ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!

ጸሎተ ሕዝቅያስና ሰላማዊት ዳዊት ማን ናቸው??

በታሪኩ ባለቤቶችና በትግል ጓዶቻቸው እንደተነገረው፤…….

“ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፤ ጥበብንም ያበዛል።”

ብዙ ጊዜ የሀገራችን ሀቀኛ ጀግኖች እዩኝ እውቁኝን ሳያበዙና ብዙ ሰውም ሳያውቃችው ህይወታቸውን ለሀገራቸው ሰጥተው ተሰውተው ያልፋሉ ። የነአብርሃም ደቦጭን ሾፌር ማን ያውቀዋል፤ ስንቱ ያስታውሰዋል? በዱር በገደሉ ፋሺስቶችን ተፋልመው፤ በየከተማው ነፍሰ ገድዮቹን ተጋፍጠው የተሰዉት ስማቸው በአሉታዊ እየተነሳ (ያውም ከተነሳ! ) የታሪክ አተላዎች የህዝብ መከታዎችና አለኝታዎች ሲባሉ እየሰማንስ አይደል?

ብዙዎች ጸሎተ ሕዝቅያስን አያውቁትም። ጸሎተ ግን ከተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች አንዱ የነበርና በ ኢሕአፓ ምስረታም ሂደት ተካፋይ የነበረ ጓድ ነው ። ጸሎተ ሕዝቅያስ በአዲስ አበባ ጣሊያን ሰፈር ይባል በነበረው ቦታ በ 1950 ዓ.ም. ተወለደ። እድሜውም ለትምህርት ሲደርስ ድሃ እናቱ እሱን ካቴድራል ትምህርት ቤት ሲያስገቡ ወንድሙን ይትባረክንና እህቱንም አስተምረዋል። ከካቴድራል ትምህርት ቤት በኋላ ጸሎተ ሕዝቅያስ አዲስ አበባ ቀ. ኃ. ሥ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በአርትስ ፋኩልቲ በታሪክ ትምህርት ተመርቋል።

ጸሎተ ሕዝቅያስ፤ በተማሪው ማህበር ንቁ ተሳትፎ የነበረውና ከዩኒቨርስቲ ማህበር መስራቾችና አጠናካሪዎች አንዱ የነበረ ሲሆን፤ ወደ አልጄሪያ ከተሰደዱት ተማሪዎች ጋር የመጀመሪያው በመሆን ከነጸጋዬ ገብረ መድህንና ሌሎች ጋር አብሮ ድርጅቱን በሀገር ቤት ለመመስረትና ለማጠናከር ጥረት ያደረገና ቀጥሎም የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ የታገለ ጓድ ነው።

በትግሉ መጀመሪያ ወጣት ታጋዮች የሚባሉት እነ ጸሎተ ሕዝቅያስ፤ መስፍን ሐብቱ፤ ብንያም አዳነ፤ ገዛኸኝ እንዳለ፤ ዋለልኝ መኮንን፤ ተካልኝ ወልደ አማኔል፤ ዮሐንስ ብርሃኔ፤ ኢያሱ ዓለማየሁ፤ ይስሐቅ ደብረ ጽዮን፤ ፍቅሬ ዘርጋው፤ ፋሲካ በለጠ ወዘተ እንደነበሩ ይታወቃል። አብዛኛዎቹም በ ኢሕአፓነት መስዋዕትነትን ተቀብለዋል።

ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቀ ጸሎተ ሕዝቅያስ በአስተማሪነት (ከአዲስ አበባ ውጪና በንፋስ ስልክ ትምህርት ቤት) ሲሰራ ባስተማሪዎች ትግል ተሳትፎ ለ3 ወር ለከርቸሌ እስር ቤት ተዳርጓል። በአዲስ አበባ በትግል ተሳትፎው በደርግ ሲጋለጥም ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢሕአሠ ጎንደር በመሄድ በዚያን ትግሉን ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ አሲምባ በመዝለቅ እዚያ ከነበረው የማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር ጋር በመሆን ትግሉን ቀጥሏል። ጸሎተን የሚያውቁት ቆራጥና ደፋር መሆኑን ሲመሰክሩ ወላጅ እናቱ በዚህ በኩል ብዙ የቃኙት መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ። ዛሬ ልጆቻቸውን ሁሉ ሞት ነጥቋቸው በህይወት ያሉ እናቱ ከርችሌ ታስሮ በነበር ጊዜ ጸሎተን ሊጠይቁት ሄደው “እሱ ምን ይሆናል ጎረምሳ ነው” ብለው ወደ ዓለም በቃኝ በመሄድ ጄኔራል ታደሰ ብሩን ይጠይቁ እንደነበር የነበሩና የሚያውቁ ይመሰክራሉ። በ አሲምባ የጸሎተ ህይወት የተቀጠፈው በላይ ሀሰን በሚባል በከተማ በዩኒቨርስቲ ያውቀው በነበር የኢሕአሠ የፋይናንስ ኮሚቴ አባል መሆኑም ይታወቃል።

በላይ ሀሰን ሜዳ ከመጣ በኋላ ሁለት ወንድሞቹ በቀይ ሽብር መገደላቸውና አባቱም ታስረው እንደነበር በመስማቱ የአንጎል መታወክ ደርሶበት ትጥቅም እንዳይዝ ተደርጎ የነበር ቢሆንም ይንከባከበው ከነበረው ከጸሎተ ጋር ወደ ወንዝ ለመታጠብ ሲሄዱ የጸሎተን መሳሪያ በድንገት አንስቶ እንደተኮሰበትና እንደገደለው የነበሩት ምስክሮች አረጋግጠዋል።

የጸሎተ ሕዝቅያስ ታናሽ ወንድም ይትባረክ ሕዝቅያስ ከአሜሪካ ተመልሶ በከተማ በድርጅቱ ስር ሲታገል በፍቅሬ መርዕድ ግድያ ላይ ተሳትፈሃል በሚል ተይዞ ሰናይ ልኬ በሚባለው አረመኔ ግብረ ስየል ከተፈጸመበት በኋላ ከ22 ሌሎች የኢሕአፓ አባሎች ጋር በአውሬው ደርግ በህዳር ወር ተረሽኗል ።

የጸሎተ ባለቤት ሰላማዊት ዳዊት ደግሞ በመስከረም 1951 ተወልዳ በመስከረም 1977 በአሲምባ በበሽታ ያረፈች ሲሆን ትምህርቷን በልዩ ልዩ የውጭ ሀገሮች ያጠናቀቀች ከመሆኗ ባሻገር በካናዳ ካርልተን ዩኒቨርሲቲ ተምራለች። አዲስ አበባ ስትመለስም በንፋስ ስልክ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ሰርታና በኢሕአፓነት ታግላ ወደ አሲምባም መጥታ እስከ ዕለተ ሞቷ ከጓደኛዋና ጓዶቿ ጋር ታግላለች። የሰላማዊት ዳዊትን ታሪክ በሚመለከት ታማራ ዳዊት የተባለችው ፊልም ሰሪ ፋይንዲንግ ሳሊ (“FINDING SALLY” ሳሊን ማግኘት) በሚል ርዕስ ፊልም ሰርታ በያዝነው ሚያዝያ ጀምሮ ለተመልካቾች እየቀረበ መሆኑም ታውቋል። ሰላማዊት ለታማራ አክስቷ እንደነበረችም ለማወቅ ተችሏል።

ጸሎተ ሕዝቅያስ፤ ወንድሙ ይትባረክ ሕዝቅያስና ባለቤቱ ሰላማዊት ዳዊት በህይወት ባለመኖራቸው ፤ ለትግሉ በመሰዋታቸው፤ ኢሕአፓ በመሪር ሀዘን ሁሌም ያስታውሳቸዋል ።

ክብር የህዝብን ጥያቄ አንግቦ ግንባሩን ለጥይት ለሰጠ ጀግና ትውልድ!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል