ዴሞክራሲያ ቅጽ 48 ፣ ቁጥር 2
መጋቢት ፣ 2012 ዓ.ም
ከቀውስ ወደባሰ ቀውስ ?
በ2011 ዓ. ም ክረምት ላይ “ለውጡ የት ገባ?” በሚል ርዕስ በከተብነው የዴሞክራሲያ እትማችን ለውጡ ሃዲዱን እየሳተ መሄዱንና ወደ ሃዲዱ እንዲመለስ መወሰድ አለባቸው ያላቸውን እርምጃዎች አመላክተን ነበር። ከነዚህ መፍትሄዎች በዋነኛነት በመንግሥት በኩል የሕግ የበላይነትን ማስከበርን ትኩረት እንዲሰጠው ጎትጓች ማሳሰቢያ ይገኝበታል።
እንዳልነውም “ያ ሁሉ ለለውጡ የተቸረ ድጋፍ ወደ ተቃውሞ ባይለወጥም አብዛኛው ዜጋ በለውጡ አካሄድ ግራ ተጋብቷል” ብለን ነበር። ዛሬ ቀስ በቀስ ወደ ተቃውሞ ጎራ የገቡ ሃይሎች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በመፍትሄነት ካቀረብናችው መካከል፡–
• የለውጡ ተቃዋሚዎች ሕግ ሲጥሱ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና አሻጥራቸውን ለማቆም ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግ፣
• የለውጥ ሃይሉ አክራሪ ብሄርተኞችን መለማመጥ ሳይሆን ሕግ ሲጥሱ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ፣
• የችግር ምንጭ የሆነውን የዛሬውን ሕገመንግሥት በብሄራዊ ዕርቅ ማዕቀፍ ለውይይት ማብቃት፣ በሕገ–መንግሥት መሠረት የክልል ጥያቄ የሚያነሱትን ዞኖች የሕገ–መንግሥቱ ዕጣ እስኪወሰን ድረስ ጥያቄያቸው በይደር እንዲቆይ፣
• ምርጫው ሰላምና መረጋጋት ከማምጣት ይልቅ፣ ይበልጥ ያሉትን ችግሮች እንዳያባብስና ለአክራሪዎች አቅም እንዳይሰጥ እንዲዘገይ የሚሉ ነበሩ።
እንደፈራነው በአመዛኙ የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ ወሮበሎች የዜጎችን መሠረታዊ መብቶችን መጣስ ያለምንም ፍርሃትና ማመንታት ቀጥለውበታል። ከለውጡ ማግሥት በድግግሞሽ ያየናቸውና አዳዲስ ችግሮች መላው ሕዝባችንን ሊባል በሚችል ደረጃ ስጋት ላይ ጥለውታል።
በመንግሥት በኩል የሕግ አለመከበር ብዙ ያስጨነቀው አይመስልም። እንዲያውም “በለውጥ ሂደት የሚታይ ወጀብ” ነው በሚል አቃልሎ ይመለከተዋል። መንግሥት አቅም አጥቶ ይሆናል ብለው መላ በሚመቱ ላይ ሕግን ለማስከበር በሚል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያየንባቸው ጥቂት ጊዜያት አሉ። ብርቱ የሀገሪቱ ችግሮች ናቸው ከምንላቸው ዋና ዋናዎቹን ብናነሳ፣ ልዩ ሃይል ተብለው በየጎሣዊ ክልሎች የተደራጁና የታጠቁ ሃይሎች የነዚህ ክልሎች ጎሣዊ አባላት አይደሉም በሚሏቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ነው።
ይህን ጥቃት የሚያደርሱት አንድም ብቻቸውን ነው፣ ወይም በኢመደባዊ ከተደራጁ ሥርዓተ–አልበኞች ጋር በመተባበር ነው። እነዚህ ጥቃቶች የታዩባቸው በኦሮምያ ክልል በተደጋጋሚ፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋና በደቡብ ክልል በተለይም በሚዛን ቴፒ ነው። የፌዴራሉ መከላከያ ሃይል ሰላም ሊያስከብር በተገኘባቸው ጥቂት ጊዜያትና ቦታዎች ልዩ ሃይሉ ለመከላከያውም ተግዳሮት ሲሆኑበት ታይተዋል። በትግራይ ያለው ልዩ ሃይልና ወታደራዊ ስሪት የፌዴራል መንግሥቱን፣ ጎረቤት ክልሎችንና አገርን የሚያስፈራራ ተቋም ሆኗል። ላለፈው በደሉ ንስሃ ገብቶ ወደ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና እድገት ስምሪት ከመግባት ይልቅ ህወሓት ለትግራይ ሕዝብና ለሌሎች ኢትዮጵያዊ እህቶቹና ወንድሞቹ እሾህ መሆኑን ቀጥሏል። ራሱ ጠፍጥፎ የሠራው ሕገ–መንግሥት ከሚደነግገው ውጭ፣ የህወሓት አመራር ባሻው ወቅት ትግራይን እገናጥላለሁ እያለ ይፎክራል።
የሥርዓተ–አልበኝነትና ጥላቻ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ዋነኞቹ ከጥቂት ወራት በፊት ጀዋር መሃመድ በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ለደጋፊዎቹ በላከው መልዕክት ቀስቃሽነት በግፍ የታረዱትና የተጨፈጨፉት 86 ያህል ዜጎቻችን ናቸው። ሌላው ተጠቃሽ ሰለባ የሃይማኖት ቤተ–ዕምነቶችና ምዕመኖቻቸው ናቸው። በእስልምና ዕምነቶችና መስጂዶቻቸው፣ በፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች ቤተ–ዕምነቶች እንዲሁም በከፋና በላቀ መጠን ሰለባ የሆኑት የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምዕመናንና ቤተ–አምልኳቸው ናቸው። በጥቃቱ ብዛትና ውድመት በታሪክም የተወሰነን ብሄርና የተወሰነ ሃይማኖትን ዒላማ ከማድረግ የቆየ ዘመቻ አንፃር፣ ኦርቶዶክስ ክርስትና የፅንፈኞች ልዩ ዒላማ እንደሆነ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው።
የተለያዩ ዕምነት ተከታዮች ለዓለም አርአያ በሆነ መስተፋቅር፣ በጋብቻና በአብሮነት ይዘውት የጠበቁትን እሴት ለመሻርና ለመናድ በእቅድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። ይህ አልበቃ ብሎ እነዚሁ የጎሣ ክልሎች በሚቆጣጠሯቸው የግልና የክልል የመገናኛ ብዙሃን አንዳንዶቹ የእርስበርስ የብሄርና የሃይማኖት ጦርነት ለመቀስቀስ ሳይቦዝኑ ጥላቻን የሚሰብኩ ናቸው።
ይህንና መሰል ጥላቻዎችን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ መንግሥት በቅርቡ በፓርላማ ያወጣው የሃሰትና የጥላቻ ዜና ማሰራጨትን የሚሸብብ አዋጅ፣ ከነእንከኑም ቢሆን (የመናገርና የመፃፍን መብት እንዳይጋፋ ስጋት አለ) በትክክል አጥፊዎቹ ላይ ብቻ ካተኮረ ውጤት ሊያመጣ ይችል ይሆናል። ሌላው ችግር ደቡብ ክልል ተብሎ በሚጠራው እየተስፋፋ የመጣው ከዞን (አውራጃ) በታች ያሉት ዞን ለመሆን፣ ዞኖች ደግሞ ክልል ለመሆን የሚያደርጉት ሩጫ ነው።
ለዚህ የክልልና የዞን ጥያቄ ዋና መሠረቱ ሕገ–መንግሥቱ ነው። በመሆኑም በኢሕአፓ እምነት ሕገ–መንግሥቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ያነሱበትና ሃገራዊ ስምምነት የሌለበት፣ ኢሕአፓም በመቅረፁም ሆነ በማፅደቁ ያልተሳተፈበት፣ በህወሃት ብቻ የተጫነ መሆኑን ደጋግሞ አንስቷል።
ስለሆነም ሕገ–መንግሥቱ ላይ ውይይት ተደርጎ በጋራ ስምምነት እስኪጸድቅ ድረስ ሕገ–መንግሥቱ ለክልሎችና ለዞኖች የሚሰጣቸው የአስተዳደር ስሪት ለውጥ ጥያቄዎች ደጋግመን እንደገለጽነው በይደር እንዲቆዩ እንላለን። መንግሥት ይህን ማሳሰቢያ ባለመስማት ባለፈው ኅዳር ወር የሲዳማን ዞን በመንግሥት እውቅናና ድጋፍ በ10ኛ ክልልነት ሊመሠረት ችሏል።
የቀረው ጉዳይ የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል ጋር የሚያደርገው የፍቺ ዝርዝር ብቻ ነው። በደቡብ ክልል ከ50 በላይ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመኖራቸው ቢያንስ 12ቱ እስካሁን የክልልነት ጥያቄ አቅርበዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ከፍ ወዳለ አስተዳደር እንዲገቡ ጠይቀዋል። በመንግሥት በኩል ጉዳዩ ቅርቃር ውስጥ እንዳስገባው የሚታይ ነው።
በአንድ በኩል ሕገ–መንግሥቱ አይነካም፣ አይደፈርም ይላል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉንም የክልል ጥያቄዎች በእኩል ማስተናገድ አገር ወደማፍረስ የመሄድ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ የተገነዘበና መውጫው የጠፋውም ይመስላል። አሁን መንግሥት ያለው ጊዜያዊ ፋታ መግዣ መከራከሪያ ነጥብ “አዲስ ዞንና ክልል ምሥረታ በርካታ የመንግሥት ተቀጣሪዎችንና ደሞዝተኞችን የሚያበዛ እንጂ ለሕዝቡ የልማት ጥያቄ አንድም አዎንታዊ መልስ አይሰጥም” የሚል ነው።
ይህ በመሠረቱ ትክክል ቢሆንም፣ ለ30 ዓመታት ያህል በጎሣ አክራሪ ብሄርተኝነት የተጨማለቀን ፖለቲካ ለዚያውም አንደኛውን ዞን አዲስ ክልል በማድረግ በር ከከፈቱ በኋላ ሌሎችን ማስቆም አስቸጋሪ ይሆናል። በደቡብ ክልል ለሚታየው መተራመስ አስከፊነቱን በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የጌዲዖ ዞን ነው። የጌዲዖ ዞን ሙሉ በሙሉ በሲዳማ ክልል የተከበበ በመሆኑ በደቡብ ክልል አባልነት ለመቀጠል የብሳዊ ግንኙነት የለውም የአዲሱን ክልል የሲዳማን ፈቃድ ማግኘት አለበት።
ይህ ለጌዲዖም ይሁን ለደቡብ ክልል የሚፈጥረውን ችግር ከወዲሁ በማየት የጌዲዖ ዞንም የክልልነት ጥያቄ አንስቷል። ከዚህ ትርምስ ለአንዴና ለመጨረሻ ለመውጣት መንግሥት አሁንም ኢሕአፓ ያቀረበውን የአዲስ ክልልና የዞን ለውጥ ጥያቄዎችን ሁሉ ሕዝብ የሚስማማበት ሕገመንግሥት ተዘጋጅቶ እስኪጸድቅ ድረስ በይደር ማቆየትን ፖሊሲው ለማድረግ እንዲያስብበት እንመክራለን።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ደግሞ ራሱ መንግሥት የሚሠራቸውና የሚወስዳቸው ኢ–ፍትሃዊ እርምጃዎች ነገሮችን ያወሳስባሉ። ለምሳሌ መንግሥት የሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን (ፋና፣ ኢቢኤስ፣ ዋልታ…ወዘተ) ተደራሽነታቸው እንደቀድሞው ጊዜ ለመንግሥት ብቻ መሆናቸውና አማራጭ ሃሳብ ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች ባመዛኙ የማያስተናግዱ መሆናቸው አሳዛኝ ክስተት ነው። ይባስ ብሎም ኢህአዴግን የተካው የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ዘመቻውን የሚያደርገው በነዚሁ የመንግሥት በሆኑ መገናኛ ብዙሃን መሆኑ ለውጡን እየተፈታተነ ነው።
በተያያዥም የመንግሥት ሠራተኞችና ከፍተኛ ሃላፊዎች በሥራ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጠናና አበል የሚያገኙበት ሁኔታ መቀጠሉ መነሳት ያለበት ነውር ጉዳይ ነው። በአንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮችም ላይ በመንግሥት በኩል ግልፅነትና አሳታፊነት አለመኖሩ ሕዝባችንን ከበፊቱ ብዙም ልዩነት የለም እንዲል እየገፋፋው ነው።
ለምሳሌ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ የብዙ ጎንዮሽ ውይይቶች ለመንግሥት ሩቅ የሆኑ ግን በጉዳዩ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ዜጎች ሃሳባቸውን ለመንግሥት ሊያቀርቡ የሚችሉበት መድረክ አለመኖሩ አንድ ምሳሌ ነው። በዚህ ሕዝባችን ከመንግሥት ጋር ባንድ ሊቆምበት በሚገባ የብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ላይና መንግሥትንና ሕዝብን ሊያቀራርቡ የሚገባቸው ሥራዎች ሁሉ በምክክር ቢሠሩ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በመንግሥትን በሕዝብ መካከል ያለውን መፈራቀቅ በማስወገድ መተማመንን ሊያዳብሩ ይችላሉ ሌላው ግልፅነት የጎደለውና እንቅልፍ የሚነሳው አሳሳቢው የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ ነው።
የመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮች አንድም በዝምታቸው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እርስበርሱ የሚጣረስ መግለጫ መስጠታቸው ሕዝባችንን ግራ አጋብቷል።
ይህ ደግሞ የተለያየ በጎም ክፋትም ለአነገቡ ወገኖች ጉዳዩን በባለቤትነት ይዘው የበለጠ መደናበርን ፈጥሯል። ስለዚህ መንግሥት በአንድ አፍ ሁለት ምላስ መሆኑን አቁሞ፣ ቀዳሚነትን ወስዶ ትክክለኛውን ዜና እንደ አስፈላጊነቱ በየጊዜው ቢያቀርብ ይህንን ክፍተት ሊሞላ ይገባዋል እንላለን።
የታገቱት ተማሪዎች በአብዛኛው (ምናልባትም ሁሉም) አማራ ተብሎ ከሚጠራው ክልል በመሆናቸው፣ ከዚህ ቀደም ግንቦት 15 በዚሁ ክልል የተፈፀመው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ በገለልተኛ አካል አለመጣራቱ ከፈጠረው መንግሥታዊ ጥላቻና ጥርጣሬ ጋር ተዳምሮ የዚህ ክልል ነዋሪዎች ለመንግሥት ያላቸው ከበሬታም ሆነ ዕምነት በእጅጉ ቀንሷል። እንደ ባልደራስ ዓይነት ድርጅቶች በአዲስ አበባ ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳናደርግ በመንግሥት ተከልክለናል የሚሉት ስሞታ ተደጋግሞ ቢቀርብም፣ በስብሰባ አከራዮች በኩል ደግሞ ሌሎች የመርሃ ግብር ችግሮች እንዳላሳኩላቸው ሲናገሩ ማድመጥ ተለምዷል።
እውነቱ የትኛው ነው? በሕዝብና በመንግሥት ክፍተት የሚፈጥርና የፈጠረ ጉዳይ ስለሆነ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አሁንም ሕዝብን ሊያጠግብ የሚችል መግለጫ በጉዳዩ ቢሰጥበት ብዥታውን ያጠራል።
ዜጎች በፍትህ ሥርዓቱም ላይ ጥርጣሬና ስጋት ካሳደሩ ቆይተዋል። በፍርደ–ገምድልነት “መበደል መበደል ወታደር በድሏል፣ ግን ባላገር ይካስ” እንዲሉ፣ የሚያዙትና የሚታሰሩት ጥፋተኞች ሳይሆኑ በደል የደረሰባቸው ናቸው የሚሉ ስሞታዎች ይሰማሉ።
ሌላም አስፈሪ የሆነ መንግሥታዊ ግልፅነት የጎደለው ክስተት አለ። ይህም ህገወጥ የመሣሪያና የገንዘብ ዝውውር ነው። መንግሥት አልፎ አልፎ በርካታ ገንዘብና መሣሪያ ይዣለሁ ከማለት ያለፈ የምርመራውን ውጤት፣ እነማን እንደሆኑ፣ ለምን ዓላማ አቅደው እንደሆነ…ወዘተ ግልፅ ተደርጎ ስለማይታወቅ ዜጎች እያንዣበበባቸው ባለው አደጋ ራሳቸውን ለመከላከል እንዳይዘጋጁ መረጃው እንኳን የላቸውም።
በሌላ በኩል በአዎንታዊ ጎኑ ልንገነባቸውና ልንጠብቃቸው የሚገቡ ጥቂትም ቢሆኑ ተስፋ ሰጭ ምልክቶች አሉ። ከነዚህ መካከል በአማራው ክልል የአማራና የቅማንት ግጭት ረገብ ማለቱና ሰላም መምጣቱ ሊጠቀስ የሚገባው ክስተት ነው። እንዲሁም በጥምቀት በዓል አካባቢ የጋሞ ብሄረሰብ አባቶች ወደ ጎንደር ሄደው በዓሉን በጋራ ያከበሩበት ክስተት ጥሩ ምሳሌ ነው።
በተጨማሪም የአቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በቅርቡ በመላ አገሪቱ ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ማድረጉ ይበል የሚያሰኝ ነው። በወርሃ ነሃሴ 2012 ዓ. ም በታቀደው ምርጫ ላይ እንደሌሎች አጋሮቻችን እኛም በጉዳዩ ላይ ሃሳባችን ሰጥተን ነበር።
በአጭሩ በሀገሪቱ በሚታየው አለመረጋጋትና ምርጫውን የሚያካሂደው ምርጫ ቦርድም በበቂ ባለመዘጋጀቱ ምርጫው ይራዘም
ያልነውን ሃሳብ እንደገና እናፍታታው። ከላይ በጠቀስናቸውና ባላነሳናቸው ሌሎች ችግሮች ምክንያት በሀገሪቱ ላይ የፈጠሩት አደጋዎች ሥር እየሰደዱ በመሄዳቸው እንኳንስ ምርጫ ተራ ልማትም ማካሄድ ከማይቻልበት አስጊ ደረጃ ላይ ተደርሷል።
ለዚሁ ምሳሌ ኦሮምያ ተብሎ በሚጠራው ክልል የሚታየው የፖለቲካ ምስቅልቅል አንዱ ነው። ምዕራብ ወለጋ ውስጥ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በቀጣይነት በማይታይ ሁኔታ ሸኔ ኦነግ የተባለ ቡድን ሕዝብና አገርን ያምሳል። ባንኮች ይዘረፋሉ፣ የመንግሥት ሃላፊዎችና ነጋዴዎች ይገደላሉ፣ ንፁሃን ዜጎች የቀን ተቀን ሥራቸውን ማካሄድ አልቻሉም።
ከላይ የጠቀስናቸው 86 ዜጎች በግፍ የተገደሉትና እስካሁን ገዳዮቻቸው ያልተጠየቁበት፣ ተጨማሪ ወንጀሎችም የሚፈፅሙበት በዚሁ ክልል ነው።
እንደ ሐረሪና ድሬዳዋ ባሉ አጎራባች ክልሎች በብልፅግና ፓርቲና በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከወዲሁ የሚደረገው መገፋፋትና በኢ–መደባዊ መንገድ የተደራጁ ወሮበሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሷቸው ጉዳቶች፣ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ከቤት ወጥተው ለመግባት ያለባቸውን ፈተና ጨምረውታል።
እንደ ኢሕአፓ ዓይነት የአንድነት ሃይሎች በህቡዕ ካልሆነ በስተቀር በግልፅና በክልል መንግሥት ድጋፍ በአንዳንድ ክልሎች (ኦሮሚያ፣ ትግራይ) ሊንቀሳቀሱና ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሊያደርጉ የሚችሉበት መንገድ ተዘግቷል። የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች አንፃራዊ ሰላም ያላቸው ቢመስሉም ጥቂቶቹ እስካሁን ድረስ እንደተዘጉና መንግሥት እንዳለው 40 ሺህ ያህል ተማሪዎች ሰላም ባለመኖሩ ምክንያት ከትምህርት ገበታ የተለዩበት ሁኔታ ነው ያለው።
መታገትን በመፍራትና ሕይወትንም ለማዳን ተማሪዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ከቀያቸው ውጭ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ግዛት ለትምህርት ይሄዳሉ ብሎ ለማመን አይቻልም። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት መሸርሸር የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። በተባለው የጊዜ ሰሌዳ ምርጫው ከተካሄደ፣ ሊከተል የሚችለውን አደጋ ብዙዎች የውጭ ተቋሞች ጭምር ከወዲሁ እየተነበዩ ይገኛሉ። ኢሕአፓም ደጋግሞ እነዚህን እምቅ አደጋዎች ጠቁሟል።
ዋነኞቹ፦ • በምርጫው የተሸነፈ ቡድን “ምርጫው ተጭበርብሯልና ውጤቱን አልቀበልም” በማለት አመፅ ከማነሳሳት ወደኋላ አይለም። የክልሎች ልዩ ሃይሎችና በተለይ ኢ–መደባዊ ድርጅቶች ባልፈረሱበትና መደባዊ አደረጃጀት ቅርፅ ባልያዙበት ሁኔታ እንኳን ዘንቦብሽ ነውና ንፁሃን ዜጎችን በሰበብ አስባቡ “ጠላቴን እገሌን መርጠሃል” በሚል ከማጥቃት አይመለሱም።
ምርጫው በግድ ይደረጋል ከተባለ፣ በመንግሥት በኩል ከአሁኑ በቂ የመከላከያ ሃይል በማዘጋጀት ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት ለመጠበቅ ስምሪት በአነሳሽነት በፍጥነት እንዲተገብር ከወዲሁ ኢሕአፓ አአበክሮ ያሳስባል።
• ምርጫ ቦርድ ካወጣው የጊዜ ሰሌዳ ውጭ በብልፅግናም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በሕገወጥነት በመቀጠሉና ይህን ተከትሎ የፓርቲ የድጋፍና የተቃውሞ መፋተጎች ከአሁኑ በመታየታቸው ሰላማዊው ዜጋ የሚጎዳበት ሰፊ ዕድል ይኖራል።
• ምርጫው በሰላም ሊካሄድ ይችላል ብለን ብናምን እንኳን ምርጫ ቦርድ ለማስፈፀም የሚችልበት ብቃት አለው ብለን አናምንም። ሰላማዊ የምርጫ ውዝግብ ቢነሳም ችግሩን ለመፍታት በቂ ቁመና ያለው የሕግ አካል ገና ስላልተፈጠረ ምርጫውን ነሃሴ 2012 ዓ. ም ማካሄድ ባወጣው ያውጣው የሚል የግዴለሽነት ሥራ ይሆናል።
• ሰላማዊ ዜጎች መንግሥት ሕግን በማስከበር እስካሁን ያሳየውን ቸልተኝነት በመታዘብ ይልቁንም በምርጫ ወቅት ሊመጣ ከሚችለው አደጋ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመታደግ በአለች አቅማቸው አስቤዛ አከማችተው ቤት ዘግተው ለመቀመጥ በሚያደርጉት ውሳኔ የዕቃዎች ዋጋ በተለይም የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ ንረት ሊከተል ይችላል።
ይህን አደጋ ሊታደገን የሚችለው ምርጫን አዘግይቶ ብሄራዊ እርቅንና ውይይትን ማስቀደም እንደሆነ ደጋግመን ገልጸናል። ምርጫው የሚራዘምበትን የጊዜ መጠን በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካይነት ሁሉም ፓርቲዎች በምክክር በጋራ እንዲወስኑት ሆኖ እስከምርጫው ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ሀገሪቱን ማስተዳደሩን ይቀጥላሉ።
ዛሬ የኅብረተሰባችን ልሂቃን በብሄር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ልዩነት እየተወዛገቡ እንወክለዋለን የሚሉትን ደጋፊም ወደዚህ ትንንቅ እያስገቡት ይገኛሉ። ስለዚህ ቆም ብለን የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና እናቶችን ማዕከል ያደረገ የእርቅ፣ የይቅርታና የሰላም ውይይት በሰፊው ማድረግ ምርጫ ከማድረግ ቢቀድም ብለን ዛሬም ድምፃችን ከፍ አድርገን በአፅንዖት እንናገራለን።
ብሄራዊ እርቅ ባስቸኳይ!!
የአንድም ኢትዮጵያዊ ሕይወት በግፍ መጥፋት የለበትም!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ!