
SourceURL:https://www.ethiopianreporter.com/article/18380 የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) እውነታዎች | ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) እውነታዎች
18 March 2020 ምሕረት ሞገስ
ኮሮና ኖቭል ቫይረስ (ኮቪድ 19) በዓለም ደረጃ 175,000 የሚጠጉ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 77,000 ያህሉ ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን፣ 6,526 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል፡፡ በቫይረሱ ከተጠቃው አንጻር የሞቱ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ የቫይረሱ ሥርጭትም ሆነ የሞቱ ቁጥር የተመዘገበበት ፍጥነት ሰዎች እንዲደነግጡ አድርጓል፡፡ በበርካታ አገሮች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ስፖርትና ታላላቅ ስብሰባዎች እንዳይከናወኑ የየአገሮች መንግሥታት ወስነዋል፡፡ የሞት ፍጥነቱ አስደንጋጭ በሆነባት ጣሊያን ደግሞ ሰዎች ቤታቸው እንዲቀመጡ ታውጇል፡፡ ወረርሽኝ ብሎ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጀው ኮሮና ኖቭል ቫይረስ፣ በሳይንሱ ረገድ ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና ክትትል ካገኙ ከ95 በመቶ በላይ ሊድኑ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ሲያሳይ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ባህላዊ የጉንፋን መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም በሽታውን መከላከል ይቻላል የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ ከማንኛውም ነገር ንክኪ በፊትና በኋላ እጅን በሳሙናና ውኃ መታጠብ፣ አለመጨባበጥና ፊትን ንጹህ ባልሆነ እጅ ባለመንካት ቫይረሱን መቆጣጠር እንደሚቻልም በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ በሽታው እንደጀመረ ሰሞን ሳይንሱ በቅጡ ያልተነተነውና ብዙዎችንም ለጭንቀት የዳረገው ኮሮና፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ትንታኔዎች ይሰጡበታል፡፡ የተሳሳተም ይሁን እውነተኛ መረጃዎች ተደበላልቀው በመስጠታቸው ጭንቅ የገባው ማኅበረሰብ፣ የተገኘውን ማምለጫ ሁሉ ከመጠቀም አይቦዝንም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ኮሮና ኖቭል ቫይረስ ምን ማለት እንደሆነና እንዴት መከላከል እንደሚቻል በድረ ገጹ በጥያቄና መልስ መልክ አስፍሯል፡፡ ምሕረት ሞገስ እንደሚከተለው አቅርባዋለች፡፡
ጥያቄ፡- ኮሮና ቫይረስ ምንድነው?
መልስ፡- ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው፡፡ ለምሳሌ ሚድል ኢስት ሪስፓራይቶሪ ሲንድሮም (ኤምኢአርኤስ) እና ሲቪየር አኪዩት ሪስፖራይቶሪ ሲንድሮም (ኤስኤአርኤስ) በከፍተኛ ደረጃ የመተንፈሻ አካላት በሽታን የሚያስከትሉና ለሞት የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ ደግሞ ሞትንም ጭምር የሚያስከትለው ኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ተከስቷል፡፡
ጥያቄ፡- ኮቪድ 19 ምንድነው?
መልስ፡- ኢንፌክሽን የሚያስከትል የመተንፈሻ አካል በሽታ ሲሆን፣ ይህም በቅርቡ የተገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ነው፡፡ ይህ ቫይረስና በሽታ እ.ኤ.አ. በታኅሣሥ 2019 በቻይና ውሃን ከተማ ከመከሰቱ አስቀድሞ አይታወቅም ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የኮቪድ 19 ምልክቶች ምንድናቸው?
መልስ፡- የተለመዱት የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ድካምና ደረቅ ሳል ናቸው፡፡ አንዳንድ ሕመምተኞች ራስ ምታትና የሰውነት ሕመም፣ የጉሮሮ ሕመም፣ ተቅማጥ፣ ንፍጥና የአፍንጫ መጠቅጠቅ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች በትንሹ ጀምረው ቀስ በቀስ የሚጎለብቱ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ኢንፌክሽኑ ይዟቸው ምንም ዓይነት ምልክትም ሆነ ሕመም ላያሳዩ ይችላሉ፡፡ 80 በመቶ ያህሉ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ምንም የተለየ ክብካቤ ሳይደረግላቸው ከሕመማቸው የሚያገግሙ ናቸው፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ስድስት ሰዎች አንዱ በፅኑ የሚታመምና ለመተንፈስም የሚቸገር ነው፡፡ አዛውንቶችና የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም፣ ስኳርና ሌሎች የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ክፉኛ ሊታመሙ ይችላሉ፡፡ ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር የገጠማቸው ሰዎች ወደ ሕክምና መሄድ አለባቸው፡፡
ጥያቄ፡- ኮቪድ 19 እንዴት ይስፋፋል?
መልስ፡- በሽታው በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ወደ ጤነኞቹ በቀላሉ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በሽታው ከሕመምተኛው አፍንጫ ወይም አፍ በሚወጣ ጥቂት ፈሳሽ አማካይነት የሚተላለፍ ነው፡፡ ኮቪድ 19 ያለበት ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲተነፍስ ወደ ሌሎች ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ከሕሙማን የሚወጣ ፈሳሽ ያረፈበትን ቦታ የነኩ ሰዎች በበሽታው በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን አለበት የተባለውም በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ኮቪድ 19 በአየር ውስጥ ይተላለፋል?
መልስ፡- እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቫይረሱ በአየር ውስጥ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከወጡ ፍሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡
ጥያቄ፡- የኮቪድ 19 ቫይረስ ኖሮባቸው ምልክት ካላሳዩ ሰዎች በሽታው ይተላለፋል?
መልስ፡- የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን ባለው ጥናት መሠረት ዋናው የበሽታው መተላለፊያ ከታማሚ መተንፈሻ አካል ከወጣ ፈሳሽ ጋር የሚኖር ንክኪ ነው፡፡ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ወደ ሌለባቸው የመተላለፍ አደጋው በጣም አናሳ ነው፡፡ አብዛኞቹ የቫይረሱ ተጠቂዎችም በጣም ዝቅተኛ ምልክት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህ ምልክት በሽታው ገና እንደጀመረ የሚታይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ሊተላለፍበት የሚችል አጋጣሚ አለ፡፡
ጥያቄ፡- ቫይረሱ በሰገራ ምክንያት ይተላለፋል?
መልስ፡- በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው በሚወጣ ሰገራ አማካይነት በሕመም የመያዝ ዕድሉ አናሳ ቢሆንም፣ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የተደረጉ ምርመራዎች በአንዳንድ ሁኔታዎች ቫይረሱ በሰገራ ውስጥ እንደሚኖር አመላክተዋል፡፡ የቫይረሱ ዋና ባህሪ በዚህ መንገድ መተላለፉ ሳይሆን፣ በመተንፈሻ አካል መሆኑ ከመተንፈሻ አካላት ለሚመጡ ፍሳሾች ትኩረት እንዲሰጥ አደረገ እንጂ፣ ቫይረሱ በሰገራ ውስጥም ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው የተጠናከሩ ጥናቶች እየተሠሩና ሰዎችም መፀዳጃ ቤት በገቡ ቁጥርና ሊመገቡ ሲሉ እጃቸውን በውኃና በሳሙና እንዲታጠቡ የሚመከረው፡፡
ጥያቄ፡- ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድል አለኝ?
መልስ፡- የመጋለጥ ዕድል ሰዎች እንዳሉበት ሁኔታ ይወሰናል፡፡ ለብዙዎች በቫይረሱ የመያዝ ዕድል ዝቅተኛ ነው፡፡ ሆኖም በዓለም ቫይረሱ እየተሠራጨባቸው ያሉ ከተሞች አሉ፡፡ በከተሞች የሚኖሩ ወይም ከተሞችን የሚጎበኙ ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥትም አዲስ የቫይረሱ ተጠቂ በተገኘ ቁጥር ዕርምጃ እየወሰዱና መሰብሰብን እያገዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም በጤና ሚኒስቴርና በመንግሥት የሚሰጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር መተባበር አለበት፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ሊውልና ሥርጭቱም ሊቆም የሚችል ነው፡፡ ይህ በቻይና ታይቷል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ደግሞ አዳዲስ ወረርሽኝ በፍጥነት እየተከተሰ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ስለኮቪድ 19 መጨነቅ አለብኝ?
መልስ፡- ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሕመም ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይ ሕፃናትና ወጣቶች ብዙ አይጎዱም፡፡ ሆኖም ከአምስት ሰዎች አንዱ የሆስፒታል ሕክምና ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ ኮቪድ 19 የሚወዱትን ሲያጠቃና ወረርሽኝ ሲሆን መጨነቅ የሰው ባህሪ ነው፡፡ መጨነቁን ግን በሽታውን ለመከላከልና ሌሎችን ለመጠበቅ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ማጀብ አለብን፡፡ መከላከያው መደበኛ የግልና አካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ነው፡፡ ከጤና ባለሙያዎች የሚመከረውን መስማትና መተግበርም ያስፈልጋል፡፡
ጥያቄ፡- ፀረ ተዋህስያን (አንቲባዮቲክ) ኮቪድ 19 ለማከም ይረዳሉ?
መልስ፡- አይረዱም፡፡ አንቲባዮቲክ ቫይረስን ለማከም አይረዳም፡፡ በአንቲባዮቲክ የሚታከመው በባክቴሪያ አማካይነት የሚመጣ ኢንፌክሽን ብቻ ነው፡፡ ኮቪድ 19 ደግሞ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ለማከም ስለማያገለግሉም፣ ሰዎች በሐኪም ያልታዘዘላቸውን መድኃኒት ከመጠቀም መቆጠብ አለባቸው፡፡
ጥያቄ፡- ለኮቪድ 19 መድኃኒት ወይም የእንክብካቤ ዓይነት አለ?
መልስ፡- ምዕራባዊ፣ ባህላዊ ወይም ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ባህላዊ መድኃኒቶች የኮቪድ 19 ምልክቶችን የሚያጠፉና ከሕመም ነፃ በማድረግ ሰላም የሚሰጡ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለው ሳይንሳዊ ጥናት በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው በሽታውን የሚቆጣጠርና የሚያድን መድኃኒት አልተገኘም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም ሰዎች በማንኛውም መድኃኒት ራስን ከማከም እንዲቆጠቡ፣ ፀረ ተህዋስያን እንዳይወስዱ ይመክራል፡፡ አሁን ላይ ምዕራባዊውም ሆነ ባህላዊው መድኃኒት ቫይረሱን ለመቆጣጠርም ሆነ ለማዳን ይችል እንደሆነ ክሊኒካል ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ክትባት አለው?
መልስ፡- እስካሁን ክትባት አልተገኘም፡፡ መድኃኒትም የለውም፡፡ ሆኖም በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ሆስፒታል በማስገባትና በቫይረሱ ምክንያት የሚመጡ ተጓዳኝ ሕመሞችን ማከም ተችሏል፡፡ አብዛኞቹም ድነው ከቤተሰባቸው ተቀላቅለዋል፡፡
ጥያቄ፡- ከቫይረሱ ለመጠበቅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) መጠቀም አለብኝ?
መልስ፡- በሽታው ካለብህ ወይም የታመመ የምታስታምም ከሆነ ተጠቀም፡፡ የታመመ በሌለበት ማስክ መጠቀም ሀብት ማባከን ነው፡፡ ሆኖም ሰው በተፋፈገበት ቦታ መጠቀሙ ጉዳት የለውም፡፡
ጥያቄ፡- ከቤት እንስሳት ኮቪድ 19 ሊይዘኝ ይችላል?
መልስ፡- በሆንግኮንግ አንድ ውሻ በቫይረሱ ተይዞ ከመገኘቱ ውጪ በውሻ፣ ድመትና ሌሎች የድመት ቤተሰቦች ላይ ቫይረሱ ስለመተላለፉ አልተረጋገጠም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው በሚወጣ ፈሳሽ ንክኪ ጋር ይተላለፋል፡፡
ጥያቄ፡- ቫይረሱ ከሰው ከመጣ በኋላ ባረፈበት ቦታ ላይ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?
መልስ፡- እንደ ቦታው አየር ፀባይ፣ ዓይነትና ወበቅ ባለባቸው ቦታዎች ላይ የቫይረሱ የቆይታ ጊዜ ይለያያል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ከታማሚው ከወጣ በኋላ ከጥቂት ሰዓታት እስከ ቀናት ሊቆይ ስለሚችል የግልና አካባቢን ንፅሕና መጠበቅ ዓይነተኛ መከላከያው ነው፡፡
ጥያቄ፡- ኮቪድ 19 ካለባቸው ሥፍራዎች ታሽገው የተላኩ ዕቃዎችን መቀበል እችላለሁ?