ሙስጠፌ እና አብዲልሀፊዝ Hardtalk
ክፍል ስድስት እና የመጨረሻው ክፍል
(ሙክታሮቪች)
ጋዜጠኛ:
ክቡር ፕሬዝዳንት የደም ባንክ ጉዳይ አጣዳፊ ስለሆነ ነው ደጋግሜ የጠየክዎት፣ ስለዚህ መቼ ለአገልግሎት ይደርሳል?
ሙስጠፋ:
በቅርቡ ይደረሳል። ይህ ደርሷል አልደረሰም ንትርክ ከሳምንታት በፊት የነበረ ነው። አሁን ላይ እንደውም ለአገልግሎት ዝግጁ ሳይሆን አይቀርም። በነገርህ ላይ በአብዲ እና ከአብዲ በፊት በነበረው አስተዳደር ትምህርት ቤት ተሰራ ተብሎ ሪፖርት ይደረጋል። ብሩ ተበልቶ ትምህርትቤቱ አይሰራም። ህንፃ ተሰራ ተብሎ ህንፃው ልትፈልገው ብትመጣ እዚህ ነበረ፣ ማን አነሳው ይሉሃል። በእኔ ጊዜ ንትርኩ አልቋል አላለቀም መሆኑ በራሱ ለውጥ ነው።
ጋዜጠኛ፣
መልካም። በእርስዎ እና በክልሉ ፓርላማው መካከል ግጭት አለ ይባላል። ምንድነው የግጭቱ መንስዔ?
ሙስጠፋ:
ምንም ግጭት የለም ማሃላችን። የመንግስትን ስራ በአግባቡ ይቆጣጠራሉ። የደም ባንኩ ንትርክ እኮ ምንጩ እኔ ለፓርላማው ባቀረብኩት ሪፖረት ላይ አባላት እኮ ናቸው ያላለቀ ስራ ሪፖርት አድርገሃል ተብዬ ያፋጠጡኝ። ይህ የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ ነው። ስራቸውን ያለምንም እቀባ በነፃነት ነው የሚሰሩት።
ጋዜጠኛ:
ክቡር ፕሬዝዳንት፣ ሌላ የማነሳሎት ጉዳይ በእርስዎ ቀጥተኛ ትእዛዝ እርስዎ ስላሳሰሩት ኢርሻድ የተባለ ሰው ነው። ለመሆኑ እርስዎ ከእስሩ ጀርባ አሉ እንዴ? ማለቴ መአከላዊ መንግስት አዲሳባ ስለታሰረ፣ እርስዎ እንዳሳሰሩት መረጃ ደርሶኛል። ለምን አሳሰሩት?
ሙስጠፋ፣
ህግ ከጣሰ ይታሰራላ!
ጋዜጠኛ፣
ለምን ታሰረ?
ሙስጠፋ:
ሰው ሲታሰር መብቱ ተገፈፈ ወይስ አልተገፈፈም? ማሰቃየት ደርሶበታል ወይ አልደረሰበት ተብሎ ይጠየቃል እንጂ እንዴት ሰው ለምን ታሰረ ይባለል?
ሰው የማይታሰርበት ሀገር አይተህ ታውቃለህ? ሰውን የማያስር መንግስት አይተህ ታውቃለህ አንተ?
ጋዜጠኛ:
አላውቅም፣ ግን በህጉ መሰረት ነው የሚታሰረው። ይህ ሰው ግን እኔ ሳላጠፋ ከህግ ውጪ ፕሬዝዳንቱ ነው ያሳሰሩኝ እያለ ነው። እርስዎ አሳስረውታል አላሳሰሩትም?
ሙስጠፋ:
እኔ እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት አልፈልግም ነበር። ግን ላንተ ልስጥህ።
ሰው ሲታሰር ሙስጠፋ ነው ያሳሰረው፣ የሙስጠፋ ወንድም ነው ያሳሰረው፣ አጎቱ ነው ያሳሰረው እየተባለ አሉባልታ ይነዛል። ሁሉም ሙስጠፋ እንዲህ አደረገኝ ይህን ፈፀመብኝ እያለ ቢያወራ እኔ እየተከታተልኩ መልስ መስጠት የለብኝም።
በዚህ ጥያቄህ ተመልካቾች እንዳይሳሳቱ ስል ጉደዩን ልንገርህ።
አሁን ያነሳኸው ሰው በአብዲኢሌ ጊዜ ከፍተኛ ወንጀሎችን አብሮ ሲሰራ የነበረ፣ የአብዲኢሌ ቀኝ እጅ ከሚባሉት አንዱ ነው። በክልሉ በደረሰው የሀምሌ 28 ካባድ አደጋና የማይታመን ውድመት ውስጥ እጃቸው አለበት ተብሎ የታሰረ ነው። መንግስት አሰረው። አለቀ።
ኋላ ለፖለቲካው መረጋጋት፣ ለለውጡ እና ሽግግሩ ሲባል እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎች ይቅርታ በተደረገላቸው መሰረት ይቅርታ ተደርጎለት ተፈታ። ክልሉ ውስጥ የደረሰው ያ መዓት በመንግስት ደረጃ የተፈፀመ ስለሆነ ሁሉም በህግ የሚጠየቁበት አሰራር ብንከተል ማንም ላይተርፍ ይችል ይሆናል። ሁሉንም አስረን ደግሞ ሀገር ማረጋጋትና ሰላም መፍጠር አንችልም። ለዚያ ብለን በሆደ ሰፊነት ከተለቀቁት ውስጥ ይህ አንተ ስሙን የጠቀስከው ሰው ይገኝበታል።
ጋዜጠኛ:
ከዚያም ወደ ክልሉ ሲመጣ ዳግመኛ ታሰረ። መለቀቁን አልደገፉትም እርስዎ?
ሙስጠፋ:
አይ እንደዚያ አይደለም። ወደ ሌላ ወንጀል ሊሸጋገር ሲል ህግ ማስከበር ስላለብን አሰርነው። ጉዳዩን በህግ ይዘነው። ኋላ ክሱን አቋርጠን ለቀነዋል።
እሱ ፕሬዝዳንቱ አሳሰረኝ ይላል። የታሰረው ግን የክልሉ የሀይማኖት አሊሞች ላይ በቀሰቀሰው ከባድ ውንጀላ ነው።
በእምነታቸው ጠንከር ብለው በደንብ የእስልምና ስርዓትን የሚያከብሩ የተከበሩ ሰዎች ላይ አልሻባብ ስለሆኑ ሊወገዱ ይገባል እያለ አደገኛ ቅስቀሳ ውስጥ ገባ። የከፋ ነገር ሳይደርስ ከህግ በታች መሆኑን ልናሳውቀው አሰርነው። እንደ አብዲኢሌ ዘመን የሚቦርቅበት ዘመን ማለፉን ልናስገነዝበው በህግ ጠይቀነዋል።
አሁን ግን አልታሰረም። በነፃነት እየተንቀሳቀሰ ነው። ከእስሩ ጀርባ ሌላ የፖለቲካ ሊጫወት ይፈልጋል። በሶማሌ ህዝብ ስቃይና መከራ ሀብት እንዳካበተ ማንም ያወቃል። ይህን በሆደ ሰፊነት አልፈነዋል። ግን ህግ ከጣሰ ዛሬም ይታሰራል ነገም ሊታሰር ይችላል። ማንም ከህግ በላይ መሆን አይችልም።
ጋዜጠኛ፥
ክቡር ፕሬዚዳንት ስለሀይማኖት ጉዳይ ካነሳን አይቀር እርስዎ እራስዎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሶማሌና ሙስሊም ያልሆኑ ሌሎች ብሔሮች እና ሌላ የሃይማኖት ተከታዮችን የእምነት በዓላትን ጅጅጋ ላይ በደማቅ እንዲያከብሩ የተለየ መብት ሰጥተዋል የሚል ትችት ይቀርብቦታል ፣ ስለዚህ ትችት ምን ይላሉ?
ሙስጠፋ
አዎ! ህገ መንግስቱ ያጎናፀፋቸው መብት ሰጥተናል፣ አንፍገቸውም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የተለያዩ ብሔርና እምነት በሰላም ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖርበት ሀገር ናት። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ጤነኛ አስተሳሰብ ያሌላቸውና ከእነርሱ በስተቀር ሌላ እምነት ተከታይ መኖር የለበትም ከሚሉ ፅንፈኛ አክራሪ ቡድኖች እንጂ ከአንተ ዓይነት በተላይ የእምነት እኩልነትና ነፃነት የተከበረበት በሰለጠነ ሀገር የእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ከሚኖር ሰው አልጠበቅኩም፣ በጣምም ገርሞኛል!
እኔ በማስተዳድርበት ክልል ህገመንግስትም ሆነ በሀገሪቱ ህገመንግስት የእምነት ነፃነት ተረጋግጧል። የፈለገህን ሀይማኖት ማምለክ እና ማራመድ በሚቻልበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው። የእኔ ህጋዊ ሀላፊነት ለሁሉ እምነት ህጋዊ ከለላ መስጠት ነው።
በነገርህ ላይ የሶማሌ ህዝብ ከሌሎች ሀይማኖት ተከታዮች ጋር አብሮ መኖር ምንም ችግር የሌለበት፣ ተከባብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። በክልሉ ከዚሀ ቀደምም በይፋ ሰው የፈለገውን እምነት በነፃነት ያመልካል።
እኔ ያደረግኩት፣ ሙስሊምን እና ክርስቲያንን ለማጋጨት፣ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የጥፋት ሀይሎች ሀይማኖታዊ በዓላት ላይ አደጋ እንዳይጥሉ ነው ደህንነታቸውን በሚገባ ያስጠበቅኩት።
አንተ አብዱልሀፊዝ ግን ለንደን ነው የምትኖረው። ሙስሊም በቁጥር የሚያንስበት ሀገር መብትህ ተከብሮ እየኖርክ፣ እንደፈለክ በአደባባይ እያመለክ፣ የሰብአዊ መብትን የሚረዳ ጋዜጠኛ ሆነህ በኢትዮጵያ ሀገራቸው ላይ ሀይማኖታቸውን ለሚያከብሩ የተለያዩ ዜጎች ከለላ ሰጥቼ ደህንነታቸውን በማስጠበቄ እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄን ትጠይቃለህ። በጣም አስገርሞኛል። መታረም ያለበት አመለካከት ነው።
(ጋዜጠኛው ተሸማቀቀ፣ ልክ ነዎት በሚል አይነት ራሱን ነቀነቀ፣ ሙስጠፋን ነጥብ ለማስጣል የተሰጠው መረጃ፣ እሱን እራሱ ነጥብ ስላስጣለው ሳያፍር የቀረ አይመስልም)
ጋዜጠኛ፣
መልካም። እርስዎ ወደዚህ ስልጣን ከመምጣትዎ በፊት የተለያዩ የአለማቀፍ ድርጅቶች ከመሰራቶ ባሻገር የሰብአዊ መብትን መዐከል ያደረገ አክቲቪስትም ነበሩ። የእርስዎን የፖለቲካ አካሄድና የአስተዳደር ሁኔታዎን የሚነቅፉ ሰዎች አቶ ሙስጠፋ እስካሁን አክቲቪስት ናቸው። ሀገር ማስተዳደር ችሎታ የላቸው። መሪነት እና አክቲቪስትነት እየተቀላቀለባቸው እና እየተምታታባቸው ነው ይላሉ።
በርካታ ኮፍያዎችን ደራርበው ለብሰዋል። መቼ ነው እነዚህን ኮፍያዎች የሚያወልቁት?
ሙስጠፋ: (በስጨት ያለ ይመስላል፣ ቃላቶችን ረገጥ፣ ሻከር እያደረገ)
ይላሉ! ይላሉ! ይላሉ።
ይበሉዋ!
ጋዜጠኛ፣
እና?
ሙስጠፋ: (ለአፍታ ዝም አለና)
እየውልህ፣ ትችታቸው ይህን ተግባር ፈፅመሃል፣ ተግባሩ ከአክቲቪስትነት የመጣ ነው። ይህን ተግባር ፈፅመሃል፣ ይህ ደግሞ ከፖለቲከኝነት አልያም ሌላ ማንነትህ የመጣ ነው በማለት ዘርዘር አድርገው ሲተቹ ምላሽ ልሰጥ እችላለሁ።
ለሁሉ የማይረባ ትችት መልስ እየሰጠሁ ጊዜ አልፈጅም። በጣም አሳሳቢ ችግሮችን የምፈታበትን ውድ ጊዜ ለምን በማይረባ ንትርክ ጊዜ አባክናለሁ። እኔ እሰራለሁ። እነሱም ይተቹ።
ጋዜጠኛ፣
ክቡር ፕሬዝዳንት፣ ጥያቄዎቼን ጨርሼያለሁ። ፕሮግራሙን አመስግኜዎት ከመዝጋቴ በፊት በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦት።
ሙስጠፌ፣
አብዲልሀፊዝ በርካታ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አንስተሃል፣ የክልሉን ጉዳይ እንዳብራራ እድሉን ሰጥተኸኛል። ያነሳሃቸው ጥያቄዎች ጠቃሚና ብዙ የክልሉ ጉዳዮችን የሸፈነ ነው። ለዚህም አመሰግናለሁ።
በመጨረሻም ይህን ፕሮግራም እየተከታተለ ያለ የሶማሌ ህዝብ፣ በኢትዮጵያም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ፣ በመላው አለም የሚገኙ ሁሉ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለውን የተሻሻለ ለውጥ በንቃት እየተከታተሉ እንዲደግፉን አደራ እላለሁ።
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን በሙሉ ልብ እንዲደግፉት ከልብ እጠይቃለሁ።
የዶክተር አብይ ራዕይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚበጅ የትብብርና የመደጋገፍ ራዕይ ነው። ይህ ደግሞ ለህዝባችን እጅግ ጠቃሚ ራዕይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን በስራቸው እና በተግባራቸው ለመመዘን ክፍት በሆነ ልብ፣ ነፃ በሆነ አዕምሮ ያልተጣራ የሚነገሩባቸውን ጉዳይ ሳይሆን በእርግጥም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ድጋፍም ሆነ ነቀፋ እንዲሰጡ በማክበር እጠይቃለሁ።
ለመላው ሙስሊም ህዝብ መልካም የረመዳን ፆም የተባረከ ፆም በተለይም ከዚህ ኮሮና ወረርሺኝ ህዝባችንን አላህ እንዲጠብቅልን የምንፀልየውን ፀሎት አላህ የሚቀበልበት የረመዳን ፆም እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ።
አንተም ለሰጠኸች እድል አመሰግንሃለው።
ጋዜጠኛ፣ (ፈገግ በማለት)
ክቡር ፕሬዝዳንት በሌላ ጊዜ ባሉበት ጂጂጋ መጥቼ ያለውን ለውጥና የጎደለውን ለማየት ብመጣ ይፈቅዱልኛል ለሌላ ቃለመጠየቅ።
ሙስጠፋ፣
በሚገባ እፈቅድልሃለው።
ጋዜጠኛ፣
በነገራችን ላይ እንደርስዎ አዋቂ ሰው እና በሳል መሪ የሶማሌ ህዝብ ስላለው እድለኛ ነው።
ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
(ወደ ካሜራው በመዞር ተመልካቾቻችን …..)
ተፈፀመ
ትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
እኔም ሙክታር ባለቤቴ ኢፍራህ አህመድ ከጊዜዋ ተሻምቼ ይህን ረጅም ቃለመጠየቅ እንድተረጉም በሞራል ስለረዳቺኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
