Feb 19-2020

ኢሳያስ አፈጨርቂ Feb 9/2020 (B B C)ወኪሎች በትግርኛ በተደረገላቸው ቃለመጠይቆች ከሰጥዋቸውን መልሶቻቸው ፤ከኢትዮጵያ ጋር በተዛመደ ከሰነዘርዋቸው አስተያየቶች ከዚህ ቀጥሎ ባሉትን ጥቂቶች ላይ ያለኝን እይታ ላጋራችሁ፦

1 . ‘በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገ ጦርነት የውጭ ሃይሎች ገብተው አወሳሰቡት ፤ ‘የአረቦች ፣ የአሜሪካንና የምዕራባውያን መንግሥታት እጆች ነበረበት’ አሉ። ይህንን ሊነግሩን የሞከሩት ከምን አንጻር ይሆን ? የኢትየጵያ ሕዝብ የማያውቀው ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተደበቀ ሚስጥር ላውጣና እንደ ውለታ ይቁጠሩልኝ ከማለት አኳያ ይሆን? ይህንን ሊነግሩን መሞከር የኢትዮጵያውያን ፖለቲካው ንቃተ ኅሊና በጣም ዝቅ አድርጎ መገመት ወይም መናቅ አይሆንምን?

እርሳቸውስ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተጫወቱትን ሚና ለምን አልተናገሩም? ለምን የሌሎችን ደባ ብቻ መናገርን መረጡ? ኢትዮጵያን ለማጥፋት እርሳቸውና ወያኔ/ህወሃት ከላይ ለተጠቀሱት አገራት መንግሥታት ቅጥረኛ (mercenary) እንደነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያውቅ መስሏቸው ይሆን? የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ይህንን ፣ በነዳጅ ዶላር ከሰከሩ አረቦች እርዳታ ለማግኘት ማንነታቸውን መሸጣቸውን ፤ ማለት የአረብ ዘር ነን ማለታቸውም ያውቃል/ እናውቃለን ።

2.ከኢትዮጵያ ‘የመገንጠል መኞት ስላላቸው ያላቸውን ሃይሎች ዓላማ እንደማይደግፉ’ ተናግረዋል። በአስተያየታቸው ብንደሰትም ፣በመርህ ደረጃ ከእርሳቸው ተግባር የሚጣረስ አይሆንምን? ከኢትዮጵያዊነት በመሸሸ፣የኢትዮጵያ አገራዊ ሉዓላዊነትን በማፍረስ ሀ ብለው የጀመሩ ሞዴል ፀረኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አይደሉምን? ወይም እንግሊዞች ጥቁር በግ (black sheep) በማለት የሚጠሩት በጥባጭ በግ አይደሉምን? ተገንጣዮች ሲኮተኩቱ አልነበረምን? አሁን ጣፋጭ የሆኑት ለራሳቸው ጥቅም ወይስ ለኛ?

ደግነት ወይም ልግስና ከቤት ይጀመራል እንዲሉ፣ ሌሎችን ከመምከራቸው በፊት ለምን በራሳቸው ላይ ሂስ አይሰነዝሩም። ተሳስቼ ነበር፣ ኤርትራና ኤርትራውያን የኢትየጵያ አካል ናቸው ፣ወደ እናት አገራችን እንመለሳልን ለምን አይሉም? ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ኤርትራውያን ወገኖቻችን ያተረፉትን ጥቅምና የደረሰባቸውን ጉዳት ፤ በእውነት ስለእውነት ለምን አይናገሩም ?

አሁን ስሟን የረሳኋት፣ ኤርትራ ለመጎብኘት ዕድል ከገጠማቸው የቢቢሲ (B B C) ጋዜጠኞች አንዷ፣ ስለኤርትራን ሕዝብ ፦ (ሰቆቃ፣ መከራ፣ እርዛት ፣ረሃብ ፣ስደት ወዘተርፈ) ስትገልጽ ፤ አንድ ብርጭቆ ሻይ ለሶስት ወይም ለአራት እስከመጠጣት መድረሳቸውን ገልጻለች። ኤርትራውያን ለሰላሳ ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጉት ለዚህ ነበርን? በማለት በአግራሞት ጠየቀች ።

3. “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ‘ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥ’ ኤርትትራን እንደጎረቤት ሳይሆን ራስዋን በቀጥታ ‘ስለሚጎዳት’ እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም።” ይህ አባባል ምንን ያምላክታል? በኢትዮጵያ የሚደረገው ፖለቲካዊ ለውጥ ለኤርትራ ሥጋትና አሉታዊ መሆኑን መግለጻቸው ከምን አንጻር ይሆን? ኤርትራውያን ያምጹብኛል ማለታቸው ይሆን? ኤርትራውያን ተንጋግተው ወደ ኢትዮጵያ ጎርፈው ብቻዬን እቀራለሁ ከማለት ይሆን?

ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት አንድ አሥመራ ሄዶ የመጣ ሰው ሲያጫውተኝ ፤ ‘የኤርትራውያን ትልቁ ሥጋት በምዕራብና በምሥራቅ ጀርመን መካከል የተገነባውን ዓይነት ግንብ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እንዳይገነባ ነው ፤ ምክንያቱም ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር መቀላቀል ይፈልጋሉ’ አለኝ።

ወያኔዎች ወደ እኔ ይዞራሉ፣ በእኔ ላይ ያሳምጻሉ፣ ይወሩኛል፣ ጦርነት ሊያስነሱብኝ ስለሚችሉ ቆቅ ሆኜ እጠብቃለሁ ማለታቸው ይሆን? በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ምክንያት ለአቶ ኢሳያስ ሥጋት ከጠቀስኳቸው ሌላ ምን ሊሆኑ ይችላሉ ? አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ለውጥ ለኤርትራ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መኖሩን መጥቀስ ለምን አልፈለጉም?

4 አቶ ኢሳያስ .’በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በሁሉም አቅማችን እንደግፏለን’ ሲሉ ምን ማለታቸው ይሆን? ከላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥ ኤርትራን….’ስለሚጎዳት እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም’ ካሉት ጋር አይቃረንምን? ከደገፉስ ፣ድጋፋቸው ከምን ምን አንጻር ይሆን? ኢትዮጵያን ዲሞክራታይዝ ከማድረግ (..) ? ወያኔዎች በአብይ መንግሥት ላይ ቢያምጹ ከአብይ ጎን ለመሰለፍ? ለአብይ የሥነአገዛዝ ምክር ለመስጠት …..? የመሪዮቻችን የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ስነልቦና ፣ አስተዳደራዊ ብቃትና የፖለቲካ ስክነት ስለሚያንሳቸው ፤ ድሮ በጠብ ያቃወሱትን አገራችን አሁን በብልጣ ብልጥነት ዲፕሎማሲ እንዳያቃውሱን እሠጋለሁ ።