22 March 2020
በኬንያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ግጭትና የፖለቲካ ውጥረት ሥጋት ያደረበት የአውሮፓ ኅብረት፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና እንድትወጣ ጠየቀ።
የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ በኬንያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ እንዳሳሰበው ይፋ አድርጓል። በሶማሊያ ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ጁባላንድ የጦር ኃይልና በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የጦር ኃይል መካከል የተፈጠረው ግጭት ወደ ተባባሰ ጦርነት በመሸጋገር፣ የጁባላንድ ወሰንን አልፎ ማንዴራ ወደተባለችው የኬንያ የድንበር ከተማ መዝለቁን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የጁባላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር የአልሸባብ መጠለያ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትን ለማዳከም በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ የፕሬዚዳንት ፋርማጆ አስተዳደር ይከሳል። የኬንያ መንግሥትም ለጁባላንድ አስተዳደር ፖለቲካዊና ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ፋርማጆ ወቀሳ ያቀርባሉ።
የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የሶማሊያ አቻቸው ፋርማጆ በችግሩ ላይ ተገናኝተው ለመነጋገር ባለፈው ሳምንት ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ ባልተገለጸ ምክንያት ሳይገናኙ መቅረታቸውን ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የሶማሊያ መንግሥት እንዲኖር ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን የሚገልጹ የዲፕሎማቲክ ምንጮች፣ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አቋምና ጠንካራ ፍላጎት ያለው የሶማሊያ መንግሥት በጁባላንድ ያለውን የአልሸባብ እንቅስቃሴ ለማጥፋት የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከጁባላንድ ግዛት የጦር ኃይል ጥቃት እንደተከፈተበት ገልጸዋል።
ይህንን ጥቃት ለመመከትና አልሸባብን ለመቆጣጠር የሶማሊያ መንግሥት የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ፣ ከኬንያ መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ እንደከተተው ገልጸዋል። የኬንያ መንግሥት አልሸባብ ከሶማሊያ ወደ ኬንያ እንዳይገባ የቀየሰው ስትራቴጂ የኬንያ ጎረቤት የሆነችውን የጁባላንድ አስተዳደር መደገፍና ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከር እንደሆነ፣ ይህም በኬንያና በሶማሊያ መካከል ውጥረት እንዲነግስ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በዚህ አካባቢ እንደማይገኝ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸው፣ በኢትዮጵያዊው ሌተና ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ጦር ግን ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ጋር በመሆን በተለያዩ የሶማሊያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀስ የአልሸባብ የሽብር ቡድን እየደመሰሰ መሆኑን አስረድተዋል።
ጀናል የተባለውን የሶማሊያ ከተማ የተቆጣጠረውን የአልሸባብ ቡድን ለመደምሰስ የአሜሪካ አየር ኃይል ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከአሥር በላይ የአየር ጥቃቶችን መሰንዘሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ የአየር ጥቃት የተወሰኑ የአልሸባብ አባላት ቢገደሉም፣ የተፈለገውን ውጤት እንዳላመጣና ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ እንዳደረገ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ነገር ግን በሌተና ጄኔራል ጥጋቡ የሚመራው የአፍሪካ ኅብረትና የሶማሊያ መንግሥት እግረኛ ጦር በዚች ከተማ በመሰማራቱ፣ አልሸባብ ሙሉ በሙሉ ባለፈው ሳምንት ተወግዶ ከተማዋን የአፍሪካ ኅብረትና የሶማሊያ መንግሥት ጦሮች እንደተቆጣጠሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
የአውሮፓ ኅብረት ግን አልሸባብን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ቅንጅት ከሌለው ውጤቱ ዘላቂ እንደማይሆን፣ በተለይም በጁባላንድ አካባቢ ያለው ውጥረት ባለመርገቡ በተለያዩ አካባቢዎች የተመታው የአልሸባብ ቡድን ወደ ጁባላንድ መሸሹንና በዚያ ያለው ሁኔታም ለመሸሸግ ምቹ እንደሆነለት ገልጿል።
ይህ ሁኔታ በኬንያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ሥጋት የፈጠረ በመሆኑና በውይይት ካልተፈታም በሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል ያለው ግንኙነት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በአካባቢው ሌላ ችግር ሊወልድ የሚችል ስለሆነ ኢትዮጵያ የበኩሏን እንድትወጣ ጠይቋል።
ተመሳሳይ ጥያቄም ከኬንያ መንግሥት በኩል መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ በተለይም በሶማሊያ የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛ አጋር ሆና ብትቆይም፣ ሥልጣን ላይ ያለው የአሜሪካ መንግሥት ግን ከዓመት በፊት በወሰደው የፖሊሲ ለውጥ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ጥምረት ዝቅ በማድረግ ኬንያን የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ አጋሩ ማድረጉ ይታወሳል።
ሪፖርተር