Saturday, 07 March 2020 12:27
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በቅርቡ የተመሠረተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በትላንትናው ዕለት ቅንጅት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ “ባልደራስ መኢአድ” በሚለው የቅንጅታቸው መጠሪያ በጋራ ማኒፌስቶና የምርጫ ምልክት እንደሚወዳደሩ ተነግሯል፡፡
ቅንጅቱ የህብረ ብሔራዊነት አደረጃጀት እንዳለው የጠቆሙት ፓርቲዎቹ እስከ ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሎች የቅንጅቱ አካል መሆን የሚፈልጉ ፓርቲዎችን ተቀብለን እናስተናግዳለን ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል አዲስ አበባን መሠረት አድርጐ የተቋቋመው ባልደራስና መኢአድ በመሰረቱት ቅንጅት በቀጣዩ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶቹ ቅንጅት መፍጠራቸውን ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸው ላይ፣ ከምንም በላይ የሀገር ጥቅምና ሉአላዊነትን ያስቀደመ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በአባይ ግድብ ጉዳይ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትንም እንደሚያወግዙ ገልፀዋል፡፡ መላ ኢትዮጵያውያንም ለብሔራዊ ጥቅማችን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል – ፓርቲዎቹ፡፡
አዲስ አድማስ