19 February 2020
የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ እየተደረገ በሚገኘው ድርድር ጫና እንደ ደረሰባቸው ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩት የሕግና የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበተደረገ የውይይት መድረክ ላይ ገለጹ።
ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አመቻችነት የህዳሴ ግድቡን የውኃ አሞላል አስመልክቶ እየተካሄደ የሚገኘው ድርድር፣ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሒደት ነው ብለው እንደማያምኑ መናገራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ውይይቱን እንዲከታተሉ የተወሰኑ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ተጠርተው የነበረ ቢሆንም፣ ውይይቱ ከተጀመረ በኋላ የውይይቱን ይዘቶች እንዳያስተላልፉ መመርያ እንደተሰጣቸው ተሰምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይት መድረኩን ከከፈቱ በኋላ ጥሪ እንደ ተደረገላቸው ሌሎች ተሳታፊዎች በታዳሚነት የተከታተሉ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ መድረኩ ከተከፈተ በኋላም የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ሁለት ሰዓት የፈጁ የድርድሩን ሒደትና ይዘት የተመለከቱ የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ጠቁመዋል። ሚኒስትሩ ገለጻቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት አስተያየት እንዲሰጡ መጋበዛቸውን፣ የድርድሩ ሒደትም በአሜሪካ መንግሥት በተወከሉ ታዛቢዎች ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ይፋ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥትን ወክለው ድርድሩን የሚታዘቡ ኃላፊዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ‹‹ኮንሲኩዌንስ (ችግር) ያመጣባችኋል›› በማለት በኢትዮጵያ ቡድን አባላት ላይ ጫና ያደርጉ እንደነበር፣ በግልጽ ለመድረኩ መናገራቸውን ምንጮች አስረድተዋል።
በዚህና መሰል ጉዳዮች ምክንያትም የግብፅ ተደራዳሪዎች የዓባይ ውኃን በተመለከተ፣ ግብፅ ዳግም የበላይነት መቆጣጠር እንዳለባት የሚያመላክቱ አቋሞችን ያራምዱ እንደነበር፣ ተደራዳሪዎቹ ለመድረኩ እንዳስረዱ ከምንጮቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
በግብፅና በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች መካከል መጥበብ ያልቻሉ የልዩነት ነጥቦች ናቸው ያሏቸውን ለመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚመጣውን የጥቁር ዓባይ የውኃ መጠን መሠረት ያደረጉ ነጥቦችን ስታነሳ፣ የግብፅ ተደራዳሪዎች ግን የጥቁር ዓባይ አጠቃላይ የተፈጥሮ ፍሰትን የድርደሩ መሠረት በማድረግ የግድቡ አሞላል እንዲወሰን መጠየቃቸውን፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በዋነኝነት ማንሳታቸውን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።
በዚህም ምክንያት እየተደረገ ያለው ድርድር ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሒደት ነው ብለው እንደማያምኑ ለመድረኩ እንዳስታወቁ ምንጮቹ አስረድተዋል። የውይይት መድረኩ ለግማሽ ቀን ብቻ የተያዘ በመሆኑ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን፣ ሚኒስትሮችና ታዋቂ ሰዎች ጥያቄዎችን እንዳላነሱ ነገር ግን ውይይቱ ከቀናት በኋላ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በስፋት እንዲቀጥል መወሰኑን ገልጸዋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ (ዶ/ር) ከሳምንት በፊት ሰጥተውት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በድርድሩ ጫና ተሰምቷቸው እንደሆነ ቀርቦላቸው ለነበረ ጥያቄ፣ ‹‹አዎ፣ ጫናዎች መኖራቸው አይቀርም። ጫናዎች በእኛ ተደራዳሪዎች ላይ ነበሩ፣ በሌሎች አገሮች ተደራዳሪዎች ላይም ነበሩ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ለሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በመሆን ማክሰኞ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ አገራቸው ጣልቃ እንደማትገባና ሦስቱም ተደራዳሪ አገሮች ልዩነቶቻቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ሪፖርተር