49.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሆነበት ምክንያት በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢ ውስን የልማት ሥራዎች በመከናወናቸው ብቻ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ይህ በግልጽ እየታወቀ 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የውኃ መጠንን የድርቅ ወቅት አመላካች አድርጎ መስማማት ስህተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ይህንንም ሲያስረዱ በረቂቅ ስምምነቱ ምክንያት ለኢትዮጵያ የተፈቀደው የውኃ መጠን በ49.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እና በ37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መካከል ያለው መሆኑን፣ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ወደፊት በዓባይ ውኃ ላይ ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ብትፈልግ፣ ከምታቅደው የልማት ፕሮጀክትና ከግድቡ የኃይል አቅርቦት መካከል የመምረጥ ግዴታ ውስጥ እንድትወድቅ ያደርጋታል ብለዋል።
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እየተደረገ ያለው ድርድር ህዳሴ ግድቡን የተመለከተ ብቻ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን ለሌሎች ልማቶች ከማዋል የወደፊት ፍላጎቷ ጋር ፈጽሞ እንደማይገናኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በላይኛው የተፋሰሱ አካል ላይ በምታከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት የሚመጣ የውኃ መጠን ለውጥም ተገናዝቦ በስምምነቱ እንዲካተት፣ ስምምነት መደረሱን በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
በመፍትሔነትም ይህ ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጓዳ መሆኑን በማስረዳት አቋርጣ መውጣት እንዳለባት ይመክራሉ። በግድቡ ላይ የሚደረገው ቀጣይና የመጨረሻ ድርድር ከረቡዕ የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአሜሪካ የሚካሄድ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም ወደ ሥፍራው አቅንተዋል።
ሚኒስትሩ ስለሺ (ዶ/ር) በቲውተር ገጻቸው ለቀጣዩ ድርድር አሜሪካ መግባታቸውን፣ ሒደቶቹን በጥንቃቄ በመከታተል የኢትዮጵያን ጥቅም እንደሚያስከብሩ አስታውቀዋል።
ሪፖርተር