
ቻይና የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ከሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ከሆቴል እንዲወጡ መገደዳቸው ከተሰማ ቀናት ተቆጥረዋል።
ለዚህም እንደምክንያት እየቀረበ ያለው የኮሮናቫይረስ ፍራቻ ነው። አፍሪካውያኑ የዘር መድልዎ እየደረሰባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥቁሮች ፓስፖርት ሲነጠቁ፣ መገበያያ መደበር አትገቡም ሲባሉና ወደ መኖሪያቸው እንዳይገቡ ሲከለከሉም ያሳያሉ።
“መደብር ሄጄ የውጪ አገር ሰው አንቀበልም አሉኝ”
ስሟ እንዲጠቀስ የማትፈልግ ቻይና የምትኖር ኢትዮጵያዊት ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ እሷም ከምትኖርበት ቦታ ፓስፓርቷ ተስዶ ነበር።
“ፓስፓርቴን ሲወስዱብኝ ለምን እንደሆነ አላስረዱኝም ነበር፤ እዚያ ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቄ በሦስት ቀን ተመለሰልኝ” ትላለች።
ቤቷ ድረስ ሄደው ፓስፓርቷን ሲወስዱ ‘ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እንመልስልሻለን’ ከማለት ውጪ ምክንያቱን እንዳላሳወቋት ትናገራለች።
በምትኖርበት አካባቢ የዘር መድልዎ እየደረሰባቸው ስለመሆኑም ኢትዮጵያዊቷ ትገልጻለች። አንድ ጓደኛዋ በታክሲ ለመሄድ ስትሞክር አሽከርካሪው ለኃላፊዎች ደውሎ፤ ወደ ለይቶ ማቆያ እንድትገባ መደረጓን እንደማሳያ ትጠቅሳለች።
“አንዳንድ ነገር ልገዛ ወደ ሱፐር ማርኬት ሄጄ ‘ይቅርታ የውጪ አገር ሰው አንቀበልም’ ብለው ከልክለውኛል” ስትልም የደረሰባትን ታስረዳለች።

እሷና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ጓደኞቿ የእንቅስቃሴ ገደቡ እስኪነሳ ድረስ ባሉበት ሆነው ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተናግራ፤ “ገደቡ ከተነሳ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ አላሰብኩም፤ ትምህርቴን መቀጠል አለብኝ” ትላለች።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እየሞከረ እንዳልሆነም አያይዛ ታነሳለች።
“እይደለም በዚህ ጊዜ በሌላውም ጊዜ ችግር አለ” ስትልም በኤምባሲው በኩል ያለውን ክፍተት ታስረዳለች።
አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ስለ ቻይና ያላቸውን አመለካከት እንደቀየረውና እምነት እንዳጡ ትናገራለች። ሆኖም ግን “ይሄም ያልፋል ብዬ ማሰብ እፈልጋለሁ” ስትል ተስፋዋን ገልጻልናለች።
“ለይቶ ማቆያ እንድንገባ አስገድደውናል”
ስሙን የማንጠቅሰው ናይጄሪያዊ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ጉዋንዡ መኖር የጀመረው ከአምስት ወር በፊት ነበር።
የቀጣዩ የትምህርትዘመን ክፍያ ካጠናቀቀ በኋላ የተከራየበት ቤት ባለቤት፤ ቤቱን ለቆ እንዲወጣ ነገሩት።
ፖሊሶች እሱና ጓደኞቹን ከቤቱ ውጪ እየጠበቋቸው ስለነበር ያለውን እቃ ለመሰብሰብ ይጣደፍ ጀመረ።
እቃውን ጓደኛው ቤት ለማስቀመጥ ሲሄድ መግባት አትችልም በመባሉ፤ ለቀናት ጎዳና ላይ አድሯል።
“አያችሁ እንዴት ቤታችንን ለቀን እንድንወጣ እንዳስገደዱን? ለይቶ ማቆያ እንድንገባም አስገድደውናል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። ተማሪው ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ ቢነገረውም ከለይቶ ማቆያ እንዲወጣ አልተፈቀደለትም። የሚገኘውም ሆቴል ውስጥ ነው።
ጉዋንዡ ውስጥ አብዛኞቹ አፍሪካውያን ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደተገደዱና ጎዳና ላይ የወጡ እንዳሉም ተገልጿል።
አንድ የአፍሪካውያን ነዋሪዎች ወኪል “የተደበቁም አሉ” ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስታውቋል።

ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሁለት ናይጄሪያውያን ማምለጣቸውን ተከትሎ፤ አፍሪካውያን የሚኖሩበትና የሚነግዱበት አካባቢ እንደተዘጋ ጭምጭምታ የተሰማው በዚህ ወር መባቻ ነበር።
የቻይና መገናኛ ብዙሀን ናይጄሪያዊ ታማሚ ቻይናዊ ነርስ ላይ ጥቃት ማድረሱን ዘግቧል። ጤና ጥበቃም አፍሪካውያንን በስፋት መመርመር ጀምሯል።
በከተማዋ ከሚኖሩ 4,500 አፍሪካውያን 111ዱ ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተገልጿል።
ናይጄሪያዊው ተማሪ እንደሚለው፤ ‘የቻይና መንግሥት ትዕዛዝ ነው’ ብለው ጤና ባለሙያዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ወስደዋቸዋል።
አንድ የጉዋንዡ ነዋሪ “ከቫይረሱ ምርመራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ነገር አለመግባባት ይመስለኛል። የዘር መድልዎ አይደለም። የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም” ብለዋል።
ጉዋንዡ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ይኖራሉ። በከተማዋ ከሚኖሩት ብዙዎቹ ከቻይና ሸቀጥ ገዝተው ወደ አገራቸው ለመላክ በአጭር ጊዜ ቪዛ የገቡ ናቸው።
የቻይና መንግሥት የቀረበበትን የዘረኝነት ክሶች አጣጥሎ፤ ቻይና እና አፍሪካ ወዳጆች፣ አጋሮች፣ ወንድማማቾች ናቸው ብሏል። ዘረኝነትን እንደማይታገስም አስታውቋል።
በተቃራኒው ቢቢሲ ያነጋገራቸው አፍሪካውያን ዘረኛ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
የአፍሪካውያን ነዋሪዎች ወኪሉ፤ “98 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ናቸው” ይላል።
“እቅዳቸው እኛን መስዋዕት አድርጎ ሌሎችን ማዳን ነበር”
በመላው ቻይና የሚኖሩ አፍሪካውያን እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ዉሃን ውስጥ ዩኒቨርስቲዎች ቢዘጉም አፍሪካውያን ተማሪዎች ግን አልወጡም። “እኛን ትተውን ሄደዋል” ይላል ጋናዊው ተማሪ ማይክል አዴኔይ
ለሁለት ወር ያህል የጋና መንግሥት ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ሲያደርግ ነበር።
ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት 5,000 አፍሪካዊ ተማሪዎች ከዉሃን መውጣት አልቻሉም ነበር። የየአገራቸው መንግሥታትም ዜጎቻቸውን አላወጡም።
“የመስዋዕት በግ እንደሆንን ይሰማናል፤ እቅዳቸው እኛን መስዋዕት አድርጎ ሌሎችን ማዳን ነበር” ሲል አንድ ተማሪ ገልጿል። የአፍሪካ አገራት መንግሥታት ዉሃን ያሉ ዜጎቻቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ምንም አለማድረጋቸውንም ይናገራል።

ዉሃን ከሳምንት በፊት እንቅስቃሴ ላይ ጥላ የነበረውን ግድብ አንስታለች። በግዛቲቱ ሕይወት የቀደመ ገጽታውን እየተላበሰም ይመስላል።
በሌላ በኩል በዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ አፍሪካውያን ተማሪዎች እስካሁን ካሉበት አልወጡም። መቼ እንደሚወጡም የሚያውቁት ነገር የለም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጉዋንዡ የሚኖሩ አፍሪካውያን መረጃ እየተለዋወጡ ነው። በመላው አገሪቱ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎችና ተማሪዎች በየትኞቹ ሆስፒታሎች እና ሆቴሎች እንደሚገኙ የሚያሳዩ ፎቶዎችም ይለቃሉ።
አንዳንዶች ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ፣ ሌሎች ደግሞ ከአቅማቸው በላይ ተጠየቁትን የህክምናና የሆቴል ቆይታ ክፍያ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራሉ።
መድልዎ ለደረሰባቸው ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ የስልክ መስመር ቢከፈትም፤ አሁንም ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ አፍሪካውያን ስጋት እንደሸበባቸው ነው።
‘ትንሿ አፍሪካ በቻይና’ በመባል የሚታወቀው ዢዎ ቤይ ሉ ጎዳና ለወትሮው በአፍሪካውያን ነጋዴዎች ይሞላ ነበር። አሁን ግን ፀጥ ረጭ ብሎ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭተዋል።
