April 15, 2020
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/103542

ከሰሙነ ሕማማት ጋር በተያያዘ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት፥ “ኦርቶዶክስ የመለካውያን እንጂ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጠሪያ አይደለም” የሚሉ ተነሥተዋል። “ተዋሕዶ” መባል ነው በኋላ የመጣው፥ ከመለካውያን ለመለየት። ቤተ ክርስቲያናችንን በዕለት ከዕለት በግሪክኛው ኦርቶዶክስ የምንልበት ምክንያት የለንም። በቋንቋችን ተርጉመን ሠለስቱ ምእት “ርቱዓነ ሃይማኖት” እንደሚባሉ የኛንም ቤተ ክርስቲያን “ርትዕተ ሃይማኖት” እንላታለን። በግሪክኛ ኦርቶዶክስ እንደማንላት በግሪክኛ “ኤክሌሲያ” አንላትም። “ኤክሌሲያ” ቤተ ክርስቲያን የማለቱ ያህል፥ “ኦርቶዶክስም” ርትዕተ ሃይማኖት ማለት ነው።
ማንም ሰው ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቢገልጥ፥ መሪዎቿም ምእመናኗም ራሳቸውን “ርቱዓነ ሃይማኖት” ሲሉ ያያል። አንዳንድ መምህራንማ “ርቱዓ ሃይማኖት”ን መጠሪያ ስማቸው አድርገውታል። የአባ ጰንጠሌዎንን ታሪክ የጻፈልን “ርቱዓ ሃይማኖት” ነው። ሌላው መምህር ለበዓላት ምንባብ የሚሆኑ ድርሳናት ደርሶልናል። መጽሐፉን በስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት” እንለዋለን። ስለቤተ ክርስቲያናችን በውጪ ቋንቋ ስንጽፍ “ርቱዓ ሃይማኖት”ን ኦርቶዶክስ (Orthodox) ብለን እንመልሰዋለን። በቋንቋችን በምንጽፍበት ጊዜ ግን የውጪ ቃላትን የተቻለውን ያህል እንርቃለን።
ይልቅስ ኦርቶዶክስ መባል የማይገባቸው ኤፌሶን ጉባኤ ላይ ቅዱስ ቄርሎስ ያሳለፋትን ርትዕት ሃይማኖት ኬልቄዶን ላይ ሽረው ንጉሡን የተከተሉት ከነስማቸው ንጉሣውያን (መለካውያን) ናቸው። ርቱዓነ ሃይማኖት መሆናቸው እየታወቀ ለምን ኦርቶዶክስ እንደሚባሉ ግልጽ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ቢቸግራቸው፥ እነሱን Eatern Orthodox፥ እኛን Oriental Orthodox ይሉናል።