አቶ መንግሥቴ አስረሴ ከአባታቸው ከአቶ አስረሴ ብሩና ከእናታቸው ወይዘሮ ሙጭት ገድበው ህዳር 9 ቀን 1930 .. በጎንደር ከተማ ተወለዱ፡፡ አቶ መንግሥቴ ሁለት ሴቶች ልጆች ከተወለዱ በኋላ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ በመሆናቸው እንደዘመዶቻቸው ሁሉ በትምህርት፤ በክህነት አድገው እግዚአብሔርንና ወገኖቻቸውን እንዲያገለግሉ በሕፃንነታቸው ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አባታቸው አስገቧቸው፡፡ ገና በጨቅላ እድሜያቸው ዳዊት ደግመው ዳዊቱንም በቃላቸው ስለወጡት የአካባቢውና የጎረቤቱን ሰው ሁሉ አስደመሙት፡፡ አባታቸውም ለከፍተኛ ትምህርት ጥሩ መምህር አሉ ወደተባሉበት ወደ ደብረታቦር ላኳቸው፡፡ ሆኖም እናታቸው የመጀመሪያ ብርቅ ወንድ ልጃቸው ገና በሕፃንነታቸው ርቀው በመሄዳቸው አዝነው በሽማግሌና በዘመድ አማላጅነት ወደ ጎንደር እንዲመለሱ ተደረገ፡፡

ከተመለሱም በኋላ በቂርቆስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በዲቁና አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ዘመናዊ ትምህርት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደርጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ት/ቤት በመግባት በመምህርነት ተመርቀው በኤርትራ ክፍለሀገር ምፅዋና አስመራ ከተማ ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ በአገር ግዛት ሚኒስቴር በሕዝብ ደህንነት ከፍል ተመድበው ለበርካታ ዓመታት አገራቸዉን በቅንነት አገልግለዋል፡፡

አቶ መንግሥቴ ብሩሕ አእምሮና ከፍተኛ የሆነ መጽሓፍ የማንበብ ፍቅር ስላላቸው የሸክስፒርን ሙሉ ድርሰቶች በመግዛት የያንዳንዱን ተዋንያን ንግግርና ግጥም መተንተን ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ፤ Black and White የተባለውን Sydney Cook and Gartlean በተባሉ ጸሓፊዎች የተጻፈውን መጽሓፍ ወጣቱን ወደ በጎ ተግባር መመለስ ይችላል ብለው ስላሰቡ ወደአማርኛ ተርጉመዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት ሥራ ላይ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ መተማና ሁመራ የሚገኘውን የዘመዶቻቸውን የሰሊጥና የጥጥ እርሻ ሲያስተዳድሩ በነበረበት ጊዜ ከወይዘሮ ንግሥት ያሬድ ሴት ልጃቸውን ወይዘሪት መታሰቢያ አስረሴን አፍርተዋል፡፡ በመተማ ቆይታቸው ጊዜ የ1966 .. የመንግሥት ለውጥና የመሬት አዋጁን ተከትሎ የአካባቢው ፀጥታ በመደፍረሱ ለተሻለ ለውጥ ከሚታገሉ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኅብረት ተብሎ በሚጠራ የፖለቲካ ፓርቲ ሌሎች ጓደኞቻቸውን ተቀላቀሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት መስራች አባል የነበሩት አቶ መንግስቴ አስረሴ ሀገር ወዳድ፣ ማንኛውንም ሰው ያለአድሎ የሚወዱ፣ ለውድ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉና ከማንኛውም ማህበረሰብ ጋር ያለምንም ችግር አብሮ መኖር የሚችሉ ልበ ሙሉ እና በፍጹማዊ ፍቅር የተሞሉ፣ ከራስ ይልቅ ለሰው መልካም ማድረግን ቅድሚያ የሚሰጡ ጠንካራ ታጋይ ነበሩ፡፡ በ1968 አም በህዳር ወር በመተማ አካባቢ በትጥቅ የታገዘ ከፍተኛ ጸረ ደርግ እንቅስቃሴ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ከነበሩት የአካባቢው ታዋቂ አርበኛ እጣናው ዋሴ ጋር ግንኙነት ፈጠረው በጋራ ለመታገል ሙሉ ውሳኔ አደረጉ፡፡ የደርግን አስተዳደር በመቃወም የኢትዮጵያን ህዝብ ከደርግ ነጻ ለማውጣት ያለመ መሆኑን እና የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን እንዲቀላቀል የሚያትት የበሰለ ቀስቃሽ ጽሁፍ ጽፈው የኢድዩ ፖለቲካዊ መርሆዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በ1969 መስከረም ወር የኢዴህ መስራች ሰራዊት ከሱዳን እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ታጋይ መንግስቴ አስረሴ በመተማ ግንባር ከነ ታጋይ ሻለቃ እጣናው ዋሴ ጋር አብረው ዘምተዋል፡፡በመተማ ግንባርም የአስተዳደር ስራዎች ሀላፊ ሆነው በተመደቡበት የስራ ሀላፊነቱ በከፍተኛ ብቃት ተወጥተዋል፡፡ በሲፍዋ የኢድዩ ማሰልጠኛ ጣቢያ ተመድበው በሀላፊነት ሰርተዋል፡፡በዃላም በኢድህ ድርጅት በአመራርና በኃላፊነት ሲታገሉና ሲያታግሉ ቆይተዋል፡፡

በመጨረሻም ወደአሜሪካ ከድሮ ጓደኛቸው ወይዘሮ ጆርጅና ግደይ ጋር ተገናኝተው በባልና ሚስትነት ወደአሜሪካ ተስደዱ፡፡ ወይዘሮ ጆርጅና እኤአ በ2006 በሞት እስከተለዩአቸው ድረስ በሚያስቀና መተሳሰብ፤ ፍቀርና መግባባት አብረው ኑረዋል፡፡

አቶ መንግሥቴ አሜሪካ በስደት ወዲያው እንደመጡ የኢትዮጵያ ማህበርሰብን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ ጀምረው በ1984 እኤአ ለተመሰረተውና እስካሁንም ኢትዮጵያውያንና የሌሎችንም አገር ስደትኞች በማገልገል ለሚገኘው በችካጎ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበር (Ethiopian Community Association of Chicago) የመሥራች ቦርድ አባልና ቀጥሎም በቦርድ ፕሬዝዳንትነት፤ በአማካሪ ቦርድና በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሁም እንደገና በቦርድ አባልነት በዚህ በያዝነው ዓመት ጀምሮ እስከዕለተ ሞታቸው ድረስ ኮሚኒቲውን በትጋት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

እንደ ኮሚኒቲ አገልግሎታቸውም ሁሉ በቤተ ክርስቲያንም በኩል እንደአሁኑ በቁጥር በቂ ካሕናት ባልተገኙበት በምእራባዊያን የዘመን አቆጣጠር በ1980ና በ1990ዎቹ ዓመታት ጊዜ በቺካጎ የሚገኘዉን ደብረ ጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በዲቁና አገልግለዋል፡፡ የሃይማኖቱን ሕግጋት ጠንቅቀው ከማወቃቸውም በላይ በተግባርም ሲያውሏቸው ይታያሉ::

የአቶ መንግሥቴን የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ በማቋቋምና ምሥረታ ላይ የጎላ ነጸብራቅ እንዲኖራቸው ከሚያደርጉት ውስጥ በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦም እንደነበረ የማይካድ ነው። ከልጅነት ጀምሮ በነበራቸው መንፈሳዊ ሕይወትና የጠነከረ አቋም፤ ቤተ ክርስቲያን በማቋቋም ላይ ደማቅ አሻራ ከተዉት ውስጥ አቶ መንግሥቴ አንዱ ነበሩ።

በምእራባዊያን የዘመን አቆጣጠር በ1980ዎቹና 1990ዎቹ ሊቀ ሊቃዉንት አባ ተክለሚካኤል (ነሲቡ) ታፈሰ በኤቫንስተን ንዑስ ከተማ የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት በተቻለ የተሟላ እንዲሆን በሚጥሩበት በዚያን ጊዜ በዲቁና ከረዷቸው አንዱ አቶ መንግስቴ ነበሩ። እንዲሁም ለቤተክርስቲያኑ ቁሳቁስ ሲገዛ በመርዳት፣ የአገለግሎት ክፍል በማደራጀትና በማጽዳት፣ ተንስኡ ለጸሎት በማለትም ለምእመናኑ የቤተክርስቲያን አገልግሎት በመስጠታቸዉ ሊቀ ሊቃዉንት አባ ተክለሚካኤል (ነሲቡ) ታፈሰ ከልባቸውከመረቋቸው የችካጎ ነዋሪም አንዱ አቶ መንግሥቴ ነበሩ።

አቶ መንግሥቴ የሰው ፍቅር የነበራቸውና ለሰው ችግር ቀድሞ ደራሽ ነበሩ። እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ አዋቂ፣ ተጫዋች፣ ሰውን አዝናኝና ኢትዮጵያዊያንን አቀራራቢ ነበሩ። ደስተኛ ሰዎች ብዙ ያላቸው ወይም ብዙ የሚፈልጉ ሳይሆኑ ብዙ የሚሰጡ ናቸው ይባላል። አቶ መንግሥቴም ለህብረተሰቡ ያበረከቷቸው ስጦታዎች እጅግ የበዙ በመሆናቸው ደስተኛ የነበሩ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነበር። በሁሉም ወገን ተወዳጁ አቶ መንግስቴ ለወገን ችግር ደራሽ፤ የተጣሉትን አስታራቂ፤ በደስታም ሆነ በሃዘን ፈጥኖ ደራሽ፤ መካሪና አስተባባሪ፤ በማንኛውም ዝግጅት ላይ ለሁኔታው ተስማሚ በሆነ፤ በአማረ፣ በሰለጠነና በታረመ አንደበት መርሃ ግብሮችን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የመድረክ ፈርጥ ወንድማችንና አባታችን ነበሩ፡፡

አቶ መንግስቴ በኮሮና በሽታ በመጠቃታቸው በሕክምና ሲረዱ ቢቆዩም በተውለዱ በ82 ዓመታቸው April 17, 2020 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሞት በሁሉም ያለ ቢሆንም ወዳጆቻቸውና ዘምዶቻቸው ተሰባስበው ሃዘናቸውን መግለጽ የማይችሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ ሀዘናችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡

አቶ መንግስቴ ከዚህ ዓለም በዚህ ክፉ ጊዜ በሞት በመለየታቸው ልጃቸውን ወይዘሪት መታሰቢያ አስረሴን፤ ታላቅ እህታቸውን ወይዘሮ ክበበ ፀሓይ አስረሴን፤ ወንድማቸውን አቶ ንጉሴ አስረሴንና አቶ ወርቁ አስረሴን እንዲሁም በጣም የሚያፈቅሯቸውን ቤተ ዘመዶቻቸውን፤ አፍቃሪ ጓደኞቻቸውንና በችካጎ አካባቢ ያለነውን ኢትዮጵያውያን ጓደኞቻቸውን እግዚአብሔር ጥናቱን ይስጠን፡፡

የአቶ መንግስቴ ቀብር ሥነ ሥርዓት CDC በደነገገው ሕግ መሰረት፣ ጸሎተ ፍትሀት በሚወዷቸውና በሚያከብሯቸው የደብረ ጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ከተከናወነ በኋላ ሰኞ፣ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ/(April 27, 2020)፣ ችካጎ በሚገኘዉ በRose Hill መካነ መቃብር ከሚውዷቸው ባለቤታችው ወይዘሮ ጆርጅና ግደይ ጎን ይፈጸማል።

ልዑል እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስ ይስጥልን!