April 26, 2020

Posted by: ዘ-ሐበሻ

አንድነት ይበልጣል – ሚያዝያ 18 / 2012 – ሐዋሳ

እስክንድር ተፈቷል፤ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ቀድሞም መታሰር አልነበረበትም፡፡ ከመንግሥት በኩል ለሌሎች ሲሆን የምናስተውለውን ልበሰፊነትና “ትዕግሥት” እዚህም እንድናይ እንፈልጋለን፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውድ ውስጥ ሆነንም ቢሆን፡፡ በተለይ መንግሥት/ሐገር በሌላ ጅምላ ጨራሽ ጠላት (የኮሮና ወረርሺኝ) ላለመዋከብ በጥበብ በሚተጋበት ጊዜ “የአይንህ/ሽ ቀለም” አላማረኝም ዓይነት ሰዎችን (ኤልሣቤጥ ከበደን ጨምሮ) የማሠር “መለሳዊ አባዜ” ሌላ ቢቀር ከላይ የገለጽኩትን ጥበብ የማይመጥን ስንፍና ነው፡፡ በአሁኑ ሠዓት እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ትኩረት ይሰርቃል! ሕብረትን ያሳሳል! ዛሬ ሌላ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ መፍጠርን እንደቅንጦት ወይም በራስ ግዙፍ አጀንዳና ልፋት ላይ አሻጥር እንደመሥራት ነው የምቆጥረው፡፡ እስክንድር መፈታቱ ጥሩ ነው፡፡ ኤልሳቤጥንም ፍቱ! … ወደ ሚዛን ልኬታችን እንለፍ፤

ስለ እስክንድር ታጋይነትና በጸረ ወያኔ ትንቅንቅ ውስጥ ስለከፈለው መስዋዕትነት፣ ዴሞክራሲና አንድነት ፈላጊ ንቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያውቁት ነው …፡፡ እንኳን እኛ መጪው ትውልድም የእስክንድር ውለታ አለበት፡፡ በሐገራችን የመጀመሪያውን የግል ሜዲያ / ጋዜጣ መሥራች እስክንድር ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብቶችን በሐገራችን በማለማመድ ደረጃ የእስክንድር አሻራ መቼም ሊጠፋ አይችልም …፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በለውጡ ጅማሮ ሰሞን “አዲስ አበባ የኛ ብቻ” በሚል ቅዠት አብዛኛውን ሕዝብ ያወኩትን ተረኞች አደብ ያስገዛልን እስክንድር ነው፤ ጓደኞቹንና ብዙ የአዲስ አበባን ወጣቶች አስተባብሮ፡፡ ለዚህም አስተዋጽኦአቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡ የተረኛ ገዢነት ስሜትና ሤራቸው የተሰበረባቸውና እንዲያፈገፍጉ የተገደዱት እነ ጃዋርና ኩባንያው፣ እነበቀለ ገርባ፣ በጠቅላላ የኦሮሞ ጽንፈኞች፣ የቀድሞ ኦፒዲኦ ቆሞ-ቀሮችና አሁንም ብልጽግና ውስጥ የመሸጉ የወያኔ ተላላኪዎች (ስድብ አይደለም!) ለጊዜው አደብ ገዝተዋል፡፡

በ”አዲስ አበባ የኛ ብቻ” ቅዠት ተደፋፍረው፣ በነጃዋርም ተቀስቅሰውና ተደግፈው ሐገሩን ሁሉ ሲያተራምሱ የከረሙት ሌሎች “እኛ/የኛ ብቻ” ባዮችም ለማፈግፈጋቸው የነእስክንድር የቅርብ ጊዜው እልህ አስጨራሽ ትግል የማይናቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡ ሐዋሳ (አጄቶ)፣ አዳማ/ናዝሬት፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ … “የኛ ብቻ” በሚል ተመሳሳይ የብሔር-ብሔር ጨዋታና ቅዠት የጠፋውን የንጹሃን ሕይወት፣ የጎደለውን አካል፣ የወደመውን ንብረት የተገፋውን፣ የተሰደደውንና የተሸማቀቀውን ዜጋ ገና ማንም በቅጡ አልቆጠረውም፣ አልጮኸለትም፡፡ …

የሚዛኑን ሌላ ሣህን/ገጽ እንቃኝ፤ እስክንድር አሁን-አሁን፣ ከተጀመረው ለውጥ በትይዩ የሚያደርገው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መብቱ ስለሆነ ሊከበርለት ይገባል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ትርጉሙና ዓላማውስ ቢሆን ይኸው አይደል እንዴ?! ነገር ግን በአሁኑ የነእስክንድር እንቅስቃሴ ውስጥ ተቃውሞን ለተቃውሞ ብቻ ሲሉ የማድረግ አባዜ በዝቶ ይታየኛል፡፡ ተቃውሞ በራሱ ግብ አይደለም፤ የሆነ ግብን መምቻ መሣሪያ እንጂ፡፡ ሐገራዊ ፋይዳቸው፣ ትክክለኛነታቸውና ወቅታዊነታቸው በቅጡ ሳይታይ ትንንሽና አላፊ አጀንዳዎችን እያነሱ ማጮህ የበዛ ይመስለኛል፡፡ ነገር በደላላ አፈላልጎ አጀንዳ ማድረግና ማስጮህ ፖለቲካ አይደለም፤ የረባሽ ልጅ ሁከት እንጂ፡፡ ጎበዝ! የአዲስ አበባን ተፈናቃዮች የመታደግና የተረኞችን ነውር የማጋለጥ ጥረቶችን እያቃለልኩ እንዳልሆነ ከወዲሁ ይታወቅልኝ፡፡ የነከንቲባ ታከለን እንቅስቃሴ እግር በግር እየተከተሉ መተቸት አጀንዳው/ፕሮግራሙ ማድረግ የፈለገ አካል ይህን ማድረግ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን የነከንቲባ ታከለን ክንዋኔ በሚመለከት እነእስክንድር የሚሉት ነገር እኛ ዜጎች እንዲገባንና እንድናምናቸው ሰዎቹ የሚሠሩትንና የማይሠሩትን ለየብቻ አድርገው፣ በማስረጃ አስደግፈውና ሚዛን ጠብቀው ቢቃወሟቸው ይሻላል፡፡ ይህ ምናልባት ለተተቺዎቹም ለእኛም ለታዳሚዎች (መራጮች/ዜጎች) ጥቅም ይኖረዋል፡፡ የተሠራውንና በጉልህ የሚታየውን ብዙ ጥሩ ነገር ሣይሆን ያልተሠራውንና እርሱም ቢሆን በጉልህ የሚታየውንም ሆነ የማይታየውን ጥቂት ነገር ብቻ ማጋነን ልክ አይደለም፡፡

የያዝነው ተቃውሞም ቢሆን ለተሠራው ዕውቅና እየሰጠን፣ ያልተሠራውን እያሳየንና እየተቸን እንዲሁም አማራጫችንን እያቀረብን መታገል ነው ጤናማ ፖለቲካ፡፡ ፖለቲካ ምክንያታዊ፣ ኃላፊነት የተሞላበትና የሐገርና የሕዝብን ጥቅም ሲያስቀድም ነው እንደኔ ጥሩና ሥልጡን ፖለቲካ የሚባለው፡፡ አለበለዚያማ ወያኔን (እነ ጌታቸው ረዳን) እንተውና ከነጃዋር፣ በቀለ ገርባ፣ ልደቱና የጽንፈኛ አክቲቪስቶች “ፖለቲካ” በምን ሊለይ ነው፡፡ እኔ ከእስክንድርና አብረውት ካሉት ይህን አልጠብቅም ነበር፡፡ ይዋል ይደር እንጂ ወደቀልባቸው እንደሚመለሱና መሻሻል እንደሚያሳዩም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ምክንያቱም እነእስክንድር አሁን-አሁን እየሆኑ ያሉት ነገር ከተፈጥሮአቸውና ከታሪካቸው (ከልፋታቸው) ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ እንዴ እነ እስክንድር እኮ ጀምረው ገና ያልጨረሱት ትልቅ ሥራ አላቸው! ረሱት እንዴ?! ፒኮክ በአንበሣ እንድትለወጥ ታሪክን (ለምሳሌ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት) ጠቅሶ መነጋገርና ከተቻለ መተማመን እያለ፣ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ ሰውን በሌላ አጀንዳ መጥመድ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ጤናማ ፖለቲካ ነው ትላላችሁ?  ለማንኛውም እነ እስክንድር ወደቀልባቸው እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ወይስ እኔ ያላየሁትና ገና ያልገባኝ ነገር ይኖራቸው ይሆን? ለማወቅ ዝግጁ ነኝ፤ ጥረትም አደርጋለሁ፡፡ እነ እስክንድርንም እኔንም እኛንም ሐገራችንንም ፈጣሪ ይርዳን!!