ሀብታሙ ግርማ ደምሴ
(በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር፤ ኢ–ሜይል፦
ruhe215@gmail.com)
መግቢያ
ይህችን ጽሑፍ ለማዘጋጀቴ ምክንያቱ የህወሃቱ አፈ–ቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ባደረገው ቃለምልል ላይ አስመልክቶ የግል እይታዬን ባሰፈርኩበት አንድ የማህበራዊ ድረ ገጽ (Facebook) ጽሑፌ ላይ የማከብረው ጓደኛዬና የሥራ ባልደረባዬ ተፈራ ተክሌ የሰጠው አስተያየት ነው።
ለዚህኛው ጽሑፌ ጭብጥ መነሻው የቀደመው ጽሑፌ በመሆኑ አንባቢ መነሻ ሃሳብ ይይዝ ዘንድ ከዚህ በታች ባለው ሊንክ ሊያገኘው ይችላል።
ህወሃት እና ግራ የመጋባት ፖለቲካው
ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በተለይ፣ ህወሃት በከፍተኛ የፖለቲካ ግራ መጋባት ህመም እየማቀቀ ነው። የዚህች ጽሑፍ ጭብጥ ህወሃት የገባበትን የፖለቲካ ቅርቃር በደበበ ሰይፉ ዝነኛዋ ግጥም -‘ለምን ሞተ ቢሉ’ – መነሻ (ዳራ) እና ይዘት መግለጽ ነው፤ አላማዬም ህወሃት ከገጠመው የፖለቲካ ግራ መጋባት ችግር ይወጣ ዘንድ ምክር ቢጤ ለመስጠት ነው፤ የጽሑፉ መንፈስ ግልብ ተቃውሞ ወይም ጭፍን ጥላቻ ሳይሆን የግል አስተሳሰብን በቅንነት እና በነጻነት መግለጽ ብቻ እና ብቻ ነው።
በእኔ ግንዛቤ ህወሃት የገባበትን የፖለቲካ ቅርቃር እና ከዚህ የመውጫ ቀዳዳ በደበበ ሰይፉ ግጥም መነሻ (ዳራ) ውስጥ እናገኘዋለን።
ኮሚኒስቱ ደበበ ሰይፉ
እንደሚታወቀው ደበበ ሰይፉ በህይወት ሳለ ብዙ በደል ደርሶበት ነበር፣ በተለይም ረጅም አመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢያስተምርም ጡረታውን እንኳ አላገኘም ። (የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እንደሚናገሩት ደበበ ጡረታ ያልተከበረለት የመንግስት አሰራር በሚያዘው መሰረት የአስተዳደር ኃላፊ ሆኖ በሰራበት ዓመታት በስሙ ተመዝግቦ የወሰዳቸውን የህዝብ ንብረት ለመመለስ ፍቃደኛ ስላልነበረ ነው ይላሉ።)
የሆነው ሆኖ ደበበ ብሶተኛ አልነበረም፤ በበደሉት ሰዎች ላይ አላቄመም፤ ምናልባት በህይወቱ ጉዞ አንዳንድ ቅሬታዎች ቢኖሩትም ለጥፋቶቹ የእርሱ ድርሻ እንደነበረበት ያመነ ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ ደበበ ‘በዳዮቹን’ ከመውቀስ፣ በእነርሱ ላይ ከመዛት ይልቅ ወደራሱ ተመለከተ፤ እናም ከራሱ ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ተማከረ፤ የምክክሩ ውጤት ይህ ነበር፦
‘……እኔ አንድ ሰው ነኝ፣ የማምንበት ሃሳብ አለኝ ነገር ግን የእኔ አስተሳሰብ ዘመኑን እንዲዋጅ ተጽዕኖ ፈጥሬ ዘመኑን መቀየር አልችልም፤ የማላሸንፈውን ጨዋታ አልጫወትም፤ አንድ ምርጫ ነው ያለኝ፣ ወይ በአቋሜ መሞት አልያም አቋሜን ቀይሬ ዘመኑን መስሎ መኖር።’
በነገራችን ላይ ደበበ Old Communist ወይም ወግ አጥባቂ ኮሚኒስት የሚባል አይነት ሰው ነበር፤ እርሱ ከኮሚኒስት አስተሳሰብ ውጭ ሌላውን ለመቀበል ቀርቶ መስማት የማይፈልግ አክራሪ ማርክሲስት–ሌኒኒስት ነው።
ደበበ ኮሚኒስት እንደመሆኑ በዚህ ርዕዮት የተጠመቀ ሰው አንዱ መገለጫ ደግሞ ሃሳብን ከዘመን ጋር ማስተካከል አለመቻሉ ነው፤ኮሚኒዝም ለተከታዮቹ እኮ ሃይማኖት ማለት ነው፤ በሃይማኖት መንገድ ደግሞ ለእምነት መሞት ጽድቅ ነው፤ ደበበ ለኮሚኒዝም ሲል ከዘመኑ ጋር ተኳረፈ፤ እናም የዘመን ኩርፊያው ጠንቶበት ሞተ።
እንግዲህ ደበበ ለእምነቱ ሲል ከዘመን መጣላት ነበረበት፤ ከዘመን መጣላት የማያሸንፉት ጨዋታ መሆኑ ገብቶታል፤ የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም የሚለውን አገረኛ አባባል ደበበ ተቀብሎታል፤ በመሆኑም ለእምነቱ ቀናኢ ስለነበር ዘመኑን ከመምሰል ይልቅ ሞቱን መረጠ።
ደበበ የዘመን (የጊዜን) አሸናፊነትን ተቀብሎ፣ ነገር ግን በአቋሙ መጽናቱን ባንድ የገለጸበትን ‘….ለምን ሞተ ቢሉ..’ ግጥሙን ጻፈ፤ ይህ ግጥም በደበበ ሰይፉ ሃውልት ላይ ተቀርጿል።
የእነ ጌታቸው ረዳ ፓርቲ ህወሃት እና ደበበ ሰይፉ ምንና ምን ናቸው?
አንድነታቸው ሁለቱም ኮሚኒስቶች ናቸው፤ በኮሚኒስት አስተሳሰባቸው ምክንያት እናምንበታለን ከሚሉት ሃሳብ ውጪ ሌላን ሃሳብ የመስማት ፍላጎት የላቸውም፤
ነገር ግን ደበበ ሰይፉ እና ህወሃት አንድ መሰረታዊ ልዩነት አላቸው።
ደበበ ከአቋሙና ከዘመን መታረቅ አንዱን መርጧል፤ እንደ ግለሰብ ለቆመ ሰው ይህን መምረጥ ይችላል፤ የደበበ ምርጫ አቋሙ ነበር፤ ለዚህ ደግሞ የሚከፈለውን ለመክፈል ፈቃደኝነቱ ነበረው፤ እንደሚሸነፍ ቢያውቀውም ምርጫው ነበር።
እነ ጌታቸው ረዳ ግን ሁለት ወደዱ፤ አንዱ የህይወት ህግ መምረጥ መሆኑን ዘነጉት፤ ከምንም በላይ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ረሱትና የግል አቋማቸውን በግድ የህዝብ ለማድረግ ሞከሩ፣ እየጣሩም ነው።
ነገር ግን ህዝቡ የሚፈልገው ሌላ እነርሱ የሚሉት ሌላ፤ በመሰረቱ በግል አቋም አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተቀብሎ መኖር ይቻላል፣ ነገር ግን ዛሬ ላይ አንደ ፖለቲከኛና እንደድርጅት በዚህ ሃሳብ ቢያንስ ኢትዮጵያን መምራት አይቻልም።
ፖለቲካ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የራስን ሃሳብ እና ምቾት መስዋዕት መሆንን ይጠይቃል፤ ስለሆነም ቢቻል ራስን ከዘመኑ ጋር አርቆ (አስታርቆ) የፖለቲካ መስመርን መቀየር ነው።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ለጌታቸው ረዳ እና ጓዶቹ ይህ አይቻልም፤ በማርክሲዝም–ሌኒኒዝም አስተምህሮ ሃሳብ መቀየር (ከዘመን ጋር ማስታረቅ) አይቻልም፤ ይህን ማድረግ አድሃሪነትነት (reactionary) ነው።
በመጨረሻም ……..
በመጨረሻም አንድ የሚገርመኝ/የሚያሳዝነኝን ነገር ለአንባቢ ላካፍል፤ ይህም በህወሃት ቤት አንድ መካሪ መጥፉቱ እና/ወይም ምክር የሚሰማ አለመኖሩ ነው። በእኔ እምነት ነፍሱን ይማረውና መለስ ዜናዊ በህይወት ቢኖር ኖሮ አሁን ዶ/ር አብይ የሚመሩትን ለውጥ ያህል እንኳ ባያመጣ፣ ነገር ግን ቢያንስ አብዮት እንዳይነሳ (እና ህወሃት እንዳይወርድ) የሚያስችል መለስተኛ ለውጥ አድርጎ ድርጅቱን ይታደግ ነበር። እነ ጌታቸው ረዳ ግን በተበላ እቁብ ማልቀስ አላቆሙም፤ time out እንደሆነባቸው አልተረዱም።
እኔም የህወሃት የፖለቲካ ግራ መጋባትን በደበበ ሰይፉ ግጥም አማካኝነት ለማሳየት ያደረግሁት ጥረት ህወሃቶች ደበበ ሰይፉ እንዳደረገው ወይ እምነታቸውን ወይም ጊዜውን እንዲመስሉ፣ ሁለት ወዶ እንደማይኖር፣ በተለይም ከዘመን ጋር መጣላት ለመሞት መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።