Apr 10, 2020

  https://www.youtube.com/watch?v=Yl3lfsgIaBg&feature=youtu.be

የነሐሴ 2012 አገራዊ ምርጫ መራዘሙን እንደግፋለን!!
መጋቢት 27/2012

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

ዛሬ ኢትዮጵያ እጅግ የከፋ አደጋ ከፊቷ በተጋረጠባት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ጊዜ ሕዝቧ በሙሉ በአንድ ቆሞ እየመጣበት ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመጋፈጥ ዝግጁነት ይፈጥር ዘንድ ከፈተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ለበለጸጉ ሀገራት የከበደ ወረርሽኝ እዚያ በተስፋፋበት ደረጃ ሀገራችን ውስጥ ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መተንበይ ከወዲሁ ያሰቅቃል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የብዙዎች ግምት ሲሆን በመጭዎቹ ሦስትና አራት ሳምንታት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልና በርካቶችም በጽኑ የሚታመሙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሲገመት ለጽኑ ሕሙማን የሚያስፈልገው የህክምና አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት መኖሩም ይታወቃል፡፡ እየመጣ ላለው ከፍተኛ ወረርሽኝ መከላከያ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያውያን የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ቤታቸውን፣ ድርጅቶቻቸውን፣ ንብረታቸውንና ገንዘባቸውን ሊመሰገን በሚገባና በሚደነቅ ለጋስነት ማድረጋቸው ኢትዮጵያውያን/ት ዛሬም አንዱ ዜጋ ለሁሉም ወገኑ የሚያስብና የሚሳሳ መሆኑን የሚያሳዩ ክስተቶች ሆነዋል፡፡

ይህ ወረርሽኝ በአስደንጋጭ ሁኔታ ዓለምን እያመሰ ባለበትና የበለጸጉት ሀገሮችም በተንበረከኩበት ወቅት፤ በርካታ ሕዝብ ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፕሮግራሞች በተሰረዙበት አስጨናቂ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ያታቀደው አገር አቀፍ ምርጫ በታሰበለት መርሀግብር እንደማይካሄድ ገልጿል፡፡ ይህ መግለጫ እንደወጣ ደግሞ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መሀል የውሳኔውን አሰጣጥ ትክክለኛ ያለመሆን (አሳታፊ ያለመሆን) እና ምርጫውን ማስተላለፍ ሀገሪቱን ለከፋ ችግር የሚዳርግ ሊሆን እንደሚችል ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡

ኢሕአፓ ቀደም ሲልም በመላ ሀገራችን ሠላምና መረጋጋት በሌለበትና የህግ የበላይነት ሳይረጋገጥ ሀገራችን ዉስጥ ነፃ፣ ርትዓዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ያለመኖሩን በመግለጽ ምርጫው እንዲተላለፍ በመግለጫዎችና ከመገናኛ ብዙሀን በተደረጉ ቃለ ምልልሶችም ላይ ጭምር አበክሮ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ሆኖም መንግሥት እና አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢሉ እንኳን ምርጫው ሊቀር እንደማይችል መግለጻቸውና ምርጫ ቦርድም ምርጫውን ለማካሄድ ቀን ከሌት እሠራለሁ ማለቱ ኢሕአፓ ሲያስገርመውም ሲያሳስበውም ቆይቶ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ገዥው ፓርቲና መንግሥት በግድ ከጫኑብን በሚል በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ጀምረን ነበር፡፡ ዛሬ ሀገራችን በምትገኝበት እጅግ በጣም አስጊ በሆነ፣ ዓለምን ያሸበረው ወረርሽኝ በርከት ያለ የህዝብ ዕልቂት እንዳያደርስ ሀገራችን ጭንቅ ዉስጥ በገባችበት ሁኔታ፣ ህዝብን ከወረርሽኙ መታደግ የሁሉም ዜጋ ግዴታ በሆነበት ሰዓት፣ ስለምርጫ መደረግ ማሰብ እንኳን ሊነወር የሚገባ ነው እንላለን፡፡

ዛሬም ቢሆን በፊት ምርጫው እንዲራዘም ያቀረብናቸው ምክኒያቶቻችን እንዳሉ ናቸው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ዛሬ እጅግ ልዩ የሆነ ሀገራዊ አደጋ ተከስቷል፡፡ ሀገሪቱ ባለባት የሰላምና መረጋጋት ያለመኖር፣ የሕግ የበላይነት ያለመስፈን ፣ የዲሞክራሲ እጦት፣ የዘረኝነት አባዜ፣ የመፈናቀል፣ በድህነት ውስጥ የመማቀቅ ….ወዘተ ችግሮች ላይ በርካታ ህዝቧን ሊጨርስ የሚችል ወረርሽኝ አንድ እግሩን አስገብቷል፡፡ይህች ሀገር እንደሀገር መጻኢውን ችግር መቋቋም የሚችል የኢኮኖሚ አቅም የላትም፣ ለእለት ጉርሱ ደፋ ቀና የሚልና በተራዘመ የኑሮ ውድነት የተዳከመ ሕዝብ፣ የጽዳት ቁሳቁስ አይደለም ለተወሰኑ ቀናት እንኳን ጉርሳቸውን መግዛት የማይችሉ ዜጎች፣ ቫይረሱን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እጁን በውሃና ሳሙና የመታጠብ ቁሳዊም ሆነ ስነልቡናዊ ዝግጁነት የሌለው ማህበረሰብ፣ ሕይወትን ለማዳን ሲባል ያልተቀራረበ ማህበራዊ ግንኙነት መፍጠርና ከሩቅ ሰላም መባባል የሚፈተነው ማህበራዊ ቁርኝቱ….ወዘተ ያለባት ሀገር ነች፡፡

በአንጻሩ በዚህ ግራ በሚያጋባ ዘመን፣ ነገ ይህን ያህል ሰው ሊቀጥፍ ይችላል በሚባል ወረርሽኝ ፊት ብቻውን በርትቶ ለመቆም እንኳንስ ኢትዮጵያን የመሰሉ አገራት መንግሥታት አይደሉም ሃያላኑም አልሆነላቸውም፡፡ በመሆኑም መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የማህበረሰብ ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት፣ የሃይማኖት ተቋማት ልዩነቶቻቸውን ሁሉ አሽቀንጥረው ጥለው በአንድነት መቆም ብቻ እንደሚያዋጣቸው ተገንዝበዋል፡፡ ወረርሽኙ የቀንና የሌሊት ሀሳብ በሆነባት ሀገር ልዩነቶችን ሁሉ ትቶ ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጋር በአንድ ለመቆም ሁሉም ቃል በመግባት ከደጅ የቆመው አስፈሪ እልቂት በሙሉ ሃይሉ እንዳይገባ ለመከላከል በጽናት መቆም ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ሁሉ የወረርሽኝ ወከባ ውስጥ ደግሞ ሰላምን የሚያውኩ እና የሕዝቡን መንፈስ የሚያሸብሩ ሁኔታዎችም ከመከሰት ወደኋላ አላሉም፡፡ ዛሬም በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀል ይታያል፣ ዛሬም ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ይፈጠራሉ፣ ዛሬም ጦርነት ጦርነት የሚሸቱ አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝቡን ማሸበሩ አይቀሬ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ በተምታታ ወቅት እና ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ በፍጹም በማይቻልበት ሁኔታ የምርጫውን መተላለፍ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት አለመደገፍ ምን ይገባል? ዛሬ እኮ መራጩም ሆነ ተመራጩ ነገን ለማለፋቸው እርግጠኛ መሆን አይደለም ማሰብ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር አያውቁም ማለት ነው? መላው ህዝብ ይሁንታውን የሰጠው ሕገመንግሥት ባለባቸው ሀገሮችስ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ፣ አንድ ሀገራዊ አደጋ ሲመጣ፣ የህገ መንግሥት አንቀጾች ራሳቸው በሚፈቅዱት መንገድ “በሥራ ላይ እንዳይውሉ” አይደረጉምን/አይጣሱምን? ደግሞስ በኢትዮጵያ ምድር ሕገመንግሥት ተጥሶ አያውቅምን?

በአብዛኛው የቅርጽ እንጅ የይዘት ለውጥ ባልተደረገበት የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ሰዎች ስለተመደቡ ብቻ ምርጫ ቦርድ የነጠረ ዲሞክራሲያዊ ተቋም እንዲሆን መጠበቅ ትክክል ይሆናልን? ሁሉ ነገር አንጻራዊ ነው፤ ምንም እንኳን ሊነሱ የሚገባቸው ጉድለቶች መኖራቸውን መካድ ባይቻልም ሁኔታዎችን በአንጻራዊነት መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ራሱን ብቁ የሆነ የዲሞክራሲ ተቋም ለማድረግ በትግል ውስጥ ያለ ድርጅት እንደሆነ ማሰብ ለሁላችንም ጠቃሚ ይመስለናል፡፡ የኮሮናው ወረርሽኝ በፈጠረው ሀገራዊ አደጋ ምክኒያት በዚህ ዐመት በነሀሴ ወር (2012) ሊደረግ የነበረውን ምርጫ በሚመለከት የምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውም ውሳኔ ትክክልና ተገቢም ነው ብለን እናምናለን፡፡

ኢሕአፓ የወረርሽኙን ወላፈን አስቀድሞ ገረፍ ላደረጋቸው ዜጎች መንግሥት ዝግጁ ሆኖ ፍላጎታቸውን ማሟላት ከመቻሉ በፊት አቅሙ በፈቀደ መጠን አጋርነቱን የገለጸ ፓርቲ ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ህዝቡ፣ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የዕምነት ተቋሞች፣ የሚያደርጉትን ጥረት አበረታችን መደገፍም ያለበት መሆኑን ያምናል፣ የእንቅስቃሴውም አካል ሆኖ ለመቀጠል ጽኑ ፍላጎት አለው፡፡ በአዲስ አበባና በየክልሉ የሚገኙ አባላቱ የእንቅስቃሴው አካል እንዲሆኑ በማንቃት ራሳቸውንና ሕዝቡን ከወረርሽኙ እንዲከላከሉ መልዕክት በማስተላለፍ ላይም ይገኛል፡፡

ከፊታችን የተጋረጠው ቀጠሮ የማይሰጥ አውዳሚ የሆነ ጠላት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልብ አብረን ከቆምን ከፊታችን የተደቀነብንን ፈተና ያለጥርጥር በአቸናፊነት እንወጣዋለን፡፡ ዓለማቀፋዊ ተሞክሮ እንደሚያመለክተውም ወረርሽኙ የሚያስከትለው መዘዝ አገሪቱን ምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚያስገባት መተንበይ አይቻልም፡፡ ኮሮናን ድል ለማድረግ በአንድነት እንነሳ!!

የነሐሴ 2012 አገራዊ ምርጫ መራዘሙን እንደግፋለ!
ሕዝብን የማዳን ጥረቱ አካል እንሁን!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!