ሰሞኑን ጎንደር ካሉ ገዳማት ባንዱ የነበሩ ቅዱስ ጽኑ መናኝ አባቴ ከሐምሳ ዓመት በላይ ዘግተው ሲጋደሉ ከነበሩበት የተጋድሎ ሕይዎት በማረፋቸው ሔጀ ለ13 ቀናት ያህል ከብዙኃን መገናኛዎች መረጃ ውጭ ሆኘ ቆይቸ ስለነበር ትናንት ስመለስ የብዙኃን መገናኛዎች ስልሳ ሦስት እስረኞች የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት!” በሚል ብልጣብልጥ የሽፋን ምክንያት መፈታታቸውን ሲዘግቡ፣ ዮሐንስ ቧያለው የመለስ አመራር አካዳሚ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ሆኖ መሾሙን ሌላም ሌላም ነገሮችን ስሰማ በዚህ ሁለት ሳምንት ብዙ ነገር ያመለጠኝ መስሎ ተሰማኝ፡፡ በርግጥም ስንት ልጽፍባቸው የምችላቸው ጉዳዮች አምልጠውኛል!!!

ሕዝባችን ሲበዛ የዋህ ነው፡፡ የታሰረ ሁሉ ጀግና ይመስለዋል፡፡ አገዛዙም ይሄንን የሕዝባችንን ጅልነት ስለሚያውቅ ወደፊት በከባዱ ሊጠቀምባቸው የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ያስርና የጀግ ካስባለ በኋላ አውጥቶ ብዙ ይጠቀምባቸዋል፡፡ የወያኔን ዘመን የፖለቲካ ታሪክ ወደኋላ መለስ ብላቹህ ብትመለከቱ አገዛዙ በዚህ ሒሳብ አስሮ የፈታቸውና እየተጠቀመባቸው ያሉ በርካታ ግለሰቦችን ታገኛላቹህ!!!

እንደምታስታውሱት ስሙን ዐሥሬ የሚቀያይረው ክርስቲያን ታደለና አብረውት የታሰሩት ሲታሰሩ ሁለቱ ካድሬዎች ክርስቲያን ታደለ እና በሪሁን አዳነ የታሰሩት ከላይ በነገርኳቹህ ሸፍጠኛ የአገዛዙ ስሌት እንደሆነ ነግሬያቹህ ነበረ፡፡ ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ እንደሚፈቱም በእርግጠኝነት ነግሬያቹህ ነበረ፡፡ ያልኩትም አልቀረ በሪሁን እስርቤት በመቀመጡ በብአዴኑ በዐሥራት ሚዲያና በበረራ ጋዜጣ ሥራ ላይ ክፍተት ስለተፈጠረ እንዴትና በምን ምክንያት እንደፈቱት እንኳ ሳይገልጹ በመታሰሩ ሕዝቡ ጀግና አድርጎ የቆጠረውን በሪሁንን ፈቱትና ወደ ሥራው መለሱት፡፡ አሁን በሪሁን የአገዛዙን ጥቅም ለማስጠበቅና የአማራን ጥቅም ለመጉዳት ዐሥራትና በረራ ላይ ምን እየሠራ እንደሆነ በግልጽ እየተመለከታቹህት ነው!!!

ክርስቲያን ታደለ ሲታሰር ከሌሎቹ የብአዴን ቁ.2 አብን አመራሮች ተለይቶ የታሰረበት ምክንያት ብአዴን አብንን በካድሬዎቹ ሲያቋቁም አክራሪ ብሔርተኛ ሆኖ በመሪ ተዋናይነት እንዲተውን ያደረገው በቀድሞ ስሞቹ ደምለው ከዚያም መንግሥቱ ተብሎ ይጠራ የነበረውን የዛሬውን ክርስቲያን እንደሆነ የምታውቁት ነው!!!

የአማራን ትግል ለመግደል ከሰኔ 15 ጀምሮ በተወሰደው የዘመቻ እርምጃ ወቅት ግን ክርስቲያን በተሰጠው የአክራሪ የአማራ ብሔርተኛ ገጸ ባሕርይ እንዲተውን ስላልተፈለገና ሳይታሰር ዝም ብሎ እንዲቆይ ቢያደርጉት ደግሞ ሲሠራው የቆየው ትወና እንደነበር ሊታወቅባቸው ስለሆነ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል የሚሉት ርእሰ መሥተዳድር ተደርጎ በተሾሙበት ዕለት በቀጥታ ስርጭት ላይ አክራሪ ብሔርተኛን ታች ድረስ ወርደን መንጥረን እናጠፋዋለን!” እንዳለው በአማራ ብሔርተኝነት የህልውና ትግል ላይ የሚወስዱትን የመደምሰስ እርምጃ እስኪጨርሱ ድረስ ክርስቲያንን እራሳቸው ከፈጸሙት ግድያ ጋር አያይዞ በመወንጀል ታስሮ ቢቆይ እንደሚሻልና በመታሰሩ ጀግና ተደርጎ በሕዝብ መቆጠሩም ለቀጣይ የክርስቲያን የቅጥረኝነት ተልዕኮው እንደሚጠቅማቸው በመታመኑ ነበር ሊያስሩት የቻሉት!!!

አሁን አገዛዙ እንዳለው አንዳንድ ስለተሰወሩ ያላሰራቸው የአማራ ብሔርተኞች ቢኖሩም የአማራን ብሔርተኝነት የህልውና ትግል ደምስሸዋለሁ!” ብሎ ስላሰበ እነ ክርስቲያንን ከእስርቤት ማውጣት አስፈለገውና አወጣቸው፡፡ አብን በቅርቡ አሜሪካ ለሚያደርገው ጉዞም ክርስቲያንን ከፊት አሰልፎ ልዑኩን በመላክ አገዛዙ በብአዴን ሊያገኘው ያልቻለውን አማራ በአብን ሊጠልፍና ሊያጃጅልበት አዘጋጅቶታል!!!

ይሁንና አብን በሚያደርገው የአሜሪካ ጉዞ ጨርሶ ማሰብ ማገናዘብ የተሳነው ዘገምተኛ ካልሆነ በስተቀር፣ በእነ ዮሐንስ ቧያለው የአሜሪካ ጉዞ የተሰበሰበውን የካድሬ ጥርቅምና ከብአዴን ባለሥልጣናት የቅርብ ዘመዶች በስተቀር አንድም አማራ በብአዴን ቁ.2 አብን የአሜሪካ ጉዞ ሰው ይገኛል የሚል ግምት የለኝም!!!

ዮሐንስ ቧያለውን የአማራ ተቆርቋሪ አድርጋቹህ በማሰብ በእነ ዮሐንስ ቧያለው የአሜሪካ ጉብኝት ወቅት ተገኝታቹህ የልዑካን ቡድኑ ያሰማቸው በነበሩ የመደለያ ዲስኩሮች ተጃጅላቹህ የነበራቹህ ወገኖች ያ የአማራ ተቆርቋሪ!” ያላቹህትና በመጃጃል የማይገባ ተስፋ የጣላቹህበት ሰው ዛሬ የቀንደኛውን የአማራን ጠላት የአቶ መለስን ፀረ አማራ አስተሳሰር አመራርና ውርስ ለማስቀጠል የሚሠራው የመለስ አካደሚ ፕሬዘደንት ሆኖ ከመቀመጡ መውሰድ ያለባቹህ ትምህርት የፈለገ ተአምር ቢፈጠር የፀረ አማራው የብአዴን ባለሥልጣናት ተቆርቋሪ እየመሰሉ በመተወን አማራን ያጃጅላሉ እንጅ ፈጽሞ አማራን ለማጃጃል እንደሚያስመስሉት ሆነው ሊገኙ የማይችሉ የማይፈልጉም መሆናቸውን ነው!!! ይሄንን በመረዳት ቢያንስ ከዚህ በኋላ እንኳ ከመጃጃል ብትታቀቡ ምን ይመስላቹሃል ወገኖቸ???

አገዛዙ አማራ ተስፋ ቆርጦ ወደ አልሆነ ነገር እንዳይገፋ ለማድረግ ብአዴን ውስጥ በየጊዜው የአማራ ተቆርቋሪ መስለው የሚተውኑ ባለሥልጣናትን መድቦ አማራን ያጃጅላል፡፡ ከዚህ ቀደም ደመቀ መኮንን ሲተውን ነበረ፣ ገዱ ሲተውን ነበረ፣ ሌሎቹም ሲተውኑ ነበሩ በቅርቡ ዮሐንስ ሲተውን ነበረ፡፡ አገዛዙ አማራ በእነኝህ ግለሰቦች የያዘውን አጉል ተስፋ በመቅጨት ሥነልቡናውን በመጉዳት፣ ቅስሙን መስበርና አንገቱን በማስደፋት ማኮማሸሽ ሲፈልግ ደግሞ ተታሎ ተስፋ የጣለባቸውን እነኝህን አስመሳይ ግለሰቦች በወሳኝ ሰዓት ላይ ለአማራ ሳይሆን ለአገዛዙ ያላቸውን ጽኑ ታማኝነት የሚያሳይ ተግባር በመፈጸም እንዲያሳዩ በማድረግ በአማራ ሥነልቡና ሲጫወትና ሲቀልድ መቆየቱና እየተጫወተ መሆኑን የምታዩት ነው!!! በዚህ ታስቦ በሚፈጸም የሥነልቡና ጥቃትም ሕዝቡ አእምሮው እየተጎዳ እየነፈዘ መጥቷል!!!

ሌላው ሊገባቹህ የሚገባው ወሳኝ ነገር ቢኖር አገዛዙ የብአዴንን ባለሥልጣናት በየጊዜው እየቀያየረ የቀንደኛውን የአማራን ጠላት የአቶ መለስን ፀረ አማራ አስተሳሰብ፣ አመራርና ውርስ ለማስቀጠል በሚሠራው የመለስ አካዳሚ ፕሬዘደንት እያደረገ ሲሾምና ተሿሚዎቹ ብአዴኖችም ሹመቱን አሜን ብለው ሲቀበሉ ብአዴን በወያኔ ላይ ዐመፀ፣ ወያኔ ተሸንፎ መቀሌ ገባ፣ ለውጥ መጣ!” ምንንትስ ቅብርጥስ እያላቹህ የምትቃዡት ቅዠት ውሸት መሆኑን ነው መረዳት ያለባቹህ!!!

ብአዴን እንደምትሉት በወያኔ ላይ ያመፀና እራሱን ከወያኔ ባርነት ነጻ ያወጣ ቢሆን ባለሥልጣናቱ የቀንደኛው የአማራ ጠላት የአቶ መለስን ፀረ አማራ አስተሳሰብ አመራርና ውርስ ለማስቀጠል የሚሠራው የመለስ አካደሚ ፋውንዴሽን ፕሬዘደንት እየተደረጉ ሲሾሙ ሹመታቸውን አሜን ብሎ ተቀብሎ እንዲሠሩ ያደርግ ነበረ ወይ እነ ነፈዞ??? በነገራችን ላይ የመለስ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት የነበረው ያ ዘገምተኛ ዓለምነው መኮንንንስ ምን ላይ ተሾመ??? ከቀጣይ ጊዜ ጠብቁ ባሕርዳር ላይ ተሹሞ ይመጣላቹሃል!!!

እናም እባካቹህ ንቁ??? ሰው እንዴት ዕድሜ ዘመኑን የአገዛዙ ድራማ መጫወቻ ሆኖ ይኖራል???

እኔ በጣም ግርም የሚለኝ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላቹህ??? በፊትስ እሽ አብን ብለው የተደራጁት ምንነታቸውንና ማንነታቸውን ሁሉም ሰው አያውቅ ስለነበረ ቢሸወድ የሚገርም ላይሆን ይችላል፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን አብኖች በሙሉ ካድሬዎችና በብአዴን ከወረዳ አሥተዳዳሪነት ሳይቀር ተነሥተው ተወስደው አብንን እንዲመሠርቱ እንደተደረጉ ሲታወቅ፣ በተለይም በሰኔ 15 የፀረ የአማራ ትግል የግፍ ግድያ ጊዜና በኋላም የአማራ ሕዝብ ይሄንን የአገዛዙን የፀረ አማራ ትግል እርምጃ እንዳይቃወምና አገዛዙ ይሄንን የፀረ የአማራ ትግል ዘመቻውን ያለምንም ችግር እንዲቋጭ የተጫወቱት የማይተካ የክፉ ባንዳ ሚና ከታየ በኋላ ሰው እንዴት ይሄንን ድርጅት ለአማራ ሕዝብ የሚታገል የቆመ የመጣ ድርጅት አድርጎ ይቆጥራል በሞቴ???

በተለይ ደግሞ ፊደል የቆጠረውና የተሻለ ግንዛቤ አለው የሚባለው ክፍል እንዲህ አስቦ መጃጃሉ እጅግ እግጅ እጅግ ነው የሚገርመኝ!!! ይሄ ነገር የእኛ የማሰብ የማገናዘብ አቅም ወይም ችሎታ እጅግ እያሽቆለቆለ መሔዱን ሁሉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል!!!

በዚህ አጋጣሚ የግፍ እስረኞችን እንኳን እግዚአብሔር አስፈታቹህ ማለት እወዳለሁ!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው