April 23, 2020 – Konjit Sitotaw
” ዓይናችንን ከግድቡ ላይ ለአፍታ እንኳን ማንሳት የለብንም “ – ዶክተር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ዋና ሥራ አስኪያጅ **********************************
(ኢፕድ) – ቁጥር አንድ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ከምናስወግድበት መድሃኒቶች አንዱና ዋናው ቁልፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመሆኑ ዓይናችንን ከግድቡ ላይ ለአፍታ እንኳን ማንሳት እንደሌለብን ተጠቆመ። የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከድህነት የሚያወጣን በመሆኑ ትኩረታችንን ግድቡ ላይ ማድረግ ይጠበቅብናል። ሁልጊዜ ዓይናችንን ከግድቡ ላይ ማንሳት የለብንም። በግድቡ ዙሪያ ውዝግቦችና የተለያዩ ችግሮች በየጊዜው ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉት ዶክተር አረጋ፣“ግድቡን አጠናቅቀን ወደ ሥራ ከገባንም በኋላ ጭቅጭቅና ጫጫታዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል“ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረግን ባለው ጥረት ልክ ድህነታችንም ሊያስጨንቀንና ሊያሳስበን ይገባል ያሉት ዶክተር አረጋ፣ ለኮሮና ቫይረስ ሰዎች መድሃኒት እየፈለጉ ነው። እኛ ደግሞ ትኩረታችንን ሁሉ የድህነታችን መፍቻ ቁልፍ በሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በማድረግ የግድቡን ሥራ ዳር ማድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ዶ/ር አረጋ ፤ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጋራ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ከማስተባበር፣ ኢትዮጵያውያንን አንድ ከማድረግና ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት ዶክተር አረጋ፤ በቅርቡ ሲፈትኑን የነበሩ የብሔር ግጭቶችን ጭምር ለማስወገድ የሚረዳን፣ የሚያስተምረን፣ የሚያስተሳሰረንና የሚያስተባብረን ፕሮጀክት ነው። ብዙ ዋጋ የሚያስፈልገውና ዋጋ ሊከፈልለትም የሚገባ ትልቁ የጋራ ጉዳያችን ነው። የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የግድቡ ሥራው ተጠናቅቆ ተግባራዊ እንዲሆን እየደገፈ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ወደፊትም ዕርዳታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። “ችግሮች እየተደራረቡብን ቢሆንም ህዳሴ ግድቡ በራሱ አንዱ ፖለቲካዊ ጉዳያችን ነው፤ግድቡ ውሃ ተሞልቶ ሥራ እንዲጀምር እንፈልጋለን “ብለዋል።