ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!
ተስፋዬ ከበደ ጥላዬ ማን ነው ??..

በ ቅርብ ጓደኛውና አብሮ አደጉ አሻግሬ መንግስቱ እንደተነገረው፤..…
ተስፋዬ ከበደ ጥላዬ ከ አባቱ ከአቶ ከበደ ጥላዬና ከ እናቱ ከወይዘሮ አማከለች ታዬ ሰኔ ወር 1948 ዓ.ም በ አዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በካቴድራል ካቶሊከ ትምህርት ቤትና በአምሃ ደስታ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት አጠናቋል።
ተስፋዬ ገና በልጅነቱ ከማንኛዉም የዕድሜ ጓደኞቹ በተለየ ሁኔታ የምእራብ አለሙን ፊልም የሚከታተል፤ በእግር ኳስ ጨዋታ የቲም መሪ፤ በትምህርት ውጤቱም አቻ የሌለዉ ጎበዝ ተማሪ ነበር። ተስፋዬ በእድሜ ጓደኞቹ ተወዳጅ ቀልደኛና ለመሪነት ተመራጭ የነበረ በሁሉም ተሳትፎ ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘትን የሚወድ ብሩህ ልጅ ነበር።
በተለይም በእድገቱ ያሳለፈዉ ዘመን በአብዛኛዉ በአልጋወራሽ ግቢ ውስጥ በመሆኑ የመደብ ልዩነትን ፤ በድሀና በሀብታም መካከል ያለውን የተዛባ ልዩነት ቁልጭ ብሎ ለማየት ሰፊ ዕድል ሰጥቶታል። በመሆኑም በአፍላ እድሜዉ ነበር ጭቆና የተንሰራፋበትን ሰርአት መጥላትና መኮነን የጀመረዉ።
ከዚሀም በተጨማሪ የሰድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲም አጎራባቹ በመሆኑ ሌላ ተጨማሪ ንቃትና የ አመለካከት ለዉጥ እንዲኖረው አስተዋፅኦ ካደረጉት ምክንያቶችም የሚጠቀሰ ነዉ።
ገና በለጋ ዕድሜዉ በዩኒቨሲቲዉ ዉሰጥ ይካሄድ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰልፎችና ስብሰባዎች ውስጥ ለመሳተፍ ዕድል በማግኘቱ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነበረ የአብዮታዊነት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የጀመረዉ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም በነበረዉ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በንቃትና በእንቅስቅሴው አመራር ከሚጠቀሱት መካከል ነዉ።
ተስፋዬ በተፈጥሮዉ እርጋታን የተላበሰ፤ በብዙ ስዎች መካከል ሲሆን ብዙ የማይናገር ከቃላት ይልቅ ተግባር ላይ የሚሰራዉን ቀድሞ ሰርቶ የሚገኝ፤ እዩኝ ማለትን የማይፈልግ፤ ለጓደኛና ለወገኑ ታማኝ፤ ላመነበት ዓላማ ሲል ህይወቱን ለመስጠት ቅንጣት ያህል እንኳን የማያወላዉል ነበር።
ይህን አይነት ባህርይ የተላበሰም በመሆኑ ነው የመጨረሻዉን የሞት ፅዋ እስከጨለጠባት ደቂቃ ድርስ የሰዉ ልጅ ሊሽክመዉ የማይችለውን የስቃይ በትር በቁርጠኝነትና በታማኝነት ካለ ምንም ማወላወል እስከመጨረሻውም ድርስ በመቻል የመላእክተ ሞት የመጨረሻ ውሳኔ የቁርጥ ቀን ለት ሲሆንም አብረውት በከፍተኛ 17 አንድ ላይ ታስረው የነበሩት የትግል ጓዶቹ እንደሚናገሩት የድርጅቱን መዝሙር የ ኢሕአፓን “የትግሉ ነዉ ሕይወቴ!” አየዘማረ የወደቀው።
ሕይወት ተፈራ “Tower in the Sky” ተበሎ በተሰየመው መጽሃፍ ላይ ስለ ተስፋዬ ምንም እንኳን የተገናኙት በእስር ላይ ብቻ ቢሆንም የመከራ አቻቻል ፅናቱን ሳትገልጽ አላለፈችም።
በ1966 አብዮት ፍንዳታ ወቅት በትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በክብርዘበኛ ጦር ሰፈር የቅስቀሳ ወረቀቶችን በመበተን ተሳትፏል። የ66 ዓ/ም አብዮት ፈንድቶ የእድገት በሕብረት ዘመቻ በታወጀበት ወቅት ተማሪው በመዝመትና ባለመዘመት በተፈጠረው የሀሳብ ልዮነት ላላመዝመት ከወሰኑት ተማሪዎች መካከል በመሆን በመሃል በደረሰበት የመኪና አደጋ እግሩ በመሰበሩ በአብዛኛዉ የ67 ዓ/ም ዘመንን ያሳለፈው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆስፒታል ነበር።
ከሆስፒታል ሲወጣም አብዛኛው ተማሪ በየዘመቻ ጣቢያው በመሄዱ እሱም ከሆስፒታል በነበረው መረጃ አዲአበባ ውስጥ እንዲዘምት ሆኖ ነበር።
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ሁሉ በህቡዕ የድርጅት ስራ ውስጥ መሳተፍ የጀመረው ገና በጠዋቱ ከኢሕ አፓ መመስረት ቀደም ብሎ ነበር።
በእድገት በሕብረት ዘመቻም ግዜ ለዘማቹ ማንቂያና መማሪያ የተሰናዱትን የ“ተደራጅ” ን መጽሔት በማዳረስና በማሰራጨት ጊዜውን ጉልበቱንና ገንዘቡን በመጨረሻም ዉድ ሕይወቱን ለድርጅት ስራ የሰጠ ቆራጥ የሕዝብ አገልጋይ ነበረ።
በነዚህም ጊዜያት ዉስጥ ተደጋጋሚ የመታሰር ቅጣቶች የተፈጸመበት ቢሆንም ከ ትግልና ከቆመለት አላማ ፈቀቅ አላደረገዉም። በተለየም ከኢሕአፓ መመስረት በኋላ ሙሉ ጊዜዉንና ራሱን ለድርጅቱ ስራ በመስጠት በ ከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አባላት መካከል ዋነኛ ነበር።
በኢሕአፓ የከተማ ታጣቂ ክንፍ (urban Squad)ውስጥ በአመራርና በማሰልጠን ደረጃ በመሳተፍ በ ከፍተኛ ዲስፕሊን ላመነበት አላማ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ እስትንፋስ ድረስ የህዝብ ወታደር በመሆን በመታገል ወድቋል።
በ1970 መጀመሪያዎቹ በኢሕአፓ ድርጅት ውስጥ በተፈጠረዉ የ መስመር ልዩነትና የ አንጃ መፈጠር ብዙ የትግል ጓዶቹ በዓይኑ ላይ በጠራራ ፀሓይ ነፃ እርምጃ በተባለዉ የደርግ የግድያ ዘመቻ ሲረግፉ ለማፈግፈግና ራሱን ለማዳን አልፈለገም። ይልቁንም ሌሎች የትግል ጓዶቹ ሰለባ እንዳይሆኑ ከላይ ታች ሲሯሯጥ ነው በደርግ ሰላዮች እጅ የወደቀዉ።
ተስፋዬ ቀደም ብሎ ወደ ሜዳ ለመዉጣት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ሁሉ አጠናቆ ለመዉጣት የሚችልበትን ዶኩመንት በእጁ ይዞ ለመዉጣት ሲችል የአይምሮ ቁስል የሆነበት ግን ትግሉንና ጓዶቹን በነበረዉ በመጨረሻው ደቂቃ የ አዲስ አበባ መዋቅር ተበጣጥሶ ሁሉም በየግሉ በሚባክንበትና ወጥቶ መግባት እንደ ትልቅ እድል በሆነበት የፈተና ጊዜ መዋቅሩን ለማስቀጠልና ስንት መስዋእት የተከፈለበትን ትግል ጥሎ ላለመሄድ ላይ ታቸ ሲሯሯጥ ነው ሰለባለመሆን የበቃዉ።
የተያዘበትንም ሁኔታ ስንመለክት ይህንንዉ ሀቅ የሚያጎላ ነው።
የተያዘበትም ሁኔታ ለትግል ጓዶች መታውቂያ በመስጠት የሚተባበር ቢሮከራሲዉ ዉስጥ የሚሰራ ዴሞክራት ከቀጠሯቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በመያዙ በሱ መሪነት ተስፋዬ በቀጠሮዉ ቦታ ተገኝቶ ሲጠብቀዉ ነበር ከበባ ያደረጉበት። በዚህ ከበባም ጊዜ የብዙ ጓዶች ፎቶ በእጁ ላይ ስለነበረ ከዚያ ሁሉ ፎቶ ጋር እጅ መስጠት እንኳን ለቆራጡ ተስፋዬ ቀርቶ ለማንም ቢሆን የማይታሰብ አልነበረም።
በዚህ ከበባ ጊዜም ተስፋዬ የጓዶቹን ፎቶና ዶኩመንቶችን እንደያዘ እጁን ላለማስጠት ተጠግቶ መሳሪያ የደገነበትን ግለሰብ ከነመሳሪያው መትቶ በመዘረር እየሮጠ ፎቶዎቹንና ዶኩመንቶቹን በመቅደድና በማጥፋት ከመርማሪዎች እጅ እንዳይገባ በማድረግ ብዙ ከሮጠ በኋላ ዙሪያው በሙሉ በመከበቡ በድብቅ ይዞት የነበረውን የመስዋእትነት ክኒን (suicidal pill)በመዋጥ የመጨረሻዉን የሞት ፅዋ ለመጠጣት የወሰደው እርምጃ ባለመሳካቱ በጨካኞች እጅ ሊወድቅ በቃ።
ይህንን ቆራጥ እርምጃ ሲወስድ የተመለከቱት ከባቢዎቹ ትልቅ አሳ እንዳጠመዱ ገብቷቸው፤ ብዙ የሚፈልጉትን ምስጢር ይዞ እንዳይሰዋ አንገቱን አንቀው በ አቅራቢያዉ ከነበረዉ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማስገባት ነፍስ እንዲዘራ አደረጉ። ሁኔታውም ትንሸ ሲሻሻልም ወደ ማእከላዊ ምርመራ እስር ቤት (torture chamber) በመዉስድ አስከፊ ግብረ ስዬልና ምርመራ ቢፈፅሙበትም ተስፋዬ ለአላማዉ ፍንክች የማይል ከብረት የጠነክረ ዲሲፕሊን ያለው በመሆኑ አካሉን በመጉዳት ቀደም ብሎ በመኪና አደጋ የተጎዳ እግሩን በመስበር የቻሉትን ሁሉ ግፍና ስቃይ ፈፅመዉበታል።
በመቀጠልም በ ከፍተኛ 19 እስር ቤት ከሌሎች ብዙ ጓዶች ጋር እንዲታሰር ሆኗል። እዚያ በነበረበት ጊዜም ከብዙ ቆራጥና ጠንካራ የትግል ጓዶች ጋር ለመገናኘት አድል አጋጥሞት ነበር። በዚሁ እስር ላይ እያለም ነበር ከ ሻሸመኔ የተያዙት እነ ህይወት ተፈራና በአንድ ላይ የተያዙት የሻሸመኔው ግሩፕ ጋር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ለመገናኘት እድል ያጋጠመው።
በዚህ እስር ቤት ዉስጥ በነበረበት ጊዜም ነበር ቀደም ሲል በትግል ጓድነት የተለያዩ ተልእኮዎች ላይ አብሮት የተሳተፈዉ ጓዱ አሁን ግን በመስመር በመለያየታቸው ምክንያት አንጃ ሆኖ ከደርግ ጋር አብሮ በመስራት ላይ ያለ ግለሰብ ተስፋዬን ያገኘው። ይሀንንም ሁኔታ አብረው በእስር ላይ ከነበሩት ግለሰቦች ለመረዳት እንደተቻለዉ ተስፋዬን ሲያገኘዉ የፈነደቀበትን ሁኔታ ሲገልጹት ተስፋዬን ያዝን ማለት የኢሕአፓ ቀንደኛ አናርኪስት አንድም አላመለጠንም ማለት ነዉ በማለት እንደገለጸዉ ነዉ የተናገሩት።
በእስር ከተያዘ ከአመት በላይ ጊዜ በዚሁ ከፍተኛ እስር ላይ ቢቆይም በመጨረሻ የሞት ብያኔ በመወሰን ከሌሎች ጓዶች ጋር በመግደል አስከሬኑን መንገድ ላይ በመጣል አረመኒያዊና ጭካኔ የተመላበትን የሞት ፅዋ በፀጋ የተቀበለዉ።
በአሟሟቱ ጊዜ የተከሰቱትን ሁኔታዎች በእስር ላይ አብረዉት ከነበሩት ጓዶች ለመረዳት እንደተቻለው ለመግደል በሚወስዱበት ጊዜ ለብሶት የነበረዉን የስራ ቱታ የሚመስል ልብስ እንዲያወልቅና ሌላ ልብስ እንዲቀይር ቢያስገድዱትም እንቢተኛነቱን አሳይቷል። ልብሱን እንዲቀይር የፈለጉበትም ምክንያት አካባቢዉ ንፋስ ስልክ በመሆኑና አካባቢዉም የፋብሪካ አካባቢ በመሆኑ የፋቢሪካ ሰራተኛ እንዳይመስል እንደሆነ በጊዜው አካባቢዉ ላይ የነበሩት ሰዎች ተናግረዋል።
በመጨረሻም ምንም አይነት ድብደባና ስቃይ ቢፈፀምበትም ቱታዉን አላወልቅም በማለቱ ከነቱታው ለመግደል ሲወስዱት “ልጓዝ በድል ጎዳና! በወደቁት ጓዶች ፋና! ፍፁም ነው እምነቴ! የትግሉ ነው ሕይወቴን እየዘመረ ወደማይቀርበት የመጨረሻዉን የሞት ፅዋ በክብር ጠጥቷል።
ከሁለም በላይ ደግሞ የእረፍቱ ዜና በቤተሰብ በኩል እንደተሰማ ቤተሰብና ጎረቤት እርማቸዉን ለማዉጣት ተሰብስበዉ በሚላቀሱበት ጊዜ የታሰረበት ከፍተኛ ካድሬዎች መኖሪያ ቤቱ ድረስ በመሄድ በ ቤተሰቡና በአካባቢዉ ሕብረተሰብ ላይ ያደረጉት ድብደባና የለቅሶዉን ስነስርዓት ለመበተን ያደረጉት የጭካኔ ድርጊትና በአካባቢዉ የተገኙትን ወጣቶች ለይ ያደረሱትም እስር የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ሁኔታ ነዉ።
ክብር የህዝብን ጥያቄ አንግቦ ግንባሩን ለጥይት ለሰጠ ጀግና ትውልድ!!
ለህግ የበላይነት፤ ለሰላም ለዴሞክራሲና ለ እኩልነት..
ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት!!!
የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!