ነቀምቴ

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይ ደግሞ ቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያለው የሠላም ሁኔታ የተረጋጋ እንዳልሆነ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

በተጠቀሱት አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ በሚነገረው ታጣቂ ቡድንና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ በተለያዩ ጊዜያት በሰዎች ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል።

ከቅርብ ወራት ወዲህም መንግሥት በአካባቢው ያሉትን ታጣቂዎች ለመቆጣጠር እየወሰዳ ያለውን እርምጃ ተከትሎ የግንኙነት መስመሮች የተቋረጡ ሲሆን በዚህም ሳቢያ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ።

በአካቢው ያለውን ሁኔታና የነዋሪዎችን ስጋት ለመረዳት በቅርቡ የቢቢሲ ዘጋቢዎች በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋች ወደ ሆነችው የነቀምቴ ከተማ አቅንተው ነበር።

በቄለም ወለጋና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ባለው የጸጥታ ስጋት ሳቢያ ጥቂት የማይባሉ የሁለቱ ዞኖች ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጥለው ወደ ነቀምቴ መጥተዋል።

በሁለቱም በኩል እየተጎዳን ነው

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ የመጡ ሲሆን በአካባቢያቸው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለመናገር አስቸጋሪበሚል ይገልጹታል።

በወረዳቸው ውስጥ ቀንም ሆነ ሌት ሠላም እንደሌለና ነዋሪው የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ምን ይፈጠር ይሆን በሚል ስጋት የተመላ እንደሆ ይናገራሉ።

ሠላም ስለሌለ ቀን ብር ይዘህ ስትንቀሳቀስ የመንግሥት ወታደሮችን ትፈራለህ፤ ሌሊት ደግሞ በጫካ ያሉትን ታጣቂዎች ትፈራለህ። ስለዚህ በአካባቢው መነገድም ሆነ ወጥቶ መግባት ከባድ ሆኗል።

ከዚህም የተነሳ እንደእሳቸው በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ነቀምቴና ወደ ሌሎች ከተሞች ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ከሁለቱም ኃይሎች ያጋጥመኛል የሚለውን ጥቃት ለማምለጥ አቅም ያለው በሙሉ ኑሮውን እየተወ ቤተሰቡን በመያዝ እየተሰደደ ነውይላሉ።

ግለሰቡ በአካባቢው ባለ ጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ባሉት ታጣቂዎችና መንግሥት ባሰማራቸው ወታደሮች እንቅስቃሴ ሳቢያ በነዋሪው ላይ እየደረሰ ያለው ጫናና ጉዳት በነዋሪው ዘንድ መረጋጋት እንዳይኖር እንዳደረገ ይናገራሉ።

ቀን ላይ በአካባቢው የተሰማራው የመንግሥት ሠራዊት አነጋግሮን ከሄደ ጫካ ያሉት ታጣቂዎች የመንግሥት ሰላይ ነህ በማለት ሌሊት መጥተው በመውሰድ፤ ምንም ሳያጣሩ እርምጃ ይወስዳሉ።

የመንግሥት ወታደሮች ደግሞ ታጣቂዎቹ ማታ እዚህ መጥተው ነበር፤ እናንተም ምግብ ሰጥታችኋልበማለት ነዋሪውን ሰብስበው ይቀጣሉበማለት ስጋቱ ከሁለቱም ወገን በመሆኑ አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሸሹ እንዳደረጋቸው ይጠቅሳሉ።

በአካባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪው የተለመደውን የዕለት ከዕለት ተግባሩን ማከናወን እንዳልቻለና አንዳንዶችም ለችግርና ለረሃብ እየተጋለጡ ነው ይላሉ።

በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ታጣቂዎች በተመለከተም ሕዝቡ ጫካ ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱት ማንነት እንዲናገር ሲጠየቅ ለህይወቱ ስለሚሰጋ አይናገርም። መንግሥትም ታጣቂዎቹ ሕዝቡ ውስጥ በመሆናቸው ሊለያቸው አልቻለምሲሉ የችግሩን ውስብስብነት ይናገራሉ።

በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቼ ነበር የሚሉት ግለሰቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በአካባቢው በተከሰተው አለመረጋጋት መክንያት ቀያቸውን ትተው ወደ ነቀምቴ እንዲሄዱ ከማድረጉ ባሻገር ሥራቸውን መስራት ስላልቻሉ ከባንክ የወሰዱትን ብድር ለመክፈል መቸገራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ለወራት የዘለቀው ያለመረጋጋት በአካባቢዎቹ ውስጥ ባለው የንግድና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖ በመፍጠሩ ብዙዎቹ ሥራ ማቆማቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ምክንያትም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነዋሪው የሚበላውንም ሊያጣ ይችላል በማለት ይሰጋሉ።

በተጨማሪም በአካባቢዎቹ የስልክና የሌሎች መገናኛ አገልግሎቶች ለወራት መቋረጣቸው ሕዝቡ ስላለበት ሁኔታ በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙት ቤተሰቦቻቸውና በአጠቃላይ ሌሎችም እንዲያውቁ ለማድረግ ተቸግረው መቆየታቸውንም አንስተዋል።

ትንሹም ትልቁም ስጋት ውስጥ ነው

ቀደም ሲል ሲኖርበት ከነበረው ቄለም ወለጋ ሸሽቶ ነቀምቴ የሚገኘውና ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙን ለመናገር ያለፈለገው ወጣት ከቢቢሲ ጋር መነጋገሩ እራሱ ችግር ሊያስከትልበት ይችላል የሚል ስጋት ቢኖረውም የሚያውቀውን ለመናገር ፈቃደኛ ነበር።

ወጣቱ እንደሚለው እነዚህ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ከሌሎቹ ተለይተው በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ በመደረጋቸው በነዋሪው ላይ የሥነ ልቦና ጫና እየፈጠረ ነው።

በእኛ አካባቢ ትልቁም ትንሹም በስጋት ውስጥ ነው የሚኖረውበማለት ሁሉም ነዋሪ ከሁለቱም ኃይሎች አንጻር እየተጎዳ መሆኑን አመልክቷል።

አክሎም ይህንን ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ከባድ ስጋት ውስጥ ሆኜ ነው። ከታየሁ ምን ሊገጥመኝ እንደሚችል በደንብ አውቃሉበማለት ለመናገርም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ ለቢቢሲ ገልጿል።

ወጣቱ በመንግሥት ኃይሎችና በታጣቂዎቹ መካከል ያለው ሁኔታ በቶሎ መፍትሄ አግኝቶ ወደ ተረጋጋ ህይወት መመለስ ይፈልጋል ለዚህም ሠላማዊ መንገድ መፈለግ አለበት ይላል።

ግጭቱ በሁለት ወንድማማቾች መካከል የሚደረግ በመሆኑ በጦርነት እስከመጨረሻው መፍትሄ ያገኛል ብዬ አላምንምበማለት ለችግሩ በውይይት ሠላማዊ መቋጫ እንዲገኝ ይመኛል።

በአካባቢዎቹ ባለው ስጋት የተሞላበት ሁኔታ ነዋሪው ሕዝብ እየተጎዳ እንደሆነና የጸጥታው ሁኔታ ከከተማ ይልቅ በገጠሩ አካባቢ አሳሳቢ እንደሆነና ብዙም መሻሻል እንደሌለ አመልክቷል።

ነቀምቴ

የቢበሲ ዘጋቢዎች በነቀምቴ ከተማ በነበራቸው ቆይታ እንደተገነዘቡት በከተማዋ ውስጥ ከጊንቢና ከደንቢ ዶሎ የተሻለ መረጋጋት ስላለ በአቅራቢያ ባሉ ወረዳዎች የሚኖሩ ሰዎች ካለባቸው ስጋት ለመሸሽ ወደ ከተማዋ መጥተው ይኖራሉ።

በከተማዋ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ቀን ላይ መደበኛና ሞቅ ያለ ሲሆን አመሻሽ አንድ ሰዓት ላይ ግን በመንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሰው ሰው ቁጥር በጣም ስለሚቀንስ ጭር ይላል።

በከተማዋ ያሉ ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ ስለማይፈቀድላቸው፤ ከአስራ ሁለት ሰዓት በኋላ የባጃድ አሽከርካሪዎች ሥራ የሚያቆሙበት ጊዜ እየደረሰ መሆኑን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። በዚህም ሳቢያ የከተማዋ እንቅስቃሴ ምሽት ላይ ይቀዘቅዛል።

በነቀምቴ ከተማ ያሉት ባጃጆች በር እንዲኖራቸው ስለማይፈቀድ ሁሉም በር አልባ ሆነው ወዲያ ወዲህ ሲሉ በሌሎች ከተሞች ውስጥ ካሉ ተሽከርካሪዎች ለየት ብለው ይታያሉ።

በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ሰፍረው ስለሚገኙ እነሱ ባሉባቸው አካባቢዎች አቅራቢያ ማለፍ ለእግረኞች የተከለከለ መሆኑን የሚገልጹ ምልክቶች ይታያሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማዋ የሚመጣ እንግዳ የጎላ የጸጥታ ችግርም ሆነ ስጋት አያጋጥመውም፤ ነዋሪዎች ግን የጸጥታ አካላት አንድ ችግር ቢያጋጥም ሊወስዱት ይችላሉ የሚሉትን እርምጃ በመስጋት በጊዜ ወደ ቤታቸው መሰብሰብን ይመርጣሉ።

በአጠቃላይ በኮማንድ ፖስት ስር የምትገኘው ነቀምቴ ቀን ቀን መደበኛ ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ ቢኖራትም አመሻሽ ላይ ንግድ ቤቶች በጊዜ ስለሚዘጉና ሰዉም ቀድሞ ወደቤቱ ስለሚገባ የነቀምቴ ምሽት ጭር ይላል።

መንግሥት ምን ይላል?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኤታማዦር ሹም የሆኑት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በቅርቡ ለቢቢሲ ሰጥተውት በነበረው ቃል ላይ መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ የተለየወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ተናግረው ነበረ።

ጄነራሉ እንዳሉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ይለመኑ እንደነበርና ልመናው ሲበዛባቸው መጠናከር ጀመሩ፤ ሕዝቡ ላይ የሚደርሰው በደል ተጠናክሮ ቀጠለ። ሕዝብ ያስፈራራሉ፣ ሕዝብ ይዘርፋሉ፣ ያስቃያሉ፣ አፍነው 70 እና 60 ኪሎ ሜትር ይዘው ሄደው ለሁለት ሳምንት ደብድበው ይለቃሉበማለት መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ የተገደደበትን ምክንያት ተናግረዋል።

ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ሠራዊቱ በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ስለሚባለው ክስም በሰጡት ምላሽ እኔ ያደራጀሁት እና እኔ የምመራው ወታደር ሕዝብ አይነካም። የመንግሥት ወታደር ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ ግን መንግሥት ይጠየቃል። እኔም በግሌ ሕዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ እክሳለሁበማለት አስተባብለዋል።

ቢቢሲ