April 23, 2020

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመከላከል በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ በርካታ ሰብአዊ ተግባራት የሚደነቁ እና የሚበረታቱ ናቸው። እርግጥ ነው መንግስት ይህን የማድረግ እና ዜጎቹን ከማናቸው አደጋና ጥቃት የመታደግ ግዴታ ስላለበት የሚመሰገነው ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት በማሳየቱ ብቻ ነው። ለድሆች የሚከፋፈለው የአገር እና የሕዝብ ሃብት ስለሆነ እንደ ተለየ ችሮታ አይቆጠርም። እርዳታ ከውጪም ማሰባሰቡ ዜጎችን በራሳቸው አቅም ለመታደግ የማይችሉ መንግስታት ኃላፊነት ስለሆነ ልክ ድርቅን እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል በመንግስት ከሚደረጉት ጥረቶች የተለየ ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም።

ይሁንና ይህን ሰብአዊ አድራጎት የሚያጠለሹ የጭካኔ እና ኃላፊነት የጎደላቸው እርምጃዎች፤ በተለይም በዚህ የወረርሽን ወቅት በመንግስት አካላት ሲፈጸም ማየት ደግሞ እጅግ ግራ ያጋባል። መንግስት የወረርሽኙን መስፋፋት ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ አንስቶ ሌሎች ይበል የሚያስብሉ እና በበጎነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰብአዊ እርዳታዎችን በአንድ ወገን እያቀረበ በሌላ ወገን ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል ሽፋን ዜጎች እራሳቸውን እና ልጆቻቸውን ለማስጠለያ የቀለሱትን ጎጆ በሌሊት ግብረ ኃይል እየላኩ ማፍረስ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው፣ ወቅቱን ያላገናዘበ፣ ጥናት ያልተደረገበት የጭካኔ እርምጃ ነው።

ለነገሩ እንዲህ አይነት እርስ በርስ የተጋጩ እርምጃዎች በመንግስት ሲወሰዱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

+ በአዋጅ ጭምር ዜጎች እቤታቸው እንዲቆዩ ደንግጎ እና በየጎዳናው ላይ የፈሰሱ ዜጎችን የመሰብሰብ እቅድ አውጥቶ የማቆያ ማዕከሎች የከፈተ መንግስት እንዴት በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ዜጎች በላባቸው የገነቡትን ደሳሳ ጎጆ አፍርሶ ከነ ልጆቻቸው ወደ ጎዳና ላይ አውጥቶ ይወረውራል?

+ እንዴት የትምህርት ተቋማትን ዘግቶ ተማሪዎች ወደ የቤታቸ እንዲመለሱ መመሪያ ያወጣ መንግስት ክልሎች በወሰዱት ድንገተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች አገልግሎት ማዕቀብ የተነሳ ተማሪዎች በየከተማው ትራንስፖርት አጥተው ለበርካታ ቀናት በአውቶቢስ ተራዎች እና በየጎዳናው እያደሩ ለእንግልት እና ለበለጠ በሽታ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል?

+ ለገበያም ሆነ ለሌሎች የግል ጉዳያቸው ከቤታቸው እራቅ ብለው የተጓዙ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይሰጥ ክልሎች ድንበራቸውን አጥረው የወጣም አይገባም፤ የገባም አይወጣም ብለው የዜጎችን የመንቀሳቀስ ነጻነት ማገድ ብቻ ሳይሆን ስንቃቸውን ጨርሰው በያሉበት ለእንግልት እና የበለጠ ለወረርሽኙ ተጋላጭ ሲሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ ሳይሰጥ የቆየበትንም ሁኔታ ልብ ይለዋል፤

+ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ከአራት ሰው በላይ በመንገድ መንቀሳቀስ አይቻልም፣ መጨባበጥ አይቻልም፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እና የኃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ መሰባሰቦችን ያገደ መንግስት የፋሲካን በዓል አስከትሎ ነፍሱን በበግ እና በበሬ የቀየረ ገበያተኛ፤ በዋናዋ ከተማ በአዲስ አበባ ሳይቀር አንገት ላንገት ገጥሞ ሲጋፋ እና ሲተራመስ እያየ እንዴት ዝም ይላል?

ሌሎችም በመንግስት የተወሰዱ እና እየተወሰዱ ያሉ ከፊል ሰብአዊ፤ ከፊል ጭካኔ፣ ከፊል ዳተኛነት የተሞላቸው እርምጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።

እንዲህ ያለው ወጥነት የጎደለው፣ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና የደመነፍስ እርምጃዎች አደጋዎችን ያባብሱ ይሆናል እንጂ መፍትሔ አይሆኑም። የሰብአዊነቱም ሆነ አልፎ አልፎ የሚታዩት የጭካኔ እርምጃዎች ለአገር ጥቅም፣ ለጠቅላላው ሕዝብ ደህንነት እና ወረርሽኙን ለመከላከል ከማሰብም ከሆነ በበቂ ጥናት ላይ ቢመሰረቱ እና የጉዳቱን መጠን ለመቀነስም በቂ የቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ እርምጃዎች ቢወሰዱ መልካም ነው። በዚህ ወቅት የዜጎችን መኖሪያ ቤት ማፍረሱ ምናልባትም ወረርሽኙን ለመከላከል ጭምር የሚበጅ ሆኖ ተገኝቶም እንኳ ቢሆን ለተፈናቃዮቹ ሌሎች የመኖሪያ ስፍራዎችን በቅድሚያ ማዘጋጀት የመንግስት ግዴታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።