እነዚህ የማይበሉ እንስሳትን የሚበሉ ሰዎች የሚያመጡብን ጣጣ ገና ገና ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን አይቀርም፡፡ ኮሮና ብትሉት፣ ኢቦላ ብትሉት፣ ቀደም ሲል ደግሞ ሐምሳ ሚሊዮን የዓለምን ሕዝብ የፈጀው እስፓኒሽ ፍሉ በሀገራችን የኅዳር በሽታ የተባለው ወዘተረፈ. ሁሉም ወረርሽኞች የተከሰቱት የማይበሉ እንስሳትን በመመገብ ምክንያት ነው!!!

በሀገራችን 1918 ... ሰው የፈጀው የኅዳር በሽታ የተባለው ስፓኒሽ ፍሉ የኅዳር በሽታ ከመባሉ በፊት የፈረንጅ በሽታ ነበር ተብሎ የነበረው፡፡ መጀመሪያ እዚህ ይኖሩ የነበሩ ፈረንጆችን ስለነበረ የፈጃቸው በዚህ ምክንያት ነው የፈረንጅ በሽታ ተብሎ የነበረው፡፡ ባይገባን ነው እንጅ እግዚአብሔር በኦሪቱ ሕግ የሚበሉና የማይበሉ (ዘዳ. 143-8) ብሎ ለይቶ የተናገረበት ምክንያት እኮ ብንመገባቸው እንዲህ ጤና የማይሰጡ በመሆናቸው ነው እንጅ እኛን ተመቅኝቶን አልነበረም እኮ፡፡ የጤና ጠንቅ መሆናቸው ብቻ አይደለም ብዙ ጣጣ አለባቸው፡፡ ዓለም ታዲያ መቸ ይሄን ይረዳል!!!

ፈረንጆቹ የራሳቸውን አሳማ እየበሉ ያመጡትን ስፓኒሽ ፍሉ በሽታ ደብቀው ዛሬ ምዕራብ አፍሪካን ችምፓዚና ጦጣ እየበላቹህ፣ ቻይኖቹን ደግሞ ሕፃን ይመስል ያገኙትን ሁሉ ወደ አፋቸው እየከተቱ!” እያሉ ይነቅፋሉ፡፡ የሚያሳዝነው የእነሱ ጦስ ለእኛም መትረፉ ነው!!!

ምን አሁንማ እኛም እኮ እንደነሱ ምናምኑን ለቃቃሚ ሆነናል፡፡ ሠለጠንን ብለው አዲስ አበባ ባሉ የባዕዳን ሬስቶራንቶች ከባሕር የሚወጡ ለዓይን የሚቀፉ ጓጉንቸሩን፣ ቅንቡርሱን፣ ትላትሉን ሁሉ ጣፋጭ ዓሣ!” እያሉ ሲበሉ የሚውሉ ሐበሾች ቁጥር የትየለሌ አይደሉም እንዴ???

አርትስ የሚባል የወያኔዎች ቴሌቪዥን የዓለም ማዕድ!” በሚባለው የምግብ ዝግጅት ፕሮግራሙ የሚያሳያቸውን ዝግጅቶች አላያቹህም እንዴ??? እስከአሁን ድረስ የዚህ ዝግጅት አቅራቢዋ በእነኝህ የባዕዳን ሬስቶራንቶች እየዞረች ስትበላ ያላየኋት አይጥን ብቻ ይመስለኛል!!! በስተቀር አፈሩን ያስበላትና ያልበላችው ነገር የለም!!!

በነገራችን ላይ ሕግ አስፈጻሚ የለምና አርትስ ቴሌቪዥንን የሚከስ ሕግ አስፈጻሚ አካል የለም እንጅ እዚህ ሀገራችን ውስጥ በባሕላችን የምንጠየፋቸውንና ለምግብነት የማይውሉ ፍጥረቶችን ለምግብነት ማዋል በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን ወንጀል ነው ያስከስሳል!!! ይቅርና ይሄንን አጸያፊ ነገር ከራሳቸው አልፈው ሕዝቡም እንዲመገባቸው ለሕዝብ እያሳዩ መገፋፋት ይቅርና!!! ይሄኔ ስንቱ አስታውኮ ይሆን???

እናም ይሄ ቻይኖቹ እንኳን ለመመገብ ለማየት እንኳ የሚቀፉትን ፍጥረት ሁሉ በባሕር ውስጥም ይሁን በምድር ላይ ያገኙትን ሁሉ ሲጠርጉ ከሌሊት ወፍና ፓንጎሊን ከምትባል አዞ ከምትመስል እንስሳ ያመጡትን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አማጩ ቫይረስ ኮረና ዓለምን በከፍተኛ ጭንቅና ጥብ ላይ ከቷታል፡፡ በዚህ ምክንያት የዓለምን ኢኮኖሚ ከባድ ቀውስ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

እየታየና እየተወራ ያለው የዕለቱ ችግር ጉዳይ ሆኖ ልብ አልተባለም እንጅ ወይም ደግሞ ይሄ ችግር የሚፈጥረውን ቀውስ ማሰብ ስላልተፈለገ እንጅ አይደለምና ዓለም ለሳምንታትና ለወራት ቀጥ ብላ ቆማ ይቅርና የአንድና የሁለት ሀገር ኢኮኖሚ መናጋት በዓለም ላይ የሚያሳድረው የኢኮኖሚ ቀውስ ተደጋግሞ የታየ በመሆኑ የዚህ ተጽእኖ ምን ያህል ግዙፍ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ቀላል ይመስለኛል!!!

ዓለም እ... 1930ዎቹ the great depression ከተባለው የኢኮኖሚ ውድቀት በኋላ ይሄኛው ከባዱ የኢኮኖሚ ፈተና ይሆንባታል ብየ እገምታለሁ፡፡ ወደፊት የምታዩት ይሆናል ዓለማችን በዚህ ምክንያት ከሚደርስባት የኢኮኖሚ ቀውስ ለመውጣት በትንሹ ዐሥር ዓመት ይወስድባታል!!! በተለይም እንደ እኛ ያሉ ድሀ ሀገራት በከባዱ የሚጎዱ ይሆናሉ!!!

ወረርሽኙ ሀገራችን መግባቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ መጨባበጥን፣ ጥግግትን ከመተውና እጅን በተደጋጋሚ ከመታጠብ ጀምሮ እቤት እስከመቀመጥ የደረሰ የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ!!!

ይሁንና ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝቡ የሚጠበቀውን ያህል እየተገበረው አይደለም፡፡ መተግበርም የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከፊሉ እግዚአብሔር አለልኝ!” ባይ ነው፡፡ ጽኑ እምነት ኖሮት እንዲህ ቢል መልካም በነበረ፡፡ ነገር ግን በምግባሩ ብልሹ!” የምትሉት ሰው ሁሉ ነው እንዲህ የሚለው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ጽኑ እምነት ስላለው አይደለም ማለት ነው እንዲያ እያለ ያለው፡፡ ምክንያቱም ምግባር በሌለበት ቦታ ጽኑ እምነት አይገኝምና ነው፡፡ ምግባር የጽኑ እምነት ፍሬ ወይም መገለጫ ነውና!!!

ታዲያ ለምንድን ነው ሰዉ እንዲህ የሚለው?” ከተባለ እኔ የሚመስለኝ በዚህ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር በመጨነቅና በመጠበብ የሚያደርገውን አጥቶ በጭንቀት ማበድ ስለማይፈልግ አንዱ ምክንያት ሲሆን ሌላው ደግሞ ይሄንን ጣጣ በእግዚአብሔር ላይ ከመጣል ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ ስለሌለው ይመስለኛል፡፡ የአኗኗር ዘይቤያችንና ድህነታችንም ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ብየ አስባለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ እነኝህ የመከላከያ ዘዴዎች የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ!!!

ለምሳሌ እቤት ተቀመጡ አትውጡ!” የሚባለው መመሪያ ለምዕራቡ ዓለም እንጅ ለእኛ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም የምዕራቡ ዓለም ማኅበረሰብ ለሁለትና አራት ሳምንታት ብቻ አይደለም ለመንፈቅ አትውጣ ቢባል ምግቡን ወይም ቀለቡን ገዝቶ የመከተት አቅም ስላለው ሊያደርገው ይችላል፡፡ የእኛ ሕዝብ ግን በአብዛኛው ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑና ተሯሩጦ አዳሪ በመሆኑ ለሁለት ሳምንት አይደለም ለሁለት ቀን ከቤቱ ሳይወጣ ማሳለፍ አይችልም!!!

ምናልባት የገጠር ነዋሪው ሕዝባችን ግን ውጣም ቢሉት ከቤቱ ወጥቶ የሚያገኘው ሰው ስለማይኖር ማለትም ፈንጠር ፈንጠር ብሎ የሚኖር ስለሆነ ከቤት መውጣት ሥጋት ላይሆንበትና ቤቱን ዘግይቶ መቀመጥ ግድ ላይሆንበት ካልቻለ በስተቀር 80% ሕዝባችን ባለበት ገጠር ተፈጻሚ ማድረግ ይችላል ይሆናል፡፡ የከተማው ሕዝብ ግን ከላይ በገለጽኩት ምክንያት በረሃብ ሙተህ እለቅ!” ካልተባለ በስተቀር አይችልም!!! ከዚህ አንጻር ቤት የመቀመጡ ነገር የማይሳካ ከሆነ ተጋላጭነቱንና ተጠቂነቱን ማስቀረት አይቻልም ማለት ነው!!!

እጅ የመጨባበጡ ሰላምታ መቅረቱ መልካም ነው፡፡ ድሮም የእኛ ባሕል አይደለምና ከእነ አካቴው ብንተወው መልካም ነው፡፡ መጨባበጥ ብዙ ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች በቀላሉ ከአንዱ ወደሌላው የመተላለፊያ መንገድ ነው፡፡ ይህ የባዕዳን እጅ የመጨባበጥ የሰላምታ ባሕል ያለው በከተማው ሕዝባችን ዘንድ ነው፡፡ ያም ሆኖ እናት አባቶቻችን በአብዛኛው አያደርጉትም፡፡ የገጠሩ ሕዝባችን ግን ጨርሶ አያውቀውም ማለት ይቻላል፡፡ እንደጥንቱ እጅ በመነሣሣት ነው ሰላምታ የሚለዋወጠው!!!

ከገጠር ኗሪው ሕዝባችን ከእስልምና ተከታዮች በስተቀር እጅ ተጨባብጦ ሰላምታ የሚለዋወጥ ሰው የለም፡፡ እስላሞች ግን ተጨባብጠው ከተጨባበጡም በኋላ እጅ እጃቸውን ይሳሳማሉ፡፡ ባሕሉ የእስልምና ባሕል ይሁን ወይም ደግሞ የዓረብ ባሕል ለይቸ አላውቀውም፡፡ የእስልምና መሪዎች ይሄ የሰላምታ ባሕል በእስልምና የታዘዘ ካልሆነና ከዓረቦች የተወረሰ ባሕል ከሆነ ቢያስቀሩት መልካም ነው!!!

በተደጋጋሚ እጅ መታጠቡም መልካም ነው፡፡ በዚሁ ልማድ አድርገነው ብንቀር መልካም ነበር፡፡ አንድ የጤና ጥበቃ ሪፖርትን ስመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን ለብዙ ስቃይ የሚዳርጉ በሽታዎች በአብዛኛው በቀላሉ እጅ በመታጠብ ብቻ ልንከላከላቸው የምንችላቸው በሽታዎች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ከዚህ አንጻር እጅን ወጥተን በገባን ቁጥርና ከእቅስቃሴዎች በኋላ ሙልጭ አድርገን መታጠብን ባሕል አድርገን ብንይዘው ጤናችንን ለመጠበቅ ሁነኛ መላ አገኘን ማለት ነበር!!!

ሌላውና ዋናው ለትዝብት የዳረገን ጉዳይ በዚህ በሽታ ምክንያት የእያንዳችን እምነት ጽናት በእጅጉ የመፈተኑ ነገር ነው፡፡ ተፈትኗል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር እምነት ያለን የምናስመስለው ነገር ውሸት መሆኑን አጋልጦ አሳይቶታል፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ነው እውነተኛውን አማኝ ከሐሰተኛው ወይም እንደኔ ካለው አስመሳዩ የሚለየው፡፡ እምነት መቸም የልብ ሀብት ናት እንጅ እንደሱቅ ዕቃ ከሱቅ ገዝተው የራስ የሚያደርጉት ዕቃ አይደለምና ወይም በግድ በድርቅና አለኝ የሚሉት ነገር አይደለምና ከሃይማኖት አባት እስከ ምእመን ሁሉንም ትዝብት ላይ ጣለው፡፡

እንጅ ቅዱስ ቃሉ እንደሚናገረው እኛም እንደምንሰብከውና እንደምናወራው ቢሆንማ፦

ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ!” ማር. 1617-18

እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻቹሃለሁ፥ የሚጎዳችሁም ምንም የለም!” ሉቃ. 1019

“…ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይዎት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጎዳችውም፤ እነርሱም። ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ። ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ!” ሐዋ. 283-8

እያልን የእግዚአብሔርን ቃል እንደምንተርከው ሁሉ ለቃሉ ታምነንና ጸንተን እንደቃሉም ሆነን በተገኘን ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ቃለ እግዚአብሔር ወሬ ሆኖ ቀረ፡፡ ምላስና ልብ ተለያዩና እንደምናወራው ሳንሆን ስለቀረን፡፡ ከላይ እንዳልኳቹህ እምነት የልብ ሀብት ናት እንጅ የግዥ ዕቃ አይደለችምና ሁሉም ገንዘቡ ሊያደርጋት አልቻለምና፡፡ በዚህ ምክንያት አንድን ሰው ለምን እምነት ጎደለህ?” ማለት አይቻልም፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎች ቅዱሳን ከክፉ ሁሉ የሚጠበቅባት እምነት ከሌለችው ደግሞ ባለው ሥጋዊ ንቃተ ሕሊና ተጠቅሞ በመጠንቀቅ እራሱን ከክፉ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ምንም እንኳ አሁንም ማንም ሰው ከክፉ የሚጠበቀው በእግዚአብሔር ጥበቃ እንጅ በራሱ ጥንቃቄ ባይሆንም ቅሉ!!!

እግዚአብሔርም የሚያስብ ጭንቅላት ወይም አእምሮ የሰጠን እኮ ደጉን ከክፉው እየለየን እንድንራመድ፣ ከአደጋ እራሳችንን እንድንጠብቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ አቅሙ የፈቀደለትን ያህል እንዲህ እየተጠነቀቀ ይኖራል፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነው ነገር እግዚአብሔር እንዲጠብቀን እራሳችንን ለእሱ አደራ ሰጥተን ማለት ነው!!!

እንደ እውነቱ ከሆነ ልብ አልባ ነንና አይታወቀንም አናስተውለውም እንጅ የእግዚአብሔር ጥበቃ ባይኖረን ኖሮ ማንም ሰው ወጥቶ መግባት ባልቻለ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ጥበቃ ስላለን ነው ከምናውቀውና ከማናውቀው፣ ከሚታይና ከማይታይ ጠንቅ፣ አደጋና ክፉ ነገር ሁሉ ተጠብቀን ወጥተን የምንገባው፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጣብን ቅጣት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጥበቃ ባይኖርና እንደ ጠላታችን ሰይጣን ምኞት ቢሆንማ ኖሮ እስከአሁን ሰይጣን ድምጥማጣችንን አጥፍቶት በነበረ፡፡ ከአደጋ ከፈተና ለመጠበቅ የእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳይለየን እግዚአብሔርን አለማስቀየም ነው መፍትሔው!!!

እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ጥበቃ ለቅጽበት እንኳ ሳይለየን የዚህን ያህል ሆኖልን እያለ አሁን በዚህ ሰሞን ግን ይሄ የእግዚአብሔር ጥበቃ ጨርሶ እንደሌለ በሚያስመስል ደረጃ ከእምነት ተቋማት እስከ ተራው ሰው ነፍሳችን በመዳፋችን ያለች አስመስለን ለመጠንቀቅ ስንሞክር የታሰበኝ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር አየ እናንተ የማታስተውሉ! አሁን ወጥታቹህ የምትገቡትና ከክፉ ሁሉ የምትጠበቁት በራሳቹህ ጥንቃቄ አላስመሰላቹህትም??? ምነው የጠባቂ መላእክቶቻቹህን (መዝ. 347) ድካምና አገልግሎት ከንቱ ባታደርጉት እናንተ ምስጋና ቢሶች???” ብሎ የሚያዝንብን መሆኑ ነው የሚታሰበኝ!!!

ምን ለማለት ፈልጌ ነው አባቶች ለራሳቸው እያደረጉት ያለው የፈጣሪን ጥበቃ የረሳ ወይም ያራቀ ጥንቃቄና እኛን እንድናደርግ እየነገሩን ያለው ጥንቃቄ የእምነትን ሚና ጥቅም አልባ ወይም ዋጋቢስ በሚያደርግ ደረጃ መሆኑ አግባብነት የለውም፡፡ ክህደትም እንደሆነ ይሰማኛል!!!

የዚህን ያህል ከተጠራጠርንማ የእምነት ወይም የሃይማኖት ጥቅምና አገልግሎት ምንድን ነው ታዲያ??? በተግባር የማይገለጥ እምነትስ ምኑን እምነት ሆነው??? ባጭሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከቤቱ ለማስቀረት ወይም ለማራቅ እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ሊያመጣ እንደማይችል መረዳት፣ መገንዘብ፣ ማመን ነበረባቸው፡፡ እንግዲህ አለማመናችንን እርዳው!” ከማለት ውጭ ምን ይባላል???

እርግጥ ነው ሑር ሕዝብየ ወባእ ቤተከ፡፡ ወዕፁ ኆኅተከ፡፡ ወተኃባእ ኅዳጠ ምዕረ፡፡ እስከ የኃልፍ መዓቱ ለእግዚአብሔር! , ሕዝቤ ሆይ ና ወደ ቤትህም ግባ ደጅህንም በኋላህ ዝጋ የእግዚአብሔርም ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ!” ትን. ኢሳ. 2620 ይላል ቃሉ፡፡ ይሄ ማለት ግን ለኃጥአን የወረደ ለጻድቃን ይተርፋልና ተጠበቁ!” ማለት እንጅ የእግዚአብሔርን ጠባቆት ተጠራጠሩ፣ ዘንጉ፣ እንደሌለ ቁጠሩ ማለት አይደለም!!!

በዚሁ ጥቅስ ቁ. 21 ላይ ስትመለከቱ መዓቱ የመጣበትን ምክንያት ሲናገር በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ያመጣባቸው ዘንድ እነሆ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል ምድርም ደምዋን ትገልጣለች ሙታኖቿንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም!” ይላል!!!

ከዚህ ቃል የምንረዳው ነገር ይሄ ወረርሽኝ ያለምክንያት እንዳልመጣ ነው፡፡ የሚያጠራውን አጥርቶም ይሔዳል፡፡ በዚህ ቸነፈር እንዲሞት የታዘዘበት ሰው ካለ የፈለገውን ያህል ጥንቃቄ ቢያደርግ አያመልጥም ወይም ከመሞት አይድንም፡፡ ከዚህ ቸነፈር የሚተርፈውም ሰው የሚተርፈው ስለተጠነቀቀ ሳይሆን መቅሰፍቱ ስላልታዘዘበት ነው፡፡ ሰው ግን ባይሞትም መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ባይሞትም እንኳ ታሞ መሰቃየት አለና፡፡ እንግዲህ መቅሰፍቱ ለቅጣት እንደመምጣቱ ከዚህ መቅሰፍት የመዳኛ መንገዱም ከኃጢአት መመለስ ወይም ንስሐ መግባት ነው ማለት ነው!!! በመሆኑም እንወቅበት!!!

በዘመናችን እግዚአብሔርን እኔን ከሕይዎት መዝገብ ደምስሰኝ!” እስከማለት ደርሶ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ፍርድ ወይም ቅጣት የሚያድን እና ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ከታዘዘበት መቅሰፍት ጋር ተሽቀዳድሞ በእጣኑ ጭስ ከጥፋት የሚታደግ እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ያለ አባት ከሌለ መቅሰፍቱን ሊያቆመው የሚችለው የእኛ ንስሐ መግባት ብቻ ነው!!!

እንዴት እንደሆነ አይገባኝም እንጅ ወይም ደግሞ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመን ከነበሩት እስራኤላውያን ኃጢአት ይልቅ በዚህ ዘመን ያለነው ሰዎች ኃጢአታችን በእጅጉ ስለከበደና ለምልጃ የማይመች ስለሆነ ይሆናል እንጅ ዛሬ በዚህ ዘመን በጋብቻ ከኖረው ከሊቀነቢያት ሙሴ የላቀ፣ የጠነከረ፣ የበዛ፣ የከበደ ትሩፋት ወይም ብሕትውና ያላቸው ደናግላን ቅዱሳን አባቶች በየበረሃው በየገዳሙ ነበሩን!!!

እስራኤላዊያን በበደሉና መቅሰፍት በታዘዘባቸው ጊዜ የእግዚአብሔር ወዳጁ ሊቀነቢያት ሙሴ በዚህ መልኩ ነበር ሕዝቡን ከእግዚአብሔር መቅሰፍት ጋር ተሽቀዳድሞ የታደገው ሙሴም አሮንን፦ ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተሥርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጥቷልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው። አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሠረየላቸው። በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ!” ዘኁ. 1646-50

እዚህ ላይ ንስሐ እንግባ ስል አንዳንዱ የዋህ ሰው ንስሐ መግባት ማለት ስልብ መሆን ወይም አርፎ ተቀምጦ ግፍ ተቀባይ መሆን የሚመስለው በርካታ አላዋቂ ስላለ ንስሐ መግባት ማለት ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ!” ብሎ መታገልን ወይም ግፈኞችን ለሰው ልጆች መብት ከመታገል መታቀብ ማለት አለመሆኑን አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ እንዲያውም ንስሐ የገባ ወይም ፈጣሪን ያለ ሰው ማንንም ሳይፈራ ሊያደርገው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ!” በማለት እስከሞት ድረስ ታምኖ ግፈኞችን መታገል ነው!!!

ስንክሳሩንና ገድላገድሉን ሁሉ ብታነቡ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሠማዕታት ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ!” እያሉ ለእውነት ሲሉ ከአላውያን ነገሥታትና ከአረማውያን ጋር ሲጋደሉ በሠማዕትነት ማለፋቸውን ትረዳላቹህ!!! በመሆኑም ንስሐ ስንገባ ለእውነት ዋጋ ለመክፈል መቁረጣችን፣ ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ!” ብለን ግፈኞችን ለመታገል መወሰናችን ማለት እንደሆነ ተረዱ!!!

ሌላው ቤተክርስቲያን አካባቢ ቀኖና ቤተክርስቲያን እራሱ የመከላከያ ዘዴ ነውና እሱን ለምእመናን ማሳወቁ መልካም ነው፡፡ የሚያስል ሰው፣ የሚያዥ ቁስል ያለው ሰው መቁረብ አይደለም ቤተክርስቲያን መግባት እንደማይችል የቤተክርስቲያኗ የሕግና ሥርዓት መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ ደንግጓል፡፡ ከምክንያቶቹ ውስጥ ደግሞ የሚያስለው ሰው ቆርቦ ሲያስል የምራቅ ፍንጣቂ ከአፉ ስለሚወጣና እንደመትፋት ስለሚቆጠር ነው!!!

ይሄ ደግሞ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ ክብር የተነሣ ፈጽሞ የተከለከለ ስለሆነ የሚያስል ሰው አይቆርብም ክልክል ነው፡፡ የሚያስል ሰው እስኪሻለው ድረስ ቤተክርስቲያን የማይገባበት ምክንያት ደግሞ ቤተክርስቲያን መላእክት እንደሻሽ የሚነጠፉባት እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ እንዳለባት ጽርሐ አርያም ስለምትቆጠር ንጽሕናዋ መጠበቅ ስላለበት ነው፡፡ የሚያስለው ሰው እያሳለ ከአፉ በሚነጥበው የምራቅ ወይም የአክታ ፍንጣቂ ሊያጎድፋት ሊያሳድፋት ስለማይገባ ነው፡፡ የሚያዥ ቁስል ያለው ሰውም ምክንያቱ ከላይ የተጠቀሰው ነው!!!

ለማንኛውም እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል!” መዝ. 1271 ይላልና ቃሉ እግዚአብሔርን ሳንይዝ የፈለገውን ያህል ብንጥር ድካማችን እንደማይሠምር ዕወቁ!!!

ወደ እነ ፌጦ እንለፍ፦

መቸስ ይሄ በሽታ ያላስጨነቀው የዓለም ሕዝብ የለም፡፡ ሕንዶችን የላም ሽንት ሲያስግታቸው እኛን ወደ ፌጧችን ወስዶናል፡፡ ፌጦ በባሕላችን እናቶቻችን በአዲስ ዓመት መባቻ ጠዋት በባዶ ሆድ በፌጦ የተፈተፈተ እንጀራ እንደሚያበሉን ይታወቃል፡፡ ለምን በአዲስ ዓመት መባቻ በጠዋት በባዶ ሆድ ከምን እንዲያድነን እንደሚያበሉን ግን በባሕል ስም ያደርጉታል እንጅ ምክንያቱን የሚገልጠው መረጃ ከጊዜ ብዛት ጠፍቷል፡፡ ለጤናም ለምናምኑም ጥሩ ነው!” በሚል ብቻ ነው እየተደረገ ያለው፡፡

ብዙ እንዲህ ዓይነት ነገሮች አሉ፡፡ በባሕል የምናደርጋቸውና የማናደርጋቸው፣ ለምን እንደምናደርጋቸውና እንደማናደርጋቸው አብሮት የነበረው መረጃ በአግባቡ ባለመተላለፉ የማናውቃቸው ነገሮች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ለምን እንደሆነ የማናውቃቸው ብያኔዎች በሳይንስም እየተጠሉና እየተመረመሩ ከጀርባቸው ያለው ምክንያት እየታወቀ ትክክል መሆናቸውም እየተረጋገጡ መጥተዋል፡፡ የሰው ልጅ በዚህች ምድር መኖር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በtrail and error ማለትም በሙከራዎች ሒደት ሲያነሣ ሲጥል ያካበታቸው በርካታ ዕውቀቶች አሉ፡፡

እነኝህ ዕውቀቶች የሳይንስ መሠረት መሆናቸውን ብዙዎቻችን አንረዳም፡፡ ለሳይንስ ያላቸው ግብአት፣ አበርክቶና ሚና ከፍተኛና የማይተካ ነው፡፡ ያለ እነኝህ ዕውቀቶች ሳይንስ የትም አይደርስ እንደነበረ የሚያውቁት ራሳቸው በምርምር ሥራ ላይ የተሠማሩት ሳይንቲስቶችና አንዳንድ አስተዋይ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ይሄም ሆኖ ሳይንስ እንደሚለው ሳይንስ እንዲህ መጠቀ ረቀቀ!” በሚባልበት ጊዜ እንኳ በዚህች ዓለም ካለው ነገር ሁሉ የተረዳውና የደረሰበት ሁለት ከመቶውን ያህል ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እናም አንድ ነገር ባሕላዊ ስለሆነና ምክንያቱ በውል ስለማይታወቅ ብቻ መናቅ ወይም ትክክል እንዳልሆነ ማሰብ ድንቁርና ነው!!!

ከሳምንት በፊት ለኮረናው ወረርሽኝ ፌጦ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጤና አዳምና ማር ቀላቅላቹህ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ አንዳንድ ማንኪያ ውሰዱ!’ የሚል መልእክት ከገዳም አባቶች ተነግሯል!” በተባለ ጊዜ በርካቶች ቀልደዋል፡፡ እነኝህ ቅመሞች anti bacteria መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሳይንሱም ምግብን እንደሕክምና እንድንጠቀም በሚመክርበት የጥናትና ምርምር ዘርፉ በሰፊው የሚጠቀምባቸው ቅመሞች መሆናቸው ይታወቃል!!!

ይሄ መልእክት በትክክል ከገዳም አባቶች መጥቷል ወይ?” የሚለው ነው እንጅ ጥያቄው መሆን የነበረበት ጉዳዩ እነ ፌጦ መሆናቸው አይደለም፡፡ ይሄ መልእክት ከገዳም መጣ!” በሚባልበት ወቅት አንዳንዶች እሽ እነ ፌጦ መድኃኒትስ ይሁኑ ግን እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት!’ መባሉ ምንድን ነው???” ብለው የቀለዱም ነበሩ፡፡ ያልገባቸው ነገር ክትባት የሚደረገው ከመያዝ በፊት እንጅ ከተያዙ በኋላ አለመሆኑን ነው፡፡ በሽታውን የያዙ ሰዎች ወደ ሀገራችን ስለገቡ ቫይረሱን ይዘውት የገቡ ሰዎች በቅርባቸው ላሉ ሰዎች ከማጋባታቸውና የተጋባባቸውም ለሌሎች ሰዎች ከማጋባታቸው ወይም ከማስያዛቸው በፊት ተሽቀዳድመው በዚያ የሰዓት ገደብ ውስጥ በእነኝህ ባሕላዊ መድኃኒቶች እንድንከተብ ማድረጋቸው ቢሆንስ??? ከመቀለዳችን በፊት ይሄንን አስበነዋል???

በርካቶች ደግሞ ሊቀልዱ የፈለጉት ከገዳም አባቶች ተነገረ!” መባሉን ነው፡፡ አንዱ እንዲያውም እባካችሁ በአባቶቻችን ስም አትቀልዱ። ገዳማውያን አባቶች በጸሎታቸው ምድርና ሰማይ ያስታርቃሉ፣ መዓት ያርቃሉ፣ ምሕረት ያቀርባሉ። ገዳም የገቡት መንፈሳዊ ኃይል ፍለጋ እንጂ ፌጦ፣ ነጭ ሽንኩርትና ኮረሪማ ለመደባለቅ አይደለም። የገዳም አባቶች ለኮሮና መድኃኒት ይሄን ፈጭታችሁ፣ በጥብጣችሁ፣ ቀቅላችሁ ጠጡ ብለዋል የሚለው መልእክት እንኳን ከገዳም፣ ከገዳም ሠፈር አይወጣም!” ብሎ ከድንቁርናው የተነሣ አፊዟል!!!

ይሄ አስተያየት የደንቆሮ አስተያየት እንደሆነ የሚመሰክረው እኔ አይደለሁም የእግዚአብሔር ቃል እንጅ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ነቢይ ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሡ ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት እሱም ይፈወሳል!” ኢሳ. 3821-22 ብሎ መናገሩን እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤልም እግዚአብሔር በራእይ ስላሳየው ወንዝና በዳርቻው ስለሚበቅለው ዛፍ ሲናገር ፍሬው ለመብል ቅጠሉ ለመድኃኒት እንደሚሆን ይናገራል ሕዝ. 4712

ከዚህም በላይ ደግሞ እራሱ እግዚአብሔር መድኃኒትነት ያላቸውን ዕፅዋት ለኖኅ እንደነገረው በመጽሐፈ ኩፋሌ በምድር ዕፅዋትን (እንጨቶችን) ያድን ዘንድ አጋንንት ከሚያመጡት ደዌ የሚያድንበትን ሁሉ ከሚያስቱበት ጋር ለኖኅ ነገረው፡፡ ኖኅም ፈውስ በሚደረግበት ወገን ሁሉ በመጽሐፍ እንዳስተማረው ሁሉን ጻፈ!” ኩፋሌ 107 ይላል፡፡ ስለሆነም ያ ደንቆሮ ገዳም ያሉ አባቶች እንዲህ አይሉም… !” እያለ የተሳለቀው ነገር በእጅጉ ስሕተት ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶች በተጋድሎ ብዛትና ብርታት ከብቃት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ከሚገለጡላቸው ነገሮች አንዱ እነኝህ እግዚአብሔር ለኖኅ የነገረው ከበሽታና ከአጋንንት ቁራኝነት የሚፈውሱ መድኃኒትነት ያላቸው ዕፅዋት ናቸው፡፡ አላዋቂዋ ዳንኤል ይሄንን ስለማታውቅ ተሳለቀች!!!

ባይገርማቹህ ቅዱሳን አባቶች ብቻ ሳይሆኑ መላእክት እንኳን እራሳቸው ዳስሰው መፈወስ እየቻሉ እግዚአብሔር መድኃኒትነት እንዲኖራቸው ባደረጋቸው ነገሮች ተጠቅመው እንደፈወሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መጽሐፈ ጦቢትን አምስት ገጽ ያላት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ናት አንብቧት፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በሰው ተመስሎ አዛርያ በሚል ስም ለጦቢት ልጅ ጦቢያ አገልጋይ ሆኖ እንደተቀጠረና ጦቢያን እንዳገለገለው፣ ገንዘባቸውን ለማምጣትና ለጦቢያ ሚስት ለማጨት ወደሔዱበት ሀገር ሲሔዱም መንገድ ላይ በጤግሮስ ወንዝ የያዙትና ጠብሰው የበሉትን ዓሣ ጉበት፣ ልብና ሐሞት ጦቢያን እንዲይዝ እንዳደረገውና ጉበቱና ልቡ ክፉ ጋኔን ባደረበት ሰው ላይ ቢያጤሱን እንደሚያድን፣ ዓይኑ ለጠፋበት ወይም ዓይኑ ላይ ብልዝ ላለበት ሰው ደግሞ ሐሞቱን ደቁሰው ቢኩሉት ዓይኑን እንደሚያበራው እንደነገረው እንመለከታለን!!!

በዚህ መሠረትም ጦቢያ ሰው መስሎ ከጎኑ ያለው የእግዚአብሔር መልአክ እንደነገረው በማድረግ በተለያየ ጊዜ ሊያገቧት ያጯትን ሰባት ወንዶች በሠርጋቸው ቀን እያነቀ እየገደለ ያለባል ያስቀራትን ሴት ጉበቱንና ልቡን ከእጣን ጋር አጢሶ ጋኔኑን በኖ እንደጠፋና ሴቲቱን እንዳገባት ሐሞቱንም የታወረውን የአባቱን ዓይን እንዳበራበት ትመለከታላቹህ!!!

እናም እንዳያቹህት የእግዚአብሔር መልአክ እንኳ እንደ መልአክነቱ ዳስሶ መፈወስ ሲችል፣ ጋኔኑንም ቀጥቶ ማባረር ሲችል እግዚአብሔር መድኃኒትነት እንዲኖራቸው አድርጎ በፈጠራቸው ነገሮች ፈውሷል፡፡ እናም የገዳም አባቶችም እግዚአብሔር መድኃኒትነት እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸውን ዕፅዋት እየነገሩ ለዚህ ሕመም ይሄንን ዕፅ እንዲህ አድርጋቹህ ተጠቀሙ!” ቢሉ እንደ ዳንኤል ክብረት ደፋር ደንቆሮ ካልሆንን በስተቀር ከእግዚአብሔር ወይም ከመንፈሳዊነት የወጡ!” በማለት ልንነቅፋቸው አይገባም ወይም ደግሞ የገዳም አባቶች እንዲህ አያደርጉም!” ብለን ልንናገር አይገባም!!! የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መድኃኒትነት ያላቸው ዕፅዋትን በተመለከተ ብዙ የሚናገሩና የሚያስተምሩ መጻሕፍት እንዳሏት ወይም እንደነበሯት ይታወቃል፡፡ እነኝህ መጻሕፍት ከየትም የመጡ አይደሉም፡፡ በእነኝህ ቅዱሳን አባቶች የተጻፉ እንጅ!!!

ይሄው ነው ወገኖች፡፡ ነገሩ በርካታ ተያያዥ ተገሮችን የያዘ ሆነና በጣም አረዘምኩት አንባብያን በጣም ይቅርታ!

እንግዲህ ከዚህ መቅሰፍት ይሰውረን ይታደገን!!! አሜን!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው