April 27, 2020

በአዲስ አበባ የተከሰተውን መፈናቀል እንቃወማለን! – ኢሕአፓአሠራሮች ሚዛናዊነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንጠይቃለን!ሚያዝያ 2012 ዓ.ም.

ዓለምን ያንበረከካትን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ህሙማኑንም ለማከም የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም፤ ሙከራዎች እዚህም እዚያም እየተደረጉ መረጃዎች ቢወጡም፣ ወረርሽኙ ገና ቁርጥ ያለ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡ የበለጸጉትን ሀገራት ያንበረከከው ወረርሽኝ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደአፍሪካ ያደረገ ይመስላል፤ ስርጭቱም በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑም ይዘገባል፡፡ በሀገራችን ውስጥ ያለው የተጠቂዎች ቁጥርም ከቀን ወደቀን እየጨመረ ቢሆንም አገግመው የሚወጡት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ለወረርሽኙ የተሰጠው ትኩረትም በጀመረበት ደረጃ መቀጠሉም የሚበረታታ ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ ፈታኝ ጊዜ ለወገን አለኝታነታቸውን በማስመስከር ቤታቸውን፣ ድርጅታቸውን፣ መኪኖቻቸውን ገንዘባቸውን ለግሰዋል፡፡ ወጣቶች በየአካባቢያቸው በመሰባሰብ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ በማሰባሰብ ሥራ ላይ ሲተጉ ታይተዋል፡፡ የሀገሪቱ መሪዎችም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለው ሕዝብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ወረርሽኙን በተገቢው መንገድ ለመከላከል ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አስፈላጊ መሆኑን በርካቶች ተስማምተውበታል፤ እንዲያውም ማስፈለግ ብቻ ሳይሆን ቀግይቷል የሚሉም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ለአምስት ወራት የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካታ ድንጋጌዎችን ይዟል፤ ከዚህ ውስጥ ዜጎች በመኖሪያ ቤት ችግር እንዳይገጥማቸው፣ የቤት ኪራይ እንዳይጨምርና ያለፍላጎታቸው ከሚኖሩበት ቤት እንዳይወጡ የሚደነግገው ይገኝበታል፡፡ መንግሥት ለሚያከራያቸው ቤቶች የሀምሳ በመቶ የኪራይ ቅነሳ ማድረጉም እንዲሁ የማይዘነጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወረርሽኙ ማህበራዊ እሴቶቻችንን የተፈታተነ ሆኖ የዘንድሮን የትንሳኤ በአል ከወትሮ የአከባበር ሥርዓታችን ወጣ ባለ መልኩ ቤተክርስቲያናት ተዘግተውና ምዕመናንም በቤታቸው ታቅበው ለማሳለፍ ቢገደዱም፤ ሥርዓተ ጸሎቱን በቤታቸው እንዲከታተሉ ቤተ እምነቶቹ ያደረገችውን ጥረት፣ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ ለዚህ የጸሎት አገልግሎት ማሰራጫነት የፈቀደውን የግል ተቋም፣ የአየር ሰዓታቸውን የሰጡትን የመንግሥት የመገናኛ ብዙሀን ማመስገን የተገባ ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረጉት ከክርስቲያኑ በዓል ቀጥሎ ደግሞ የተጀመረውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ የረመዳን ጾም የመያዣ ሥርዓትም ማስተላለፍ መጀመሩ እጅግ መልካም ሥራ ነው፡፡ በዚህ በዓል “ማዕድ ማጋራት” በሚል እሳቤ በየአካባቢው ከፍተኛ የበአል ስጦታዎች ሲደረጉ የአገር መሪዎችም ተሳትፈዋል፤ በየሰፈሩ በመገኘት የተለያዩ ቁሳቁሶችን አበርክተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን በአንዳንድ አሠራሮች አካላዊ መራራቅን ማስጠበቅ ያለመቻሉም ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል ታይተው መታለፍ የሌለባቸውን እና በዚህ በከፋ ጊዜ በዜጎች ላይ ሊደረጉ የማይገባቸውን ተግባራትም በዝምታ ማለፍ ትክክል ያለመሆኑን መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን፡፡ ፓርቲያችን በሕግ የበላይነት የሚያምን መሆኑን ሁሌም አበክረን የምንገልጸው ጉዳይ ሲሆን ለሕዝብ መብቶች በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ወገናዊነቱን ይገልጻል፡፡ ይህንን መግለጫ እንድንሰጥ ዋናው ምክንያታችን በዚህ ወቅት በዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል ሲሆን ሌሎችን ስህተቶችንም እንገልጻለን፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተደረገውን ማፈናቀል እንቃወማለን፡ ጠዋትና ማታ ሕዝብን ከወረርሽኙ መታደግ የወቅቱ አንገብጋቢ ተግባር መሆኑ እየተገለጸ፣ የወቅቱ የትኩረት አቅጣጫ ሁሉ ለዚሁ በተሰጠበት ጊዜ፣ ዜጎች ከሚኖሩበት ቤት እንዳይወጡ እንዲያውም ኪራዩ እንዲቀነስላቸው እየተደነገገ ባለበት ሁኔታ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን ከመጠለያቸው ማፈናቀል ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? መንግሥት የሕዝቡን መጠለያ የማግኘት መብት ማስከበር ሃላፊነቱ ሆኖ ሳለ በሕገ ወጥ ግንባታ ምክንያትነት ድሆችን ማፈናቀሉ ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም በዚህ ሰዓት በቦሌና በኮልፌ አካባቢ የፈጸመው ተግባር ግን እጅግ አሳዛኝና ከሰብአዊነት ውጭ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ምግብና ቁሳቁስ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች በማደል ሲታትሩ የሚታዩት መሪዎች ዓይኖቻቸው እነዚህን እናቶች፣ አባቶችና ሕፃናት ማየት ለምን አቃታቸው? አዲስ አበባ በቤት ግንባታና ፈረሳ ዙሪያ ያላት ችግር አብሯት የኖረ ሆኖ እያለ፤ አሁን ሀገራችን ያለባት አንገብጋቢ ጉዳይ ሕይወት ማዳን መሆኑን ሁሉም ወገን ተስማምቶ በአንድ በቆመበት ጊዜ፣ የተባለው “ሕገ ወጥ የቤት ሥራ” ተፈጽሞ ቢሆን እንኳን ሕጉን ለማስከበር ይህን ቀውጢ ጊዜ ማሳለፍ እንዴት አልተቻለም? ይህ ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ እና ድርጊቱም ይቅርታ ሊጠየቅበት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለሕዝብ የሚያስፈልገውን መረጃ የመስጠትና ዕውነታዎችን የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በማመን እነዚያ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታና የተሰጠውን መፍትሔ ለሕዝብ ግልጽ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ ዜጎችን ወደመጡበት ክልል የመመለስ ተግባር፡ በዚሁ ኮሮናን በመከላከል ሂደት ውስጥ አዲስ አበባ ትዝትን ያጫረ ድርጊት አስተናግዳለች፡፡ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የአማራ ተወላጅ የሆኑ በቀን ሥራ የሚተዳደሩ እንዲሁም የጎዳና ልጆችን ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ በአውቶቡሶች እያሳፈረ ወደመጡበት ክልል እንደመለሳቸው ተሰምቷል፡፡ ድርጊቱ ዕውነት መሆኑም ተነግሯል፡፡ ሌሎች ሀገሮች በእኛ በአፍሪካውያን ላይ የፈጸሙት አድልኦ እየተወገዘ ባለበት ቅጽበት ዜጎች ደግሞ እዚሁ በሀገራቸው ላይ የተፈጸመባቸው በደል የበለጠ ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡ መቺም በሀገራችን ነገሮችን አለባብሶ ማለፍ የተለመደ በመሆኑ ችግሩን በፈጠሩት ሃላፊዎች ላይ ማጣራት እየተደረገ ነው ተብሎ የውሃ ሽታ ሆኖ እንዳይቀርና ሁኔታው ተጣርቶ ትክክለኛ መረጃ በመገናኛ ብዙሀን እንዲገለጽ እንጠይቃለን፡፡ የመመሪያዎችን የጋራ ተፈጻሚነት ስለማረጋገጥ፡ ይህ በዓለማችንና በሀገራችን የተከሰተ ፈተና በተለይም የሀገርችንን ፖለቲካዊ ፍጥጫ ያበረደ፣ በዘር የመከፋፈላችንን አባዜ የሚፈውስ ሊሆን ይችላል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ትንቢት መሰል ነገር ተነግሯል፡፡ ሁሉም ፖለቲካዊ ልዩነቱንና ሌሎች ችግሮችን ወደጎን በማድረግ ለዚህ የጋራ አጀንዳ እንዲቆም ጥሪዎች ተላልፈዋል፤ ተቀባይነትንም አግኝቶ የፖለቲካ ትኩሳቱ ሙሉ በሙሉ ቀዝቅዟል ባይባልም ተረጋግቷል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ሁኔታዎች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ ሩጫዎችም ተስተውለዋል፡፡ ከምንንቀሳቀስባቸው ክልሎች በሚደርሱን መረጃዎች መሠረት በተለይም የገዥው ፓርቲ መዋቅሮች ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እያዋከቡ አንዳንዴም አባሎችን ለእስር እየዳረጉም እነርሱ ግን መመሪያም በመጣስ በየወረዳው ስብሰባዎቻቸውን ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ በመሆኑም ለቀሪዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወራት የሕጉ ተፈጻሚነት ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ እንዲተገበርና ከአዋጁ ዓላማ ለወጡ ርምጃዎች እንዳይውል እናሳስባለን፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን መረጃ እንዲያገኝ መሥራት፡ በሀገራችን በመንግሥትና በሕዝብ መሀል ያለው የመተማመን ደረጃ ከዜሮ በታች የሆነና በመጠራጠር የተሞላ መሆኑን ለመግለጽ መረጃም ማስረጃም ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ይህ የወረርሽኝ ወቅት ደግሞ ሁሉም ያለውን ጥርጣሬ ወደጎን በማድረግ በአቅሙ የቻለውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በደፈናው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና በርካታ ሀብት እንደተሰበሰበ ይነገራል፡፡ በአንጻሩም በአዲስ አበባ ብቻ በሽዎች በሚቆጠሩ ቀበሌዎች/አካባቢዎች የምግብ ባንኮች እንደሚከፈቱም ተገልጿል፡፡ ይህ እጅግ አበረታች ነው፤ ሕዝብ ግን ከዚህ ከፍ ያለ መረጃ ይፈልጋል፡፡ የተሰበሰበውን ሀብት መጠን ብቻ ሳይሆን የተገኘው በምን ጥቅም ላይ እንደዋለ፣ የምግብ ባንኮች እንደሚከፈቱ መስማት ብቻ ሳይሆን ተከፍተው ምን እያደረጉ እንደሆነ፣ ለምን ያህል ሕዝብ ምን ዓይነት ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ…ወዘተ መስማት ይፈልጋል፡፡ ሰምቶም የጎደለውን ለመሙላት ይበረታታል፤ ቀስ በቀስም ያለውን የመተማመን ደረጃ ከፍ ያደጋል፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላት በኮቪድ 19 ዙሪያ እየተደረገ ስላለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሪፖርት ለሕዝብ እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን፡፡ መቼም ቢሆን መቼ የዜጎችን መፈናቀል እናወግዛለን! ወረርሽኙን ተባብረን ለመከላከል እንሥራ!