Saturday, 07 March 2020 12:27

አለማየሁ አንበሴ

ኢዜማና ኦፌኮን ጨምሮ ከስድስት የፖለቲካ ድርጅቶች ለቀረቡ አቤቱታዎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳሰበ ሲሆን፤ በዚህ መሰረት ምላሾቹን ትናንትና ከትናንት በስቲያ ሲቀበል ውሏል፡፡
ለቦርዱ አቤቱታ ያቀረቡት ድርጅቶች፡የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የጌድዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ) መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዶ/ር አረጋዊ በርሄ የሚመራው ትዴፓ፤ በትግራይ ክልል አባላቶች ላይ እስር፣ ማስፈራራትና የቢሮ መዘጋት ችግር እንደገጠመው ሲያመለክት፤ ኢዜማ በበኩሉ፤ ህዝባዊ የህዝባዊ ስብሰባዎች መሰናክል በጐንደርና በደብረ ብርሃን እንዳጋጠመው አቤቱታ አቅርቧል፡፡
ኦፌኮ በበኩሉ፤ የአባላት እስርና ማስፈራራት እንደደረሰበት በብ/ጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦብፓ ደግሞ የአባላት እስራት፣ የቢሮ መዘጋት፣ ታፔላ መነቀልና አባላት ማስፈራራት አጋጥሞኛል ብሏል፡፡

ኦነግ ደግሞ የፓርቲ መመስረቻ ፊርማ መነጠቅ አጋጥሞኛል፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችም አባላቶቼ ታስረውብኛል ሲል አቤቱታውን ማቅረቡ ታውቋል፡፡

የጌድኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በበኩሉ፤ የፓርቲ ምስረታ ማሟያ ፊርማ የማሰባሰብ ሂደት መደናቀፍ ገጥሞኛል ማለቱን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል፡፡

የፓርቲዎቹን አቤቱታ የተቀበለው ምርጫ ቦርድም፤ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸው አካላት የካቲት 26 እና 27 ቀን 2012 .ም በቀረቡባቸው ስሞታዎች ላይ ምላሻቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንና የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ የዝዋይ (ባቱ) ከተማ ፖሊስ ምላሽ እንዲያቀርቡ የተጠየቀ ሲሆን፤ ቦርዱ ትላንትና ከትናንት በስቲያ ምላሻቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዲስ አድማስ