ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
26 February 2020
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በጠብና በሰላም የተሟሸ ውስብስብ ግንኙነት እንደሆነ በርካቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ አዲሲቷ የአፍሪካ አገር በመሆን እ.ኤ.አ. በ1994 የተመሠረተችው ኤርትራ፣ በመጀመርያዎቹ ዓመታት በርካቶች የመጀመርያው ጫጉላ በማለት በሚጠሩት የፍቅር ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት ነበራት፡፡ ሆኖም ይኼ የጫጉላ ጊዜ ዕድሜው አጭር ሆኖ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሁለቱም ወገን የታሪክ ጠባሳን ያሳረፈ የጦርነት ታሪክ እንዲኖራቸው ተደረገ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሆኖ የበርካቶች ሕይወትም ተመሰቃቀለ፡፡ ይኼ ጦርነት አንዳንዴ የወንድማማቾች ጦርነት አንዳንዴም ሁለት መላጦች በሚዶ (ማበጠሪያ) ሳቢያ የሚያደርጉት ጦርነት፣ እየተባለ ሲነገርለት ነበር፡፡ በመጨረሻ ቤተሰብን በመለያየትና የሁለቱንም አገሮች ኢኮኖሚ በመጉዳት ተጠናቀቀ፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በአኅጉራዊና አካባቢያዊ ኃይሎች ጥረት ለጦርነቱ ማብቂያ በአልጀርስ ከስምምነት ቢደረስም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት የመፋጠጥና የመተነኳኮስ ጊዜ ከማምጣት የዘለለ ሚና አልነበረውም፡፡ በዚህ ሁኔታ ዓመታት እንደ ዘበት አለፉ፡፡
እነዚህን 20 ዓመታትና የጦርነቱን ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የተመለከቱና ጥናት የሠሩ የታሪክ፣ የፖለቲካና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው በሁለቱ አገሮች ሳይሆን በሁለቱ አገሮች መሪዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ስለነበር ነው ሲሉ ይገመግማሉ፡፡ በመሪዎቹ እልህ ሳቢያም ለ20 ዓመታት የዘለቀው ሰላምም ጦርነትም አልባ ወቅት እንዲፈጠርና ተያያዥ ችግሮች እንዲከሰቱ በር ከፍቷል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም በዓለም መድረክ የተፈራረሙትን ስምምነት ወደ ጎን በመተው ለፍፃሜው አንድ ዕርምጃ እንኳን ለመራመድ ድፍረት ከማጣትም በላይ፣ ፍላጎት አልነበረምና የባለ ብዙ ወገን የዓለም ግንኙነት በእነርሱ ዘንድ ያለውን ሥፍራ ያጠየቀ ነበር ሲሉም ያስታውሳሉ፡፡
ይሁንና በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. በአገሪቱ በታየው ከፍተኛ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ሳቢያ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ውስጥ በመጣው የአመራር መሸጋሸግ ሥልጣን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው አንስቶ ቃል የገቡለትን የኢትዮ ኤርትራ ሰላም ዕውን ለማድረግ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በድንገት ወደ አስመራ በመሄድ የእርቁን ጅማሬ አብስረዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ የሁለቱ አገሮች ድንበር የተከፈተ ሲሆን፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ቤተሰቦች የመስከረም አንድ የዘመን መለወጫን (ቅዱስ ዮሐንስ በዓልን በኤርትራውያን ወገን) በጋራ አከበሩ፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረግ የስልክ ጥሪ ልውውጥና የአየር ትራንስፖርት ወዲያውኑ የተጀመረ ሲሆን፣ በቁጥር በግልጽ የማይታወቅ የሁለቱም አገሮች ዜጎች ድንበር እያቋረጡ ቤተሰብ ሲጠይቁ ነበር፡፡ አባትና እናታቸውን፣ ወንድምና እህታቸውንም በፍለጋ ለማግኘት የታደሉ ቀላል የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን የዚህን ግንኙነት ዘላቂነት የሚያረጋግጡ ስምምነቶች ምንድናቸው? ስምምነቶችስ ዕውን አሉ ወይ? ካሉስ ይዘታቸው ምን ይላል የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት ሲንሸራሸሩ ቢቆዩም፣ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳያገኙ ድንበሮቹ ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ ተዘጉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በየብስ በሕጋዊ መንገድ ድንበር የሚያቋርጥ ሰው እንዳይሆን ሆኖ በጉቦፖለቲካ በማታለል፣ ከኤርትራ በየቀኑ ከ400 እስከ 500 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይነገራል፡፡
ስለዚህም አንዱ ሲፈልግ የሚከፍተው ሳይፈልግ ሲቀር ደግሞ የሚዘጋው ድንበር እንዳይኖርና ይባስ ብሎም ወደ ሌላ ግጭት እንዳያመራ፣ ለድንበር ንግድም ሆነ ለሰዎች ዝውውር ግልጽ ሕግ መበጀት አለበት በማለት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይኼንን የዕርቅ ሒደት የሚመለከት ምንም ዓይነት ሰነድ አለመኖሩ፣ ግርታም ሥጋትም እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይም ስለጉዳዩ ሲጠየቅ እየሠራንበት ነው ከማለት የዘለለ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚናገርና ያለበትን ደረጃ የሚያስረዳ ኃላፊ አይገኝም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ የረገጧት ኢትዮጵያ፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚጠሯትና ስለውስጣዊ ጉዳዮቿ ምክረ ሐሳቦችን የሚያዘንቡላት ሆናለች፡፡
በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቢበዛ በዓመት ሁለቴ ለመንግሥት ጋዜጠኞች በሚሰጡት መግለጫ በአንደኛው ዓርብ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. እና ታኅሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ያስተላለፉት መልዕክት፣ በኤርትራ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በኤሪ ቲቪና በራዲዮ በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው፣ ‹‹በሌላ አገሮች ውስጣዊ ሉዓላዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ባይኖረኝም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከእኛ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፤›› ብለው በማመካኘት አሟሽተው ወደ አስተያየታቸው የገቡት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ተቋማዊ የተደረገው የብሔር አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲሉ ይጀምራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም. ስለመፅደቁ አስተያየት ተጠይቀው የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ እንደማይበጃት ቢናገሩም፣ አድማጭ አጥተው ሕገ መንግሥቱ መፅደቁን ተናግረዋል፡፡ ለተቃውሟቸው ምክንያት ይኼን መሰል ሥርዓት ለኢትዮጵያዊያን አይበጅም በሚል ነበር ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም፣ ‹‹አገሪቱን ከፋፍሎ ለመግዛት ሲባል የተሸረበ ሴራ ነበር፤›› በማለት ይገመግሙታል፡፡ ይኼም የኢትዮ ኤርትራን የድንበር ግጭት እንዳመጣው ያወሳሉ፡፡
ኢትዮጵያም በየአምስት ዓመቱ ምርጫን ስታደርግና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሲያፀድቅላት እንደ ነበር ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይኼ ግን ሥልጣን ላይ ለነበረው አነስተኛ ጠባብ ቡድን ጠቀመ እንጂ ብዙም ፋይዳ አልነበረውም ይላሉ፡፡
ይኼንን የፕሬዚዳንቱን ንግግር የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ገብተው መናገራቸውን ሲተቹ የተደመጡ ሲሆን፣ በተለይ ይኼንን ንግግር ወስደው ያስተጋቡት የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ አብ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ጥቅስ ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸዋል፡፡
ይኼ የአቶ የማነ የትዊተር ጽሑፍ፣ ‹‹አቋማችን የሚያወላውል አይደለም፡፡ ተቋማዊ የተደረገ ብሔርተኝነት መርዛማና የማይጠቅም መሆኑን አጥብቀን እናምናለን፡፡ በእኛ አመለካከትም የዚህ በሽታ መወገድ ለኢትዮጵያ ጥቅም ያመጣል፡፡ በተጨማሪም ኤርትራም ሆነች አጠቃላይ ቀጣናው ከዚህ ተጠቃሚ ይሆናል፤›› ይላል፡፡
ለዚህ የትዊተር ጽሑፍ በዚያው መድረክ በጽሑፍ መልስ የሰጠው የቀድሞ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስኪያጅና በቅርቡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል የሆነው አቶ ጃዋር መሐመድ፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም እንዲመጣ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲቀጥልና እንዲጠናከር የኤርትራ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ክርክሮች ውስጥ እጃቸውን መስደድ ማቆም አለባቸው፡፡ መልካም ያልሆነና የማይጠቅም ነው፡፡ ስለእናንተ ጉዳዮች ብዙ ልንል እንችላለን፣ ግን ምንም አንናገርም፤›› ሲሉ ተችቷል፡፡
ይኼንን ጉዳይ አስመልክተው ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በበኩላቸው፣ የተነሳው ወሳኝ ሐሳብ (Critical) መሆኑን በመጠቆም፣ እንደ ግለሰብ ፕሬዚዳንቱ የፈለጉትን ቢናገሩ ሐሳባቸውን እያንፀባረቁ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ነው የሚያስፈልጋት ለሚለው ጥያቄ ሙሉ ሉዓላዊ መብት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ይኼ በኢትዮጵያውያን የሚወሰን ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
አቶ ናትናኤል ኢዜማ ዜጋ ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት የሚከተል ፓርቲ መሆኑን በመጠቆም፣ የእሳቸው ፓርቲ እንኳን ይኼ መሆን አለበት በማለት በሕዝብ ላይ የሚጭነው ሳይሆን ለሕዝብ ምርጫ የሚተው ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ ወገን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ይኼን ያህል በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ገብተው እንዲናገሩ በር የከፈተላቸው ግን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ዕርቅ መርህ አልባ በመሆኑና የመሀል አገር መንግሥት የብሔር ፖለቲካን በተመለከተ ያለው አቋም የተለሳለሰ ስለሆነ ነው ሲሉ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሊጂ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ትካቦ ይሞግታሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በብዛት ከአገሪቱ እየወጣ ያለው ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚተም የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝሙ ለኢትዮጵያ እንደሠራ በመረዳት ወደ አገሩ ሲመለስ ለሥልጣናቸው ሥጋት ስለሚሆን ትኩረት ሰጥተው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ በኤርትራ የሚገኙ ዘጠኝ ብሔሮች በመንግሥት ውስጥ ውክልና ያላቸው ባለመሆኑ የዚህ ሥጋት አንዱ ገጽታ ነው ይላሉ፡፡
ስለዚህም ሕዝቡ በብዛት እየወጣ ስለነበር ድንበሩ እንዲዘጋ መደረጉን፣ ይኼም ሊመጣ ያለውንን ሥጋት ለመቀነስ ታስቦ ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡
እንደ አቶ ናትናኤል ገላጸ መንግሥት የስምምነቱን ይዘትና የሰላሙን ድርድር በተመለከተ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት እንዳለበት፣ ይኼንን ክፍተት ግን የኤርትራ መንግሥት እየተጠቀመ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እየተናገረ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡
‹‹እንደ መንግሥት እንዲህ ያለ አቋም ይዘው ከሆነ ትክክል አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ናትናኤል፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ የመወሰን ብቸኛው ሥልጣን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤›› በማለትም ይከራከራሉ፡፡
ነገር ግን እስካሁን ባለው ግምገማቸው ሁለቱም አገሮች አንዱ አንዱን ለመጉዳት ያለመ ሳይሆን፣ ለመጥቀም ያለመ ግንኙነት ለመመሥረት ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳንኤል ግን ፕሬዚዳንቱ ባለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የማየት ዕድል ስለገጠማቸው ያንን እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ስለዚህ ባለፉት አሥር ዓመታት ስለኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እምብዛም መረጃ የሌላቸው ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን ባገኙት ዕድል ተጠቅመው ሕልማቸው የሆነውን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በወታደራዊ ኃይል ያልተደላደለች ኢትዮጵያን ለማምጣት እየጣሩ ነው ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በብሔር ስም የተደራጁና ኢትዮጵያን በጦር ለመውጋት ያለሙ የፖለቲካ ቡድኖችን መደገፋቸው እየታወቀ፣ አሁን ግን ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መስለው መቅረባቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው ይላሉ፡፡
ስለዚህም ይኼ ቀይ መስመር ስለሆነ የኢትዮጵያ መሪ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አይግቡ በማለት፣ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ሪፖርተር