ፖለቲካ
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያበሳጨው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀባበል
19 February 2020
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ግንኙነት ለማጠናከር፣ በቀጣይ የትብብር አቅጣጫዎች እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ለመገናኘት ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ያመሩ ሲሆን፣ በዕለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የጫነው ተሽከርካሪ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በር ላይ ሲደርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን ደኅና መጡ አቀባበል ለማድረግ እየጠበቋቸው ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፕሮቶኮል ኃላፊዎች የመኪናውን በር ከፍተው ሚኒስትሩ እንዲወጡ ሲጠየቁ የሚጠብቁት ሰው እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ ከዚያም ወዲያው ይጠበቁ የነበሩት ግለሰብ የፖምፒዮ ፎቶግራፈር መሆናቸውን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በብስጭት ፊታቸውን አዙረው ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ሲያቀኑ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኋላ ተከትለው ሰላምታ ሲያቀርቡላቸው በምሥሉ ላይ ይታያሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያደረጉትን ውይይት ከጨረሱ በኋላ ዓብይ (ዶ/ር) ከፖምፒዮ የፕሮቶኮል ኃላፊዎች ፈቃድ ውጪ መኪና እያሽከረከሩ ምሳ ወደሚበሉበት ቦታ ወስደዋቸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ፖምፒዮ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ስላለው ለውጥ በዝርዝር የተወያዩ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቀንድን የፀጥታና የሰላም ሁኔታ በዘላቂነት ማረጋገጥም ተመክሮበታል፡፡ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተው መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ስለዓባይ ግድብና ስለሚደረገው ድርድር ተጠይቀዋል፡፡ ፖምፒዮም ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ እያደረጉ ያለውን ድርድር አሜሪካ ከመታዘብ ያለፈ ሚና እንደሌላት ቢገልጹም፣ ሰሞኑን በነበሩት የድርድር ስብሰባዎች አሜሪካ የኢትዮጵያ አደራዳሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረች መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሁሌም ከሚዲያው ጋር ውዝግብ የማያጣቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፖምፒዮ፣ በቅርቡ በተመሳሳይ ከናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ (ኤንፒአር) ጋዜጠኛ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ የኤንፒአር ጋዜጠኛዋ ሜሪ ሉዊዝ ኬሊ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ያባረሯቸውን በዩክሬን የአሜሪካ አምባሳደርን እንዳልተከላከሉላቸው ፖምፒዮን ስትጠይቃቸው፣ ቃለ ምልልሱን የተስማሙት በኢራን ጉዳይ ላይ መግለጫ ለመስጠት እንደሆነ በመንገር ለጥያቄው አጥጋቢ መልስ ሳይሰጡ የነበራቸውን ቆይታ አቋርጠዋል፡፡ ከዚያም ጋዜጠኛዋን ሌላ ክፍል ውስጥ አስጠርተው እንደጮሁባትና ስለዩክሬን ጉዳይ መጠየቃቸው እንዳላስደሰታቸው ነግረዋት፣ ‹‹አሜሪካ ስለዩክሬን ትጨነቅ ይመስልሻል?›› ብለው እንደጠየቋት ተናግራለች፡፡ ፖምፒዮም ዩክሬንን የዓለም ካርታ ላይ ማመላከት ትችል እንደሆነ ጋዜጠኛዋን ጠይቀዋት እንደምትችል ስትነግራቸው፣ ረዳቶቻቸው የአገሮች ስም የሌለበትን ካርታ አምጥተውላቸው እሷም ዩክሬን ያለችበት ቦታ ማሳየቷን ገልጻለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ጋዜጠኛዋ ከቃለ ምልልሳቸው በኋላ የነበራቸው ቆይታ ለሕዝብ ይፋ እንዳይደረግ ተስማምተው ያደረጉት መሆኑን በመግለጽ፣ ጋዜጠኛዋ ዋሽታኛለች ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ረቡዕ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፡፡