April 12, 2020
የአማራ ክልል ሕዝብ ለሕግ የበላይነትና ለሰላማዊ ሕይወት ታላቅ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን ለሕግ መከበርና ለሰላም ልዕልና እንኳንስ ሃብቱንና ጉልበቱን ደሙን ለመገበር የማይሳሳ ስለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው። በዚህ ዘመንም በሚኖርበት ክልል ብቻ ሳይሆን ከወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በጋራ በአጥንትና በደሙ በገነቧት ሃገራቸው ዜጎች በማንነታቸው ሳይገፉና በህገ-ወጦች ሳይንገላቱ በየትኛውም ቦታ መብታቸው ተከብሮ በፍትህ፣ በእኩልነትና በሰላም መኖር እንዲችሉ የሚሻ ብቻ ሳይሆን የሚታገል ሕዝብ ነው።
የአማራ ክልል ሕዝብ በጥበብና በአርቆ አስተዋይነት መፈታት ያለባቸው ውለው ያደሩ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ ከሃገራችን ሕዝቦች ጋር በጋራ በመቆም ታግሎ ድል ሊነሳቸው የሚገቡ ከባድ ሃገራዊ ሥጋቶች አሉ። የክልሉን ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች ለመመለስና እንደ ክልልና እንደ ሃገር ከፊታችን የተደቀኑ ሥጋቶችን መክቶ በድል አድራጊነት ለመዝለቅ የውስጥ አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስትና ሰፊ ሕዝብ ጠንቅቀው ይረዳሉ።
ከዚህ በተፃራሪ ከማሕበረሰባችን የሕግ አክባሪነት፣ የሰላም ወዳድነትና ፍትሃዊነት በእጅጉ ያፈነገጡ በአጭሩ ካልተቀጩም የሕዝባችንን አንድነትና ጥንካሬ የሚሸረሸሩ ከተራ ውንብድና፣ ቅሚያና ዘረፍ ያልዘለሉ የሥርዓት አልበኝነት ተግባራት በማቆጥቆጥ ላይ ይገኛሉ። ይህንን እኩይ ተግባርም የበደላቸው ወላፈን ላልደረሰውና በቅርብ ለማያውቃቸው የክልላችን ሕዝብ በማይመጥነውና በጀግንነቱ መጠሪያ ስም በሆነው የፋኖ ካባ ጀቡነው ሊያቀርቡት ይሞክራሉ።
ፋኖነት አርበኝነት ነው፤ ፋኖነት ለሃገር ክብር ዘብ መቆም ነው፣ፋኖነት ከራስ በላይ ለሚልቅ የሕዝብ ጥቅምና ፍቅር ሕይወትን አሳልፎ መስጠት ነው። ፋኖ የልማት ፈጻሚ፤ የሰላም ጠባቂ፤ የበጎነትና የጀግንነት ምሳሌ ነው፡፡ ፋኖ የህዝብ ቀኝ እጅ ፤ የችግርና የመከራ ተካፋይ፤ የጎደለውን የሚሞላ ፤ የሞላውን የሚጠብቅ ነው፡፡ ፋኖ አሁን ለደረስንበት የለውጥ ጊዜ የማይተካ ሚና የተጫወተ ሃይል በመሆኑ መንግሰት፤ ህዝብና ታሪክ አይዘነጉትም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ፋኖ የአማራ መንግሰትና ህዝብ የጸጥታና ልማት አቅምና መከታ እንጅ ጠላትና ስጋት አይደለም፡፡
ካባውን አጥልቀው የሚንቀሳቀሱት ህገ-ወጦች ግን ከማህበረሰቡ እሴትና ባህሪ እጅግ አፈንጋጭ የሆኑ ግብሮችን አየፈጸሙ መቆየታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ህፃናትን ማፈንና መግደል፤ ባለሙያዎችንና ባለሃብቶችን አግቶ እንደ እንስሳ ዋጋ እየተመኑ ማስከፈል፤ የእናቶችንና የእህቶችን መቀነት መፍታት ብሎም መድፈር፣ በብዙ ድካምና ላብ ያፈሩትን ሃብት መንጠቅ፣ ነጋዴዎች ከወረታቸው /ካፒታላቸው/ በላይ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉ ማስገደድ… ወዘተ የመሳሰሉት እንደ አብነት የሚጠቀሱ አፀያፊ ተግባራት በህገ-ወጡ ቡድን ተፈጽመዋል። ከምንም በላይ ህገወጥነት በጠራራ ጸሃይ እና በአደባባይ ታውጆ እነዚህና መሰል ድርጊቶች ከራሱ አብራክ በወጡ ልጆቹ መፈፀሙ ህዝባችንን እጅግ አሳዝኖታል አሳፍሮታልም።
እውነታውና ሃቁ ይሄ ሁኖ ሳለ እነዚህ ህገ-ወጥ ቡድኖች መራራ ድርጊታቸውን የሚሸፍኑት “ለአማራ ህዝብ ነፃነትና መብት መከበር የታጠቅን የክፉ ቀን ጠበቃዎች” በሚል ስላቅ ነው፡፡ ይህንና ሌሎች ከህገ-ወጦቹ መንደር የሚመረተውን ሃሰትና የወዥንብር ወሬ ተቀብለው በማህበራዊ ሚዲያ የሚያከፋፍሉና ከዚህ ግርግር ለማትረፍ የሚታትሩ ተስፈኞች ጥቂት አይደሉም፡፡ ሰበር ዜናቸውም “አማራ ተወሯል ታጠቅ” አሰከማለት ይዘልቃል፡፡ ጩኸቱና ፕሮፓጋንዳው ግን ለእውነትና ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ድብቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍና በግፍ ከተነጠቀ ሃብት ፍርፋሪ ለመልቀም የሚፈልጉ ቡድኖች የሚያደርጉት መሆኑን ልብ ማለት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለእውነትና ለህዝብ የቆሙ ቢሆኑማ ኖሮ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት ህፃናት፣ እናቶች፣እህቶች፣ ሃብት ንብረታቸው የተዘረፉባቸው ዜጎች፤ ካላቸው አንጡራ ሃብት በላይ የግዴታ ዕዳ ተጥሎባቸው ተበድረው ከከፈሉ ዜጎች፡ ቤተሰቦቻቸውን እንደ እንስሳ በገንዘብ ከገዙ ዜጐቻችን ጎን በመቆም የእነርሱ ድምጽ ሆነው ማገልገል ነበረባቸው፡፡
የአማራ ክልል መንግስት የታጠቁና ያልታጠቁ ስርዓት አልበኞችን የማስተካከልና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ህገ-መንግሰታዊ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። ወላጆቻችን ፍሬውን ከገላበው ለዩ እንዲሉ፤ እውነተኛውን ፋኖ ከዘራፊዎች ቡድን ለመለየትና ፀያፍ ድርጊት ፈፃሚዎች እንዲሁም ከኋላቸው ያደፈጡ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተስፈኞች ከስህተታቸው ተምረው የሰላም እንቅፋት እንዳይሆኑ፤ እንደ ሃገራችን ባህል በሃገር ሽማግሌዎች፣ በእምነት አባቶችና በታዋቂ ግለሰቦች እንዲመከሩና እንዲመለሱ የክልሉ መንግስት በፍፁም ሆደ ሰፊነት ዕድል ሲሰጥ ቆይቷል። ህገ-ወጡ ቡድን ግን ከዚህ በተጻራሪ የመንግሰትን የሠላም እጅ እና የትግስት አንቀልባ በተለያየ ሁኔታና ቦታ ሲቆርጡና ሲቀዱ ቆይተዋል፡፡ ለአብነት ያክል ለድርድር የሚጓዙ የመንግሰት ተወካዮች ላይ የደፈጣ ጥቃት፤ በድርድር ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተስማምተው ቀነ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ለልማት የተሰማሩ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችን አድፍጦ መግደል፤የዘረፋ ማዘዣ ጣቢዎችን ለማፍረስና ዘረፋን ለማሰቆም የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ ሀይሎችን መግደል …ወዘተ ይገኙበታል፡፡
እነዚህን ሁኔታዎች ለማስቆም የክልሉ መንግሰት በሙሉ አቅሙ የጸጥታ ኃይሉን አሰማርቶ ከሰላም ወዳዱ ማህበረሰባችን ጋር በመሆን ህግና ስርዓት የማሰከበር ስራውን ሲጀምር ለህግ ተገዥ በመሆን ፈንታ የክልሉን የጸጥታ ሀይል በማኮሰስ የተወሰደውን አርምጃ በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን አንደተተገበረ አድርጎ በማቅረብ የተለመደውን የበሬ ወለደ ትርክታቸውን በአጉል ተሰፈኛ ፖለቲከኞችና በጥቅም ተጋሪ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊታቸው ህዘቡን ግራ ለማጋባት ሞክረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ግን በዚህ ውዥንብር ሳይዘናጋ የህግ ማሰከበር ስራውን ከሽምግልና ጥረቶች ጋር ጎንለጎን በማሰኬድ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች የጀመሩት የሰላም ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ አድርጓል፡፡
በመሆኑም በክልላችን በልዩልዩ አካባቢዎች መሽገው የነበሩ ህገ-ወጦች ለክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስከባሪ ሀይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ቦታዎች ህገ-ወጡ ሀይል ለሰላም ካለው ንቀትና መንግስት ለአካባቢው ሠላምና ደህንነት ካለው ጥንቃቄ የተነሳ የጸጥታ ሀይሉ ጥቂት የማይባል የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ለተከፈለው መስዋእትነት መንግስትና ህዝባችን ታላቅ ክብር ይሰጣሉ፡፡ ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ የጸጥታ ሀይሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እርምጃ ሲወሰድ ተስፈኞች የተለመደውን የ”ፋኖ ተጠቃ” ጩኸት በማስተጋባት በክልሉ ግጭት እንዲነሳ ለማድረግ ቀስቅሰዋል።
በኃያላን ሃገሮች ሳይቀር የሰውን ልጅ ሕልውና እየተፈታተነ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በሃገራችንም ሆነ በክልላችን የደቀነውን የሞት ድግስ ለመከላከል ሌት ተቀን በሥራ በተጠመድንበት ወቅት መንግሰት ሃሳቡን፤ ሃብቱንና ጉልበቱን እንዲበታትን የሚደረገው ዘመቻና ሁከት የዘራፊውና የተስፈኛው ቡድን ከራስ ርካሽ ጥቅም በላይ አሻግሮ የማያይ መሆኑንና ለህዝብ ጥቅም ደንታ የሌለው መሆኑን ነባራዊ ምስክር ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ለአማራ ህዘብና መንግስት ፋኖ ማለት ለሰላምና ለህግ የበላይነት ዘብ የቆመና ቀፍድዶ የያዘንን ድህነት ከስሩ መንግሎ ለመጣል ቀን ከሌት በየሙያ ዘርፉ ተሰማርቶ የሚደክም የልማትና የሰላም ሰራዊት ሁሉ ነው፡፡ እታገልለታለሁ ከሚለው ሕዝብ ጉያ ነጥቆ አግቶ የሚገድል፡ በገንዘብ የሚሸጥ ፤ ዜጎች ከቀያቸውና ሰርተው ሃብት ካፈሩባት የሚያፈናቅልና በህዝብ ህልውና ሰላም ጠባቂዎች ላይ ቃታ የወጠረ የፋኖን ክንድ ሊወክል አይችልም፤ መቸም ቢሆን ፋኖ ሊሆንና ሊባል አይችልም፡፡
አሁን በመንገኝበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ለሕዝብ ደህንነት በጋራ መቆም ሲገባ በማድባት አደጋ ለመደቀን መሞከር የሃገር ክህደት በመሆኑ፤ የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይል የህግ የበላይትንና ሰላምን ለማረጋጋጥ የማያዳግም እርምጃ መወሰዱን የሚቀጥል መሆኑን እያሳወቅን፡-
1. የአማራ ህዝብ ደህንነትና ሰላም የሚጠበቀው በመንግሰት መዋቅር በሚመራ የዕዝ ሰንሰለት ብቻ መሆኑን እየገለጽን ለዚህ ዓላማም በአካባቢያቸው ማህበረሰብ በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑና ከመንግሰት ጋር ለመሰለፍ የሚፈለጉ ሁሉ በራችን ክፍት መሆኑን እንገልጻለን፡፡
2. አስተዋዩ የክልላችን ሕዝብ ህገ-ወጥ ቡድኖች የክልላችን የፀጥታና የልማት ሥጋት መሆናቸውን በመረዳት፣ በሌላ በኩልም የማያያቸውና ማንነታቸውን የማያውቃቸው በማህበራዊ ሚዲያ ወደ ጥፋት የሚገፋፉ አዛኝ ቅቤ አንጓች ኃይሎችን የረቀቀ ደባ በመረዳት መንግስትና የጸጥታ ሀይሉ ለሚወስዱት የሰላምና ፀጥታ ማስከበር እርምጃ የተለመደውን ድጋፉን እንዲያሰቀጥል ጥሪ እናቀርባለን።
3. የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ከመንግሰት ጋር በመሆን የጀመሩት የሰላም ጥረት ፍሬ እያፈራ ስለሆነ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ እያቀረብን ከዚህ በፊት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና ከአክብሮት ጋር እናቀርባለን፡፡
4. ምግባሩን ሳይኖሩት በፋኖ ስም በሚነግዱ ቡድኖች ተወናብደው የጥፋት አካል የሆኑ የክልላችን ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ ወጣቶች በሰላም ወደ ማሕበረሰባቸው እንዲመለሱ ጥሪ ስናቀርብ መንግስትና ሕዝብ የይቅርታ እጆቹ የማይታጠፉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
5. የመንግስትን የሰላም ጥረትና የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎችን ምክር ተቀብለው በሰላም እጃቸውን ለመንግስት ጸጥታና ህግ አስከባሪዎች የሰጡና ወደፊትም የሚሰጡ ወጣቶች በወንጀል የሚጠረጠሩትን በመለየት ለፍትህ ሲያቀርብ በወንጀል ያልተጠረጠሩትን ደግሞ መንግሰት ፍላጎታቸውንና ችሎታቸውን መሰረት አድርጉ የጸጥታና የልማት ኃይል እንዲሆኑ የሚሰራ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
6. ህግና ሰላም በማሰከበር ሂደት በግርግር አጉል ህዝበኝነትን ለማትረፍ በሚንቀሳቀሱና መሃል ሰፋሪ በሆኑ አንዳንድ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሀይል አመራሮች ላይ መንግሰት እርምጃ እንደሚወስድ እንገልጻለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሚያዚያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም
ባህር ዳር