የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፀጥታ ምክር ቤት በቅማንት ብሔረሰብ ወረዳዎች በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ፡፡የተከበራችሁ የቅማንት ሕዝቦች፡-በዞናችን የሚገኙ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ለረጅም ዓመታት ተቆራኝተውና ተሳስረው የኖሩ የተጋቡ፣ የተዋለዱ፣ የተዛመዱ ክፉውንም ደጉንም ዘመን አብረው በጋራ ያሳለፉ ሕዝቦች ናቸው፡፡በሀገራችን እኩልነት እንዲሰፍን፣ ሠላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ከሌሎች የክልላችንና የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በመሆን ይህ ለውጥ እንዲመጣ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ለውጡንም በግንባር ቀደምነት ደግፈዋል፤ ነገር ግን ከለውጡ ማግስት ከቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በርካታ ፈተናዎችና ችግሮች አሳልፈናል፡፡ እነዚህ ፈተናዎችና ችግሮችም ለበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፍ፣ ንብረት መውደም፣ አካል መጉደል፣ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከቀያቸው መፈናቀል እና ሰፊ የሥነ-ልቦና ጫናም አድርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ በአካባቢው የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት ደርሷል፡፡በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥትና የዞናችን ሠላም ወዳዱን ሕዝብ ማዕከል በማድረግ ከመንግሥት አመራሮች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ጋር በጋራ በመሆን በጭልጋ፣ በአይከልና በላይ አርማጭሆ የነበረውን የሠላም እጦት፣ ሕገ-ወጥነትና አለመረጋጋት ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ከወስጥም ከውጭም የተጠነሰሰውን ሴራ ከምንጩ እንዲደርቅ ብስለት የተሞላበት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለዚህም ስኬት መንግሥትና ጥምር ኮሚቴው የመግባቢያ ነጥቦችን በጋራ በማውጣትና መግባባት በመድረስ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ ለምሳሌ፡- በተፈጠረው ችግር ምክንያት በነፍስ ግድያ ወንጀል ከተጠረጠረ ግለሰብ ውጭ በተለያየ ምክንያት የታሰሩ እንዲፈቱ ተደርጓል፣ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና መልሶ የማቋቋም ሥራ ተሠርቷል፤ እየተሠራም ይገኛል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የመንግሥት መደበኛ ሥራዎችና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል፤ ብሔረሰብ ዞኑን ራሱን አስችሎ ለማቋቋም ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተሰሩ በርካታ ሥራዎችም በአካባቢው የሚኖሩ የቅማንትና የአማራ ሕዝቦች ማኅበራዊ ትስስራቸውን ይበልጥ በማጠናከር ከውስጥና ከውጪ የተቃጡ የጥፋት አጀንዳዎችን በማምከን አንድነታቸውንና የታላቅነታቸውን ከፍታ ማሳየት ችለዋል፡፡ይሁን እንጅ በአካባቢው በተገኘው ሠላምና መረጋጋት፤ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ጥቅማቸው የተነካባቸው ጥቂት የተደራጁ ቡድኖች በላይ አርማጭሆ ወረዳ – በሮቢት ቀበሌና አካባቢው፣ በአይከል ከተማ አስተዳደር፣ በብሔሩ ጭልጋ ወረዳ – በጮንጮቅና አካባቢው እንዲሁም በነባሩ ጭልጋ ወረዳ – በጫንድባ ቀበሌ አካባቢ፣ በጎንደር ከተማ – ወለቃ፣ ቁስቋምና አርባባ አካባቢዎች በርካታ ኢ-ሰብዓዊና ሌሎች ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ይገኛል፡፡ ሰዎችን መጥለፍ፣ ሰው መግደል፣ የመንግሥት ስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች እንዳይካሄዱ መከልከል፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እንዳይሳኩ ማደናቀፍ፣ በየደረጃው በሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ግድያ መፈፀም፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ማዛወር፣ ታጥቆና ተደራጅቶ መቀስቀስ፣ የተደራጀ ዘረፋና ሥርቆት መፈፀም፣ ጥይት በመተኮስ ሕዝቡን ማሸበር፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሕዝቡንና ባለሀብቶችን የገንዘብ ቅጣት መፈፀም በአጠቃላይ ሕገ-ወጥ መረቡን በማስፋት በአካባቢው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ወንጀል በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡በአጠቃላይ ይህ ሕገ-ወጥ ድርጊት እጅግ ከተከበረው የቅማንት ሕዝብ ባህልና ወግ ያፈነገጠ አስነዋሪ ተግባር ከመሆኑም በላይ የአማራና የቅማንት ሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚሸረሽር እኩይ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡የተከበራቹሁ የቅማንት ሕዝብ ሆይ፡-መንግሥትና የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ኮሚቴ በጋራ በሠራናቸው ሥራዎች በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለናል፡፡ በሠላምና ማረጋጋት፣ የታገቱ ሰዎችን በማስለቀቅ፣ የተዘረፋ ንብረቶችን በማስመለስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ፣ የመንግሥት ሠራተኛውን ወደ ሥራ በመመለስ፣ ሕገ ወጥ ቡድኑ ሠላማዊ መንገድ እንዲመርጥ የውይይት መድረኮችን በጋራና በተናጠል በማዘጋጀት በመምከርና በመገሰፅ፤ በአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የብሔረሰቡ ኮሚቴ ከመንግሥት ጐን በመሆን አኩሪ ሥራ እየፈፀመ ይገኛል፡፡መንግሥትና የብሔረሰቡ ኮሚቴ አባላት የቅማንት ብሔረሰብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ባለፋት ወራት እጅግ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡የክልሉ፣ የፌዴራልና በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር እንደከዚህ በፊቱ መሠዋዕትነት እየከፈሉ ከሕዝቡ ጐን በመሆን ቀጠናውን ከተደራጀው ፅንፈኛ ቡድን በማፅዳትና ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በተግባር እና በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ሆኖም ካሁን በፊት በጋራ ባካሄድናቸው የውይይት መድረኮች መረዳት እንደቻልነው በሕገ-ወጥ መንገድ የተደራጀው ዘራፊ እና ሕገ ወጥ ቡድን በዞናችን ብሎም በአካባቢያችን የተገኘውን ሠላምና መረጋጋት ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለመቀየር የብሔር ሽፋን በማስያዝ ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር ግንባር ፈጥሮ የሚችለውን ያህል እየሠራ ይገኛል፡፡መንግሥት ባለፉት ከታዩት የሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀሎች፣ የሠላም እጦቶችና የኢኮኖሚ ቀውሶች በቂ ትምህርት ተወስዶባቸው ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ከመሆኑም በላይ የአማራና የቅማንት ሕዝቦችን አብሮነት፣ አንድነት፣ ሠላምና መተባበር ለማጠናከር በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠራ ይገኛል፡፡የተከበራቹሁ የቅማንት ህዝብ፡-የተከበረውን የቅማንት ሕዝብና የብሔረሰቡን ኮሚቴ የማይወክሉ የብሐየር ሽፋን ይዞ በመንቀሳቀስ በአካባቢውና በሌሎች ሕዝቦች ላይ የሰው ሕይወት በማጥፋት፣ የተደራጀ ሌብነት፣ የገንዘብ ቅጣት፣ ዜጎችን በማንነታቸው የማጥቃት የመሳሰሉትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ፈፅመዋል፤ በመፈፀም ላይም ናቸው፡፡ ስለሆነም መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጡ ምክንያት የገቢ ምንጩ እየደረቀበት ያለው ፅንፈኛ ቡድን ሌሎች አዳዲስ የጥፋት ታክቲኮችን እየተከተለ አካባቢውን ወደ ዘላቂ ትርምስ ለማስገባት ሌት እና ቀን እየሠራ መሆኑን የአካባቢው ሕዝብ ሊገነዘበው ይገባል፡፡የተከበራችሁ ሠላም ወዳዱ የቅማንት ሕዝቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የቅማንት ኮሚቴ አባላት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ክብራንና ክቡራት፡-በዞናችን በሚገኙ በብሔረሰቡ ጭልጋ ወረዳ – በጮንጮቅና አካባቢው፣ አይከል ከተማ አስተዳደር፣ በነባሩ ጭልጋ – በጫንድባና አካባቢው፣ በነጋዴ ባሕርና አካባቢው፣ በላይ አርማጭሆ – በሮቢትና አካባቢው እና በጎንደር ከተማ – ወለቃ፣ ቁስቋም፣ አርባባና አካባቢው እና በጎንደር ዙሪያ ወረዳ – በዳዋ ዳሞት ቀበሌና አካባቢው በሚገኙ ሕገ-ወጥ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴውን ለማምከንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚከተሉት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡1. በአሁኑ ወቅት የአካባቢውን ሠላም፣ ልማትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጐን ተሰልፎ መልካም ሥራ እየሠራ ለሚገኘው የብሔረሰቡ ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ አክብሮትና ምሥጋና ያለን መሆኑን ተረድታችሁ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ከጐናችን እንድትሆኑ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡2. ሕጋዊ ከሆነውና በመንግሥት ዕውቅና ከተሰጠው የቅማንት ብሔረሰብ ኮሚቴ ውጭ ብሔረሰቡንና ኮሚቴውን እንደሽፋን በመጠቀም በሕይወት ማጥፋት፣ በሰዎች እገታ፣ በገንዘብ ቅጣት፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በጥይት ተኩስ በተደራጀ ሥርቆት፣ ዜጐችን በማፈናቀል በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ የፀጥታ መዋቅሩ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡3. በአኩሪ ታሪካቹሁ፣ አንድነታችሁና አብሮነታቹሁ ዘመን የማይቀይራቹሁ እጅግ ለተወደዳቹሁና ለተከበራቹሁ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች የምናቀርበው ጥሪ ያለፉትን ክፋቶችና በደሎች በይቅርታ በማለፍ መጪውን ብሩህ ተስፋ ለልጆቻችን እንድናወርስ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡4. ከወረዳ – ወረዳ፣ ከቀበሌ – ቀበሌ የጦር መሣሪያ ይዞ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብ ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣሰ መሆኑ ታውቆ መሣሪያውን የማስወረድ ሥራ ይፈፀማል፡፡5. ለሀገራችን፣ ለክልላችንና ብሎም ለዞናችን ኢኮኖሚያዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሚያበረክቱ ዓለም አቀፍ መንገዶች ከጎንደር – መተማ እና ከጎንደር – ሰሮቃ መስመር ላይ የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማስቆምና ለማስተጓጐል በሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካላት ላይ ጥብቅ ርምጃ ይወስዳል፡፡6. የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም መንግሥትና ሕዝቡ የሚያደርጉትን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደናቅፍና በተፈናቃዮች ላይ የሥነ ልቦና ጫና በሚያሳድር ማንኛውም ግለሰብ ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡7. በዞናችን ውስጥ በማንኛውም ወረዳና ቀበሌ በዜጐች ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅኖ በሚያሳድር የጥፋት ኃይል ላይ ሕጋዊ ርምጃ ይወስዳል፡፡8. በመኸር የግብርና ምርታችን ለማሳደግና የዜጐችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በግብዓት አቅርቦት ዝውውርና የግብርና እርሻ ሥራውን ማደናቀፍ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡9. የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት የኑሮ ውድነቱን በሚያባብሱና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ ይወስዳል፡፡10. በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ወረዳዎች በሕገ-ወጥ መንገድ በተናጠልና በቡድን ተደራጅቶ በሕዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለ ግለሰብ ወይም ቡድን ለመንግሥት እስከ ሚያዝያ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ በዞንና በወረዳ ደረጃ በሚገኙ የፀጥታ ተቋማት በመገኘት እጁን እንዲሰጥ እየገለጽን ይህን ሕጋዊና ሠላማዊ አማራጭ አልቀበልም ባለው ሕገ-ወጥ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ በደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራውን በተደራጀና በውጤታማነት የሚፈፅም መሆኑ ታውቆ ሠላም ወዳዱ የቅማንት ሕዝብ ከፀጥታ መዋቅሩ ጐን እንድትሰለፉ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡የተወደዳቹሁና የተከበራቹህ የዞናችን ሕዝቦችሁላችሁም እንደምትገነዘቡት ባለፋት ዓመታት በዞናችን በተከሰቱ የሠላምና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የአካባቢያችን ልማት፣ ሠላምና የቱሪስት እንቅስቃሴ በእጅጉ ተጐድቶ ሕዝባችን ለከፍተኛ የሠላም እጦትና ሥራ አጥነት ተጋልጦ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ከለውጥ ማግስት የተደራጀው የመንግሥት መዋቅር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ቢንቀሰቀስም ችግሮቹ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡና ስፋት ያላቸው በመሆኑ በዚህ ወቅት የዞናችንና ብሎም የክልላችን ሕዝብ በእጅጉ እየተፈታተነ ያለውን የሠላም እጦት ለመፍታትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሕዝቡ፣ ከወጣቱና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እንገኛለን፡፡ስለሆነም የዞናችን ሕዝቦች በየአካባቢው በተደራጁ ሕገ-ወጥ ቡድኖችና ግለሰቦች እየደረሱት ያሉትን አስከፊ የሠላምና የፍትሕ እጦት፣ ሥራ አጥነትና ድህነት ምን ያህል ከጊዜ ጊዜ እየሰፋ የአካባቢያችን ሠላምና ልማት እየጐዳው ያለ መሆኑን ተገንዝባቹሁ እንደካሁን ቀደሙ ከመንግሥትና ከፀጥታ ኃይሉ ጐን በመሰለፍ ዞናችንና አካባቢያችን ከሕገ-ወጦች ትርምስ ነፃ እንድናወጣው ጥሪያችን እናቀርብልሃለን፡፡በተጨማሪም በዓለም አቀፍና በአገራችን ከፍተኛ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመከላከል የሃይማኖት አባቶችና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር መስማትና መንግሥት ያወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ራሳችንና ሕዝባችንን ከወረርሽኙ እንድንጠብቅ ጥሪያችን በድጋሜ እናስተላልፋለን፡፡“የዞናችንና የአካባቢያችን ሕዝቦች እንኳን ለትንሳኤ ዋዜማ አደረሳቹሁ”ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ምየማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፀጥታ ምክር ቤት
የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ – እዚህ ላይ ይጫኑ