ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!


ሻምበል አመሀ አበበ ማን ነው??..

Image may contain: 1 person, closeup

በባለ ታሪኮቹ እንደተነገረው፤.

ማሳሰብያ፤….ከሻምበል አመሀ አበበ ጋር የ10ኛ ኮርስ የአባዲና ምሩቅ የነበረውና በ ኢሕአፓነትም ይፈለግ የነበረው ሌላው ጓደኛው አሁንም በህይወት ያለ ስለሆነ ታሪኩን ሊተርክልን ከፈለገ ከ በለጠ መረጃ ጋር ልናቀርብ እንደምንችል በዚሁ ማስታወቅ እንፈልጋለን ፡፡ ሌሎችም ሻምበል አመሀ አበበን የምታውቁ አንባቢዎቼ ካላችሁ፤ ስለ ህይዎት ታሪኩም ቢሆን መረጃዎችን ብትሰጡኝ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው።….የጀግኖቻችንን ታሪክ አብረን ተጋግዘን እንፃፍ።

ሻምበል አመሀ አበበ የመጀመርያ ደርጃ ትምህርቱን በደብረ ዘይት አፄ ልብነድንግል፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ናዝሬት በሚገኘው አፄ ገላውድዮስ ት/ቤት ከተማረ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘውና አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በመባል ይታወቅ በነበረው ተቋም በመግባት፤ በ 10ኛው ኮርስ፤ በምክትል ሌውተናንትነት በጥሩ ውጤት ተመርቋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረባ ሆኖ ጥቂት ጊዜ ከሰራ በኋላ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የፖሊስ ስራዎችን አከናውኗል። ከዚያም ጅማ በሚገኘው ፖሊስ ማሰልጠኛ መአከል አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል። አባቱ ሻምበል አበበም ከአፄው ስርአት ጋር ስለማይስማሙ በደረሰባቸው ተፅዕኖ ራሳቸውን መግደል ተገደው ነበር ይባላል።

በሰራዊቱና በመለዮ ለባሹ በጣም ተወዳጅ የነበረው ሻምበል አመሀ አበበ ይህንን ተወዳጅነቱን በመጠቀም ብዙ ፖሊሶችን ሲቀሰቅስና ሲያነቃቃ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡ በተለይም በየካቲት/ 66 አብዮት ጊዜ የህዝብን ትግል ለማጠናከር ብዙ አስተዋጾ አድርጓል፤ የ ንዑስ ደርግ አባል በመሆንም በሰራዊቱ ተመርጦ ሰርቷል። ወደ ሩስያ ተልከው የፖለቲካ ኮርስ ከወሰዱት አንዱ ሲሆን ተመልሶም ከጓደኞቹ ጋር ከደርግ ጽህፈት ቤት ሆነው የፖሊስና ደህንነትን የፖለቲክ ጉዳይ በሚመለከት ካድሬ/ሀላፊ ሆኖ ሰርቷል ፡፡

በዚህም ጊዜ ሻምበል አመሀ አበበ ከደርግ ባለስልጣኖች በተለይም ከመንግሥቱ ጋር በነበረው ግንኙነት፤ በደርግ ላይ እምነት በማጣቱና ተቃዋሚ በመሆኑ፤ በነ መንግሥቱ ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብሎ ስላሰበ፤ ይህንኑ ለኮርስ ጓደኛው ለቁምላቸው ተካ አወያይቶት ስለነበር፤ ይህም ሰው ለፖሊሱ ኮለኔልና ለደርግ አባል (3ኛ ኮርስ የአባዲና ምሩቅ) ለፈለቀ ገድለጊዮርጊስ ሹክ በማለቱ ፈለቀ ወንድሙ ጂኔራል ስዩም ገድለጊዮርጊስ በመንግሥቱ/ደርግ ከተገደሉት 60 ዎቹ አንዱ ነበርና ደርግ ፊት ነስቶት በመቆየቱ ለመወደድ በምስጢር የተነገረውን ለደርግ ነግሮ ለሹመት በቅቷል፡፡ ለዚህም ከሻምበል አምሀ ጋር ከነበሩት ውስጥ አምባሳደር ሲኒማ ላይ ከደርግ ወታደሮች ጋር ተታኩሶ የተሰዋውን ሻምበል ባሻ አብርሀምን መጥቀስ ይቻላል ፡፡

ኢሕአፓ ተብሎ በጥርጣሬ በደርግ አይን ውስጥ ገብቶ የነበረው ሻምበል አምሀ አበበ ከነተፈሪ በንቲና ሻለቃ አለማየሁ ግድያ በኋላ ሙሉ በሙሉ ህቡዕ ገባ፡፡ በፎቶ የተደገፈ ይፈለጋል የሚል ማስታወቂያ ወጥቶ ተሰራጨ፡፡ ጠቋሚው ቁምላቸው ተካ ለህይወቴ ያሰጋኛል ብሎ ወደ ዩጎዝላቪያ ተልኮ ሲመለስም ምንም የረባ ሹመት ሳያገኝ ቆይቶ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ ህይወቱ አልፏል፡፡

ሻምበል አመሀ አበበ የኢሕአፓ ስኳድ አባል በመሆኑ ብዙ ግዳጅ በ አዲስ አበባ የተወጣ ሲሆን በፋሺስቱ መንግስቱ ላይ በተደረጉትም የግድያ ሙከራዎች የተሳተፈ ደፋር ጀግና መሆኑ ይታወቃል ፡፡ በመጨረሻም ፋሺስቱ ኮለኔል ወደ ውጭ ህገር ይጓዛል ተብሎ ወደ አየር ማረፍያ በጉዞ ላይ እንዳለ፤ ሻምበል አመሀ አበበ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር ሆነውና አሸምቀው የግድያ ሙከራ ሲያደርጉ፤ በሰዓት እላፊ ከአብዮት ጥበቃዎች ጋር ተጋጥመው ተታኩሰው ጓዶቹ ሲገደሉ፤ አሱ አምልጦ ቦሌ አካባቢ እሚገኝ የጓደኛው ቤት ተደብቆ ከቆየ በኋላ በጥቆማ ቤቱ ተከቦ ሊይዙት ሲሉ በተኩስ መሀከል በክብር ተሰውቷል፡፡
በፀረ ደርጉ ትግል በርካታ የአባዲና፤ ፖሊስ ኮሌጅ ምሩቆችና መኮንኖች ለትግሉ አስተዋፅኦ አድርገው እስከ መሰዋት ሲደርሱ ሌሎች ደግሞ (እንደ ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ)ባንዳ ሆነው ከርመው ወያኔንም ሳይቀር አገልግለዋል ፡፡ በደርጉም በወያኔም ፀጥታ/ደህንነት ተቋም ሰርገው ገብተው ለኢሕአፓና ለህዝብ የታገሉትን ሁሉ የስምሪታቸው ይዘት ስማቸውን መጥቀስ ዛሬም ባይፈቅድልንም ድርጅቱም ህዝብም መቸም አይረሷቸውም ፡፡

ክብር የህዝብን ጥያቄ አንግቦ ግንባሩን ለጥይት ለሰጠ ጀግና ትውልድ!!

ለህግ የበላይነት፤ ለሰላም ለዴሞክራሲና ለ እኩልነት..
ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት!!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!