
አፍሪካ ቀጣይዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘ ማዕከል ልትሆን ትችላለች ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ አንዳንድ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ታይቷል።
በአፍሪካ እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ወደ 18000 ሰዎች ገደማ ሲኖሩ ከእነዚህ መካከል ወደ 1000 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። በርግጥ ይህ ቁጥር በአሜሪካና በአውሮፓ ከታዩት አንፃር አነስተኛ መሆኑ ነው የተነገረው።
የዓለም ጤና ድርጀት ቫይረሱ በአፍሪካ በዋና ከተሞች ብቻ ተወስኖ አልተቀመጠም ብሏል። አክሎም አህጉሪቱ በሽታው ለጠናባቸው ታማሚዎች ለመተንፈስን የሚያግዙ በቂ መሳሪያዎች የሏትም።
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማቲዲሶ ሞይቲ ለቢቢሲ እንዳሉት ድርጅታቸው ቫይረሱ ከዋና ከተሞች ወደ ክልል ከተሞች እየተስፋፋ መሆኑን ገምግሟል። በደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ አይቮሪኮስት፣ ካሜሮንና ጋና ከከተማ በራቁ ስፍራዎች ቫይረሱ መሰራጨቱን ገልፀዋል።
አክለውም የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው መከላከል ላይ ማተኮራቸውን ይናገራሉ።
“የጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ሕሙማንን ቁጥር ለመቀነስ እየሰራን ነው፤ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት የህክምና ክፍሎች በበርካታ የአፍሪካ አገራት በበቂ እንደማይገኙ እናውቃለን” ብለዋል።
“አህጉሪቱ ከምትጋፈጣቸው ነገሮች መካከል ቀዳሚው የቬንትሌተሮች እጥረት መሆኑን መናገር እችላለሁ” ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ለታመሙ ሰዎች ቬንትሌተር የማግኘት ጉዳይ የሞትና የሕይወት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ መሳሪያ በጽኑ ታመው በራሳቸው መተንፈስ ለተቸገሩ ህሙማን ወደ ሳንባቸው ኦክስጅን በማድረስና ካርቦን ዳይኦክሳይድን በማስወጣት ቁልፍ ሚና አለው።
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከሞቱ ሰዎች መካከል ቀዳሚው ዚምቧቤያዊው ጋዜጠኛ ሲሆን በወቅቱ በዋና ከተማዋ ሐራሬ የሚገኙ ባለስልጣናት እርሱን ለማከም ቬንትሌተር እንዳልነበራቸው ተናግረው ነበር።
በአፍሪካ ሌላው ቫይረሱ በስፋት ይሰራጭባቸዋል ተብሎ ከተሰጉ ስፍራዎች መካከል አንዱ ከፍተኛ ጥግግት ያለባቸው ቦታዎች ሲሆኑ በእነዚህ ስፍራዎች የሚኖሩ የማህበራዊም ሆነ አካላዊ ርቀታቸውን ለመጠበቅ ፈታኝ እንደሚሆን እንዲሁም በርካቶቹ እጃቸውን የሚታጠቡበት ውሃና ሳሙና ላይኖራቸው ይችላል ተብሏል።