ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አገዛዙ የአማራ ክልል በሚለው በፋኖ/አርበኞችና በገበሬው ላይ እየወሰደው ያለውን ፀረ አማራ እርምጃ ኢሳትና ቪኦኤ ሳይቀሩ አገዛዙ እንዲዘገብ ከሚፈልገው በላይ እውነታ ላይ ባልተመረኮዘና ፈጽሞ ሚዛናዊነትን ባልጠበቀ መልኩ አዛብተው በመዘገብ አገዛዙን እየደገፉ ይገኛሉ!!!
ኢሳትስ እሽ ከነ ጋዜጠኞቹ ለአገዛዙ ስለተሸጠ በተለይ ተመልሶ ቀመጣ በኋላ በዜና ዘገባውና በዕለታዊ ውይይቱ እያደረገ እንዳለው ኢቴቪ፣ ፋናና ዋልታ እንኳ ሊዘግቡበት ፈጽሞ በማይደፍሩትና በማይሞክሩት ደረጃ አገዛዙን ተጠቃሚ ለማድረግ እውነታን ሆን ብሎ ባዛባና የጋዜጠኝነትን መርሕ ማለትም ሚዛናዊነትን ፈጽሞ ባልጠበቀ መልኩ ቢዘግቡና ቢያወሩ ላይገርም ይችላል!!!
የቪኦኤ እንዲህ መሆን ግን አይገባምም??? ቪኦኤን መከታተል ካቆምኩ ቆይቸ ነበር፡፡ ለውጥ እያለ የሌለ ለውጥ እያራገበ ተጨባጩን እውነታ እያዛባ መዘገብ ሲጀምር ነበር ያቆምኩት፡፡ አሁን ተመልሸ ማዳመጥ ስጀምር ቅኝቱ ከጠበኩትም በላይ በጣም ተለዋውጦ ፍጹም የአገዛዙ ተለጣፊ ሆኖ ነው ያገኘሁት!!!
ጽዮን ግርማ ሰኞ ለታ በፋኖ ላይ እየተወሰደ ስላለው የግፍ እርምጃ ፍጹም ሚዛናዊነት በጎደለውና እውነታን ባዛባ ደረጃ አገዛዙን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ዘግባ ዝግጅቷን አቅርባ ነበር፡፡ ከፋኖ ወገን ያለውን እውነት ሰው አቅርባም ሆነ ከሚናገሩት ጠቅሳ ዘገባዋን ሚዛናዊ ለማድረግ ፈጽሞ አልፈለገችም!!!
አገዛዙ በዚህ መልኩ ከራሱ ውጭ ያሉትን የብዙኃን መገናኛዎችን ገዝቶ እውነቱን በማፈንና በማዛባት የግፍ ሰለባው ሕዝብ ድምፅ እንዳይሰማ አድርጎ ፀረ አማራ ዘመቻውን ለማጠናቀቅ አስቀድሞ በሚገባ የተዘጋጀበት መሆኑን እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ደባ በሚገባ መረዳት ይቻላል!!!
ማንም ነጻና አመዛዛኝ ጭንቅላት ያለው ዜጋና ጋዜጠኛ ከሆነም ለሞያዊ ሥነምግባሩ ተገዥ የሆነ ሁሉ በምንም ተአምር ቢሆን በፋኖ ጉዳይ ያለው እውነታ ሊሰወረው አይችልም፡፡ ከአገዛዙ የተምታታ መግለጫና ከሰለባዎቹ ድምፅ እውነቱን ፈጦ ያገኙታልና!!!
አገዛዙ ፋኖ/አርበኞችን በተመለከተ ሲናገር ዘመቻው “ወንጀል ሠርተዋል!” የሚላቸውን ብቻ እንደሚመለከት ይናገርና በሌላ በኩል ደግሞ እንዳለ የፋኖ/አርበኞችን አደረጃጀት “ኢመደበኛ ነው ስለሆነም በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር መካተት አለበት ካልሆነ ግን መፍረስ አለበት!” የሚል የጸና አቋም ይዞ ይሄንን አቋሙን ተፈጻሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ ጭንቅላት አለኝ የሚል ሰው አይደለም ለማንም ተራ ሰው በዚህ የአገዛዙ አንደበት ቁልጭ ብሎ የተረገረው እውነት አይሳተውም፡፡ አገዛዙ ወንጀልን ሽፋን ያድርግ እንጅ በፋኖ/አርበኛ ላይ የዘመተው ፋኖ/አርበኛ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ በአገዛዙ መዋቅር ለመታቀፍ ስላልፈቀደ ነው!!!
ፋኖ/አርበኞች “በሀገር መከላከያ ስምም ይሁን በሕገወጡ ልዩ ኃይል አደረጃጀት ያለው የጸጥታ አካል አወቃቀር የምንቃወመውና የምንታገለው የፀረ አማራው አገዛዝና የፀረ አማራው ሕገመንግሥት ጠባቂና ዘበኞች ሆነው የተዋቀሩ በመሆናቸው የእነዚህ የጸጥታ አካላት አባል ልንሆን አንችልም!” የሚል ትክክለኛ መርሕ ተኮር ጥያቄ አንሥተው የአገዛዙን “ተካተቱ!” የሚል ጥያቄ ውድቅ በማድረጋቸው መዝመቱ ግልጽ ነው!!! አገዛዙ በመግለጫው ላይ ፋኖ/አርበኛ ወደ ፀጥታ መዋቅሩ እንዲታቀፉ ያቀረበላቸውን አማራጭ ውድቅ እንዳደረጉት መግለጹ ይታወሳል!!!
ጋዜጠኛም ሆነ ሌላ ይሄንን ልብ ማለት ወይም መረዳት የሚችል ማንኛውም ሰው ሁሉ አገዛዙ የፋኖ/አርበኞችን አቋም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በፋኖ/አርበኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲመቸው አስቀድሞ ስማቸውን ለማጥፋት ሆን ብሎ የራሱን የጸጥታ አካላት እያሰማራ “ፋኖ ነን!” እያስባለ ሲያስፈጽማቸው የቆያቸውን ወንጀሎች እየጠቀሰና እየገለጸ በዚህ ወንጀል ምክንያት በፋኖ/አርበኞች ላይ እንደዘመተ የሚናገረው ነገር ሽፋን መሆኑን መረዳት መገንዘብ ሊሳነው አይችልም ለአገዛዙ ተገዝቶ ካልሆነ በስተቀር!!!
ለማንኛውም ቪኦኤም ሆነ ኢሳት በዚህ አሳፋሪ ተግባራቸው የሚያፍሩበት ቀን ሩቅ አይሆኑም!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው