
1965 ዓም ነው። የባሕርዳር ሁለተኛ ደረጃ ተማሪወች አመጽ ላይ ነበርን። ትምህርትቤት በታህሳስ 19/1965 ዘግተን የጥላሁንን ሙት አመት ልናከብር ወጥተን አልተመለስንም። ያ የሆነበት የታሰሩ ወጣቶች ካልተፈቱ በሚል ሽምግልና ከፖሊስ አዛዥ ጋር ተቀምጠናል (የተማሪው መሪወች) ማለት ነው። በዚያ አጋጣሚም ብዙ የፖሊስ ድብደባ ስለነበር ወላጆች ገሚሶቹ መሳሪያም ይዘው የወጡ ነበሩ። መቸም መልካም ዘመን ነው እና የወላጅ ኮሚቴወች ከተማሪ መሪወች እና ከአስተዳደር በመነጋገር ከሁለት ሦስት ቀናት በኋላ እርቅ ሆኖ የሰርፀድንግል ሁለተኛ ደረጃ (ዛሬ ጣና ሀይቅ) ተማሪወች ተመለስን። መቸም የተማሪው ትግል ሲቀሰቀስ ስህን ወሎ፣ ፋሲለደስ ጎንደር፣ ሰርፀድንግል ባሕርዳር ግንባር ቀደሞች ነበሩ። እንደቀላል እንዳታዩት ትልቁን ዘውዳዊ ስርአት የተፈታተነ ትግል ስለነበር ማለቴ ነው። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ የነዚህ ጠቅላይ ግዛት አርበኞች ብዙ ቅሬታ ነበራቸው እናም ወላጅ ከልጁ ጎን ይቆም ነበር። የያንዘመን ወላጅ ብየ ስል የሁለተኛው የአለም ጦርነትን በድል አድራጊነት የተወጣ ባለ ግርማ ሞገሱ የኢትዮጵያ አርበኛ ማለቴ ነው። ሁላችንም ወይንም ብዙወቻችን ከአርበኛ ቤተሰብ የመጣን። ብዙ ጀብድ እና የሀገር ፍቅር ገድል የተነገረን። ብዙወቻችንም ቂም ቢጤ የቋጠርን። ለምሳሌ በጎጃም ንጉሠ ነገስቱ ዛሬ በታሪክ ያላቸውን ክብር ያክል ሳይሆን ሁሉም በየቤቱ ጥርስ የነከሰባቸው ሰው ነበሩ። የጎጃም እና የጎንደር አርበኞች ጠላትን ከሀገር ለማባረር ትልቁን ድርሻ ይዘው ሳለ ንጉሠ ነገስቱ በፍራቻ ብዙ አርበኞችን በማሰር፣ በግዞት በማግለል፣ ብሎም በመግደል። ከእስሩ፣ ከግዞቱ፣ ከሞቱ ያመለጡትን ደግሞ የሚገባውን ክብር ሳይሰጧቸው፤ ይባስ ብለው ባንዳ በመሾም አንገታቸውን አስደፍተዋቸው ስለነበር። ልጆች በእርሳቸው ላይ አመጽ ብናነሳ ድጋፍ እንጅ ተግሳጽ አልነበረብንም።
ለምሳሌ 1966 ይመስለኛል ደጃዝማች አበረ ይማም የሜጫው አርበኛ መሪ ለብዙ ዘመን በንጉሱ ታስረው ሊሞቱ ስል ተልቀው (በጣር ላይ በነበሩበት ሰአት) የቀብራቸው እለት የሰርፀድንግል ተማሪወች አምጸን ከፊሉ ወደቀብር ስንሄድ ያልገባቸው ወይንም ዜናው ያልተነገራቸው ተማሪወች ትምህርት ሳያቋርጡ ውለዋል። የሆነው ሆኖ አርበኛውን በደመቀ ቀረርቶ እና ፉከራ የቀብር ስነስርአት የተካፈልን ሊሰማን የሚችለውን ስሜት መግለጽ ክከባድ ነበር።
የሰሜን ጠቅላይ ግዛት ተማሪወች ሁሌም ለትግል ሲነሱ በይበልጥ ጎንደር እና ጎጃም አብሮ በመነሳት የትግሉ አጋር ወንድም እና እህት ነበሩ። በእርግጥም በተማሪው ትግል ብቻ ሳይሆን ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በጻፉት ግለታሪክ እንደሰፈረው የጎንደር እና የጎጃም አርበኞች በአንድ ቆመው ጠላትን መውጫ መግቢያ ያሳጡ ለሀገር ነጻነት መመለስም ጋሻ ሆነው በጋራ የቆሙ እንደነበር አትተዋል። ሁለቱን አርበኛ መለያየት አይቻልም ለዚያም ነው ጠላት በሌላ ያንሰራራውን ያህል በሁለቱ ጠቅላይ ግዛቶች የእግር መርገጫ መሬት አጥቶ የተባረረው።
በዚህ ታሪካዊ እና አካላዊ/ስጋዊ ቁርኝትም ይመስለኛል የዚያ ትውልድ የወጣት ትግል ሲቀሰቀስ ግንባር ቀደም ሆነው በተናጠል ሳይሆን በአንደት የቆሙት። ሌላው ከውጭ እንደሚሰበከው ሳይሆን በነዚህ ሁለት ጠቅላይ ግዛቶች የትግራይ፣ የኤርትራ የኦሮሞኛ ተናጋሪ ተማሪወች የቋንቋ ስብጥር እንደነበር በትግሉም በቀደመው የአርበኝነትም ሆነ በወጣት ተማሪ ትግል ዘመን አንዱ ከሌላው ሳይለያይ የታገሉ። ለሀገር ነጻነት በተደረገው የአርበኝነት ተጋድሎም ደማቸውን ያፈሰሱ ለዴሞክራሲ እኩልነት ሲባል በተደረገው ትግል በቀይ ሽብር መስዋ’እት የሆኑ ብዙ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖች የነበሩበት ነው። ይህ በመሆኑ የ66 አብዮት ከመቀስቀሱ አመት ቀደም ብሎ የባህርዳር እና ጎንደር ወጣት ማህበር ለመመስረት የተጠራው ስብሰባ በባህርዳር እስታዲዮም ተካሄዶ አንድ የወጣት አመራር ኮሚቴ መስርተን እንደተለያየን በትልቅ ትዝታ አስታውሳለሁ የእድሜ እኩዮቸም አሁንም ስለአሉ ይህን ጽሁፍ ያያሉ እና እውነታውን እነሱም በተሻለ ሊገልጹት ይችላሉ። ያ ማህበር የአብዮቱን የወጣት ትግል እስከመጨረሻ ባይመራውም መልክ እስኪይዝ ግን በጋራ ቆመው እንዲታገሉ አስተዋጸኦ ያበረከተ ነበር።
የዘረኛ ጎጥ/የህወሓት ልቃቂት ዘመን ታሪክስ?
ከላይ ያሳየሁትን እውነታ ዛሬ የህወሓት ሰራሽ ፖለቲካው እንደገለበጠው እና ወገን ከወገኑ አብሮ እንዳይቆም የተሳካ ስራ የተሰራበትን ሁኔታ እየታዘብን ነው። ከላይ ያሳየሁት የተማሪ አመጽ በተነሳበት ግዜ የአባቶቻችን/እናቶቻችን ከልጆቻቸው ጎን መቆም ታሪክን ዛሬ ወላጅ ከልጁ እንኳን አብሮ እንዳይቆም የህወሓት ፖለቲካ ሰርጾ ገብቶ አለያይቶታል። በዚህ በማህበራዊ ሚዲያ ሰውን በዘሩ፣ በጎጡ፣ በመንደሩ ብቻ ሳይሆን በእድሜ መለየቱም ሌላው ህወሓት ሰራሽ በሽታ አንድ አካል መሆኑን እናያለን። እናም በእውኑ አለም የእድሜ ተመክሮ፣ የእውቀት እና ልምድ ልውውጥ የትውልዶች የቅብብሎሽ መሰረት ሆኖ ሳለ ትውልዱን ከዚህ ሁሉ እንዲለይ እና ሌላውን እንዳያዳምጥ ልምድ እና እውቀትን እንዳይጋራም ተስርቶበታል ብል ስህተት አይሆንብኝም። በይበልጥ አሳፋሪው እና እጅግ ዘግናኝ ብሎም አደጋ ሆኖ የምናየው መንደርተኝነት ወርዶ ወርዶ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ እና ቀጣይነት ከባዱን መስዋ’እትነት የከፈሉ አርበኞችን፣ ነገስታቱን ሳይቀር ወደመንደር ፖለታካ የማስጠጋት አሳፋሪ ወንጅልንም ይንጸባረቃል (ወንጀል ይደገም)።
“አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” በፌስቡክ እና በመንደር ፖለቲካ የጦዙ ጀብደኞች ተነስተው ቴወድሮስን ያልሰጧቸው ስም የለም። ከዚህ ዘር ተወለደ ከዚያ በሚል ያየነው አሳፋሪ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ደግሞ ከኔ መንደር ነው የተወለደው የሚል ስናይ ቢያንስ የታሪክ ሊቃውንቱን ስራ እና ተግባር መዳጡ ባይከብዳቸው ስለተነሳሁለት ስለተባለው አቋም መናዳቸው ማፍረሳቸው መሆኑን ግለሰቦች እንዴት መገንዘብ ተሳናቸው? ይህ ነቀፌታ ይከብዳል ግን ተገቢ ነው እና ተቀበል—
እኔ ጎጃሜ ነኝ። ግን ሁልግዜ ጎንደሬነት ያኮራኛል ጎጃሜነት ያኮራኛል ምክንያቱም የኢትዮጵያዊነት ከሌሎች ጋር ተዳምሮ የአድነት ጋሻና መከታ ስለሆነ። ሌላው ነፍሴን በጥርሴ ይዠ በታገልሁበት በዚያ ቀውጢ ቀን ጎንደር መመኪያየ ነበር። በ1973 የወርሀ ነሀሴ መላኩ እና ገብረህይወት ጎንደር። ካሳየ አራጋው እና እሸቱ ጎጃምን ሲለበልቡት ጎንደር የገበሬ ልብስ ለብሸ መጠለያ የሰጡኝ በዚያ ጭንቅ ዘመን ጸጉረ ልውጥ ማስጠጋት ፍርዱ ጥይት በነበረበት እቤታቸውን እንድጠለልበት እንዳልሞት ያደረጉት እናት ምንግዜም አይረሳኝም። በትግሉም የጎንደር እና ጎጃም ቀበሌወች ቋራ፣ በለሳ፣ አርማጭሆ፣ ወልቃይት ጸለምት። በኋላም አቸፈር፣ ዝብስት፣ በላያ፣ መተከል አገው ምድር በኢሕአሠ/ኢሕአፓ በሰራዊት የተደረገው እንቅስቃሴ እና የአንድነት አብሮነት የተጋድሎ ታሪክ እንዴት በህወሓታውያን ፍልስፍና መንደርተኝነት ሊፋቅ ይቻለዋል? ጎበዝ አደብ መግዛት ይገባል። ወንድም ከወንድሙ የማለያየት ፖለቲካ የመጨረሻው ለሰሪው የሚከፋ እና አጥፊው ይሆናል። ይህን ፖለቲካ የሚያራምዱ በገዥ ፓርቲ እንደፖለሲ የሚሰሩት ሲሆን። የእነርሱ ቫይረስ ተሸካሚ የሆኑ በስም ተቃዋሚ፣ በገቢር ግን ህወሓታውያን እና የስርአቱ ደመወዝተኞች መሆናቸው ልንገነዘበው ይገባል። ይህን የጎጠኝነት በሽታ ሁላችንም ፊት ለፊት ካልገጠምነው ወደፊት ሊያስከትል የሚችለው አደጋን መገመት ከባድ ነው። እንዳልሁት ዜጋን በመንደሩ ከለያየው በኋላ የሚቀረው ለጠላት እጅን ለፊጥኝ አስሮ መነዳት ብቻ ነው! በየትኛውም መልክ የህወሓት/ኦነግን ፖለቲካ እና ዘረኝነት ጎጠኝነትን ልንታገል ሀገርን ከእንዲህ ያለ ክፉ ደዌ ነጻ ልናወጣ ይጠበቃል። ስለ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ስለ የህወሓት አፍራሽነት እያወራን በጓዳ በር አጥፊ ህወሓታዊ ፖለቲካን መፍቀድ ለማንም አይበጅም፡ይቁም። ሁላችንም ልንታገለው ግድ ይለናል። ከየትኛውም የሀገራችን ክፍል ይምጣ ወይንም ማንም ይሁን ይህን ፖለቲካ ያነገበ ሁሉ ሰይጣናዊ አላማ እንደያዘ ልናሳይ ልንታገል ግድ ይላል፤ ሀገርን፣ ወገንን፣አስታውሱ ህወሓት እና ኦነግ ሻብያ ሲነሱ እና ምክንያታዊ አላማ ብለው ፕሮግራም ሲነድፉ አማራ ጠላቴ ነው በሚል ነበር። ያ የዘረኝነት ደዌ ዛሬም ሊለቃቸው አልቻለም አይናቸው እያየ ሲሰምጡ እንኳን የአቋም ለውጥ አላሳዩም። ዘረኝነት ደዌ ነው። ጎጠኝነት ደዌ ነው መድሀኒት ይፈልጋል አለያም እንዳይጠጋ ቀድሞ መከላከል ይኖርብናል ወገንን ዜጋን ከጥፋት እና ከእርስ በእርስ መበላላት ለማትረፍ ከታሰበ አጥብቀን ልንጠየፈው እና ልንታገለው ግድ ይለናል።፡ስለወልቃይት፣ ስለእራያ፣ ስለ መተከል እየጮኸ የግፍ ሰሪወችን ተግባር የሚደግም ወገኑን ለባርነት ለፊጥኝ አስሮ አብሮነትን አለያይቶ ለጠላት የሚሰራ ደመኛ ነው ሁላችንም ወጊድ ልንለው ይገባል።