የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች ባለፉት 60 ቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ዘጠኝ ህፃናትን አግተው እንደወሰዱ የጋምቤላ ክልል አስታወቀ።

ታጣቂዎቹ ከህጻናቱ በተጨማሪም ሁለት ሰዎችን ገድለው ከ80 በላይ እንስሳትን ዘርፈው እንደወሰዱም ተገልጿል።
ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግሮ የሚመጣው ይህ ታጣቂ ቡድን በጋምቤላ ክልል በኑዌር እና በአኝዋ ዞኖች ባለፍት ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑ ህፃናትን ማገቱ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑ የሁለት ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ከብቶችም መዘረፋቸውን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ምክትል ዘርፍ ሃላፊ ኦቶው ኦኮት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ቡድኑን ለመቆጣጠርና ሌላ ጉዳት እንዳያደርስ ለማስቻልም ለተለያዩ የፀጥታ አካላት መመሪያ ተሰጥቶ ስፍራው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ብለውናል፡፡
በተጨማሪም ክልሉ በድንበር በሚዋሰንባቸው አምስት ቦታዎች ላይ የተለየ ጥንቃቄ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል ፡፡
የኮሮና ቫይረስ የሚያመጣውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባትም በታጣቂ ቡድኑ ታፍነው የተወሰዱ ህፃናትን ለማስመለስ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ለመነጋገር እቅድ መያዙን አቶ ኦኮት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም