ታጠቅ መ. ዙርጋ

27 March 2020

አግኝቼ ባላነብም ስለዚህ ጦርነት የተጻፈ ወይም የተጻፉ መጽሃፍ/ት ሊኖር/ኖሩ ይችላል/ሉ ። መንግሥቱ ወደ ዝንቧቤ ከመኮበለሉ በፊት የተጻፈ/ፉ ከሆነ/ኑ ታአማኒነት ያለው/ቸው መረጃ አይሆንም/ኑም። ጦርነቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ በውስጡ ባለፈ/ች ፣ርዕዮታዊና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በሌለው/ላት፤ ነገር ግን መንግሥቱ ወደ ዝንቧቤ ከፈረጠጠ በኋላ በሃቀኛ ኢትዮጵያዊ/ት ስለጦርነቱ የተጻፈ መፀሃፍ ይኖር ይሆን?አለ የምትሉ ካላችሁ እባካችሁ ጠቁሙኝ።

ከላይ ከተጠቀስው ክብረ በዓል ጋር በተዛመደ የፋሽስቱ መንግሥቱ ሃ/ማርያም ክህሎት ወደ አጼ ቴድርስም ፣ ወደ ኣጼ ምኒሊክም ለማስጠጋት የሞከሩ ሰዎች እንዳሉ ታዝቤያለሁ ።

እየሱስ በእስራኤል ምድር በነበረበት ዘመን ፣ ስዎች እውሸቱን እውነት፣ እውነቱን እውሸት እያሉ ሲዋሹና ሲዘላብዱ ሲሰማ ‘እውነቱን እውነት፣እውሸቱን እውሸት በሉ’ እያለ አስተምሯል።‘ጀግናው መንግሥቱ! አገር ወዳዱ! ዳርድንበሩ ያላስደፈረው! ሉዓላዊነታችን ያስጠበቀው !’ ወዘተርፈ ተብሎለታል። ፍጹም ዓይን የጠነቆለ ውሸት። የፋሽስቱ መንግሥቱ ግዙፍ ጥፋቶቹ፣ድክመቶቹና ጸረሕዝብነቱ ከዚህ ቀደም በዝርዝር ፣ስለሄድኩበት ያንንኑ መድገሙን ትቼ ባጭሩ፦አስብን፣ ምጽዋና ኤርትራን በሻቤያ የተወሰዱት ገና ወደ ዚምቧቤ ከመኮብለሉ በፊት አልነበረምን/አይደለምን?

ፋስሽስቱ መንግሥቱ ለኢትዮሱማሊ ጦርነት ጠብ አጫሪ ባይሆንም ጦርነቱ ይፈልገው ነበር። ማን፣ እነማን፣የትና መቼ ወደተሰኙ ዝርዝር ወስጥ መግባቱን ወደጎን ትቼ ፣ ከታሪክ እንደተማርነው፣ የበርካታ አገራት ፋሽስቶችና አምባገነን ገዥዮች የውስጥ ተቀናቃኞቻቸውን ፤ለመምታት፣ ለማዳከምና ለማጥፋት ድንበር ጥሶ የሚመጣ ጦርነት ይፈልጋሉ ወይም ሰበብ አስባብ ፈልገው ጦርነት ይቀሰቅሳሉ። መንግሥቱ ጦርነቱ ኢ...ፓዎችን ለመምታት ተጠቅሞበታል።

በወቅቱ በሞያዬ የትምህርት ምኒስተር ሠራተኛ ሆኜ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ነበርኩኝ። ከጦርነቱ በኋላ አንዳንድ የምዛመዳቸውና ሌሎች በጓደኝነት የምቀርባቸው ወታደራዊ መኮነኖች – “የሱማሊ ወራሪ ጦር እስከ ድሬዳዋ መድረስ የሚችል አቅም አልነበረውም ፣ኦጋዴ ላይ ልናቆመው እንችል ነበር፣ ደጋግመን መሳሪያ አቀብሉን ብለን ስንጮህ ወደኋላ አፈግፍጉ የሚል ትእዛዝ ይሰጠን ነበር፣ ሆን ተብሎ ነው ጦርነቱ እስከድሬዳዋ እንዲዘልቅ የተፈለገው” በማለት በጣም ጥንቃቄ ባለው ሚስጥር አጫውተውኛል።

እነዚያ መኮነኖች ስለአጫውቱኝ ሚስጥር ላይ ተጠራጣሪ(sceptic) ስለነበርኩ የነገሩኝን በትንሹም ቢሆን ፈታትቼ <deconstruct> አድርጌ ለማየት ተገደድኩ ። ስለሆነም ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲከፍት በራሱ ተዋጊ ሠራዊት ብቻ ኢትዮጵያን አሸንፋለሁ በማለት ነበርን? አይመስለኝም። ታዲያ ማንን በተማመን ነበር አገራችንን የደፈረው? ኪዩባና ረሺያ ። እነዚህ ሁለቱ አገራት ከዚያድ ባሬ ጋር ብዙም ሳይቆዩ ፈታቸው ወደ ኢትዮጵያ አላዞሩምን? ታዲያ የዚያድ ባሬ ተዋጊ ሃይል ራሱን ችሎ ኦጋዴን አልፎ ወደ ሃረረና ድሬዳዋ የመዘለቅ አቅም ነበረውን?

ከፊሉ ዕድገቴና ከፊሉ የትምህርት ዘመኔ ያሳለፍኩት አዲስ አበባ ነው ። በመሆኑም አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ነገር ቶሎ የሚገባቸውና ቶሎ የሚዘይዱ ወይም ‘ያራዳ ልጅ አራዳ’ የሚባሉ ጓደኞች ነበሩኝ። አንድ ሰው በሆነ ነገር ሊያታልለን ሲምክር ወይም የማይመስል ሃሳብ ሲያቀርብ ፤ “እኛ እንኳን ይህንን የዝንብ ጠንጋራ እናውቃለን” ይሉ ነበር።

ከመንግሥቱ ፋሽስታዊ ባሪ፣ መሰሪነት፣ ከነበረው የጋለ የሥልጣን ጉጉት (ultra power ego) እና ከላይ ካስቀመጥኳቸው አመክኖታዊ/ሎጂካዊ መላምት አንጻር መኮነኖቹን የነገሩኝን ሚስጥር ጭብጥነት እንዳለው አመንኩ። ማለት የዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር እስከ ድሬዳዋ እንዲደርስ የተደረገው ታቅዶና ተፈልጎ እንጂ ከአቅም በላይ ሆኖ አልነበረም/አይደለም ።

እዚህ ጋ ከጉጉል ባገኘሁት የቀን ስሌት ነው የተጠቀምኩት። እ..አ ከ(12 July 1977 -15 March 1978) የተደረገው የኢትዮሶማሊ ጦርነት ስምንት ወራት ከሁለት ቀኖች ነበር የወሰደው ። የወራሪዩ ጦር ድሬዳዋን የከበበው እ..አ ማርች 5/1978 ነበር። ምሊሺያው ጦር ከዚያ አንድ ቀን አስቀድሞ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ለሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አደሮ ማርች አራት ጠዋት ድሬዳዋ ደረሰ ።

ምሊሺያው በቂ ዕረፍት ሳያገኝ ፣ አካባቢዩውን በደንብ ሳያውቅና በቅጡ ሳይመሽግ በዚያው ዕለት ማታ ፤ ወራሪዩ ጦር ድሬዳዋን ከቦ መደብደብ ስለጀመረ ምሊሺያው ወደ ጦር ግንባር ተሰማራ ።

ምሊሺያዎቹ ከአውቶቢስ ወርደው በከተማው ሲዘዋወሩ ላይዋቸው ፤ ስብዕናና የወገን ፍቅር ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እጅግ በጣም የሚያሳዝኑ ነበሩ። የወታደር አልባሳት ይልበሱ እንጂ አብዛኞቹ በግብርና ሥራ የተጎዳ ሰውነት የነበራቸው ፣ ፈጠን ብሎ የመራመድም ሆነ የመሮጥ አቅም ያልነበራቸው ጎስቋሎች ነበሩ ።

ያንን ያዩና በብሄራዊ ስሜት የታነጹ፣ የነቁና የተደራጁ ወጣት ኢ ሕ አ ፓዎች (ኢ ሕ አ ፓነታቸው ሳይገልጹ) የድሬዳዋ ከተማ ወጣቶችን በመቀስቀስ ከምሊሺያዎች ጎን ለመሆን ጦርነት ወደ ሚደረግበት ግንባር (ድሬዳዋ ከተማ ወደ ከበበው) ጠላት አመሩ። የሞቱትና የቆሰሉትን ምሊሺያዎች በማንሳት፣ ቆስለው በወደቁበት ውሃ የፈልጉ ውሃ በማጠጣት ፣ ጠመ ንጃቸውን ተረክበው ጠላት በማጥቃት ወዘተርፈ ተሳትፎዋል ፤ የሞቱም አሉ። በዚያ ጦርነት ምሊሺያው እንደ ቅጠል ረገፈ።

ከዚያ ይሁንታ በተጻራሪ ፋሽስቱ መንግሥቱ እና ካድሬዎቹ መኢሶኖች ገና ጦርነቱ ሲጀመር ጀምሮ ፣ ኢ ሕ አ ፓ ዎች የዚያድ ባሬ ወረራ ደግፏል፣ከዚያድ ባሬ ጦር ጋር ተሰልፈው ኢትዮጵያን እየወጉ ነው ፤ እያሉ የፕሮፓጋንዳ ጽሁፎች በኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች በትኗል/አስራጭቷል። ልጆቻችሁ ከባዕድ ጋር ተሰልፈው አገራቸውን እየወጉ ነው በማለት ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋና ግዲያ አሚን ብለው እንዲቀበሉ የታቀደ ዘዴ ነበር።

በጦቢያ መድረክ ላይ ‘በፍራሽ አዳሽ’ የትወና ስም የሚተውነው ወጣት በጠጅ አስመስሎ “የሚቀርብልህን ሳይሆን የሚጣድልህን አስተውል” እንዳለው ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን የፋሽስቱ መንግሥቱ ካድሬዎቹን ያወሩለትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ማስተጋባት እንጂ፤ በዚያ ጦርነት ስም ምን ግፍ እንደተፈጸመ አያውቁም። እንዴት ? ለምን? መቼ? የት? ብለው በመጠየቅ እውነቱን ለማወቅ አይሞክሩም ።