April 27, 2020 1 min read
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ከዘመናት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት አርማ የነበረውን አንበሳን የጥላቻ ቃል አወረዱበት። አሁን ደግሞ ምስሎቹን ከቤተ መንግሥት አጥር በራፍ ላይ አንሥተው በጣዎስ ምስሎች ተኩበት። ፍጥረተ እግዚአብሔር የሆነውን አንበሳን ለምን እንደጠሉ የሰጡት ምክንያት ብዙዎቻችንን አላረካቸውም። አሁን ደግሞ ቦታውን ለምን ለጣዎስ እንደሰጡበት፥ ምክንያታቸውን ቢያረካንም ባያረካንም አልነገሩንም። አንበሳን እንዲህ የጠሉት ምን ቢያጠፋ ነው? አንበሳ እንደ ጣዎስና እንደሁላችንም እኩል የእግዚአብሔር ፍጡር ነው። አምላክ ሲፈጥረን የፈጠራቸውን አራዊትና እንስሳት ሌሎችንም ፍጥረታት አይቶ ሥራው እንዳስደሰተው መጽሐፍ ቅዱስ ቁልጭ አድርጎ መዝግቦልናል። ኅብስቱንና ወይኑን ወደቍርባን የሚለውጠው ጸሎታችንም ፥ “ንብል እንከ ከመ ኵሉ ሠናይ ፍጥረተ እግዚአብሔር” (እንግዲህ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ ቆንጆ ነው እንበል) ይላል። ስማቸው ባይጠራም የጣውስና የአንበሳ መፈጠር እኩል አስደስቶታል። የሚነፍሰው ዜና በአገሩ ውስጥ ያሉት የአንበሳ ምስሎች ሁሉ በአደጋ ላይ እንዳሉ ነው።
ከጊዜ በኋላ ሰዎች የያንዳንዱን እንስሳ አውሬ ባሕርይ እያዩ፥ መገለጫ አውጥተውላቸዋል። በእኛ ዘንድ ባሕርይ አይቶ መግለጫ ለመስጠት ዋናው ምንጭ “ድርሳን፡ ዘቅዱስ፡ ፊሳልጎስ” ነው። (ፊሳልግስ ማለት Physiology ማለት ነው ተርጓሚው የደራሲው ስም መስሎት ቅድስና ሰጥቶታል።) አንበሳን በጉልበት አሸናፊ ስለሆነ የአራዊት ሁሉ ንጉሥ ይሉታል። አሸናፊነቱም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሥጋ-በላና ፍሬ-በላ አድርጎ የፈጠረን ጎበዙ ደካማውን እንዲበላ ነው። አንበሳ ሚዳቆ አሳዶ፥ ካጋጠመው ሰውንም፥ ይበላል። እኛም የምናሸንፈውን በሬ በግ ፍየል ዶሮ አርደን፥ ሚዳቋ ድኩላ ጅግራ ቆቅ አድነን፥ ዓሣ አጥምደን እንበላለን። ምንም ልዩነት የለውም። ጣዎስም ሳትቀር በተሰጣት አቅም የምታሸንፈውን ትላትል ትለቃቅማለች። ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ እንዲበላ የቅዱስ አምላክ ዘዴ ነው።
አገሮች አንዳች ነገርን በምክንያት አርማቸው ያደርጋሉ። አርማ እንደባንዲራ ማንነትንና አንድነትን ይገልጣል። አሜሪካውያን ንስርን ሲመርጡ ካናዳውያን ሎተስ የምትባለዋን ቅጠል መርጠዋል። ሎተስ የካናዳውያን መታወቂያ ነች። አሜሪካ ማንም አይደፍረንም ስትል በንስር ታስፈራራለች። እኛ በአንድ በኩል አንደፈርም ለማለት፥ በሌላ በኩል ክርስቲያኖች ስለሆንን ከዘመናት በፊት አንበሳን መርጠናል። በአንድ በኩል የዮሐንስ ራእይ ከይሁዳ ነገድ የተወለደውን ክርስቶስን አንበሳ ስለሚለው፥ በሌላ በኩል አንበሳን የአራዊት ንጉሥ፥ ስለሚባል ማለት ነው። አንበሳ ሲመረጥ በሀገራችን ውስጥ ሌላ ሃይማኖት ያላቸውና ሃይማኖት የሌላቸው ዜጋዎች የሉም ማለት አይደለም። ሌላ ሃይማኖት ያላቸውና ሃይማኖት የሌላቸው ዜጋዎች የሚኖሩባቸው ብዙ የአውሮፓ አገሮች ባንዲራቸው ላይ መስቀል ያደርጋሉ። ከመንግሥት አጀማመር ታሪክ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስቲራችን ከአንበሳ ይልቅ ጣዎስን ለምን እንደመረጡ አልነገሩንም። ይኸም እትችት ጫካ ውስጥ ገብተን እንድንዋዥቅ አድርጎናል። አንዳንዴም ጠቅላይ ሚኒስቴራችንን የሚጎዳ ምክንያት ላይ እናርፋለን። በሕዝብ ቈጠራ ኩሻውያን ኦሮሞዎች ስለሚበዙ፥ የተጫነባቸው የሴማውያን ባሕል ተወግዶ፥ ገለልተኛ የሆነ ሕዝብን በሚወክል ምልክት ለማምጣት ነው የሚሉ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጣዎስ ባለብዙ ቀለም ላባ ስላላት ባለ ብዙ ነገዶችና ጎሳዎችን ስለምትወክል ነው ይላሉ። በአንድ ሰው ሥራ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ የአንድምታ ባህላችንን አዥጎደጐድንበት።
ምክንያቱ እውነት ይኸ ከሆነ፥ መሪያችን ዓለም ያወገዘውን የጎሰኝነት ፖለቲካን በማድረቅ ፈንታ የባሰውን እንዲያለመልም ውሐ ያጠጡታል ማለት ነው። ሌላውን ባይሰሙ፥ ለምን ያሁኖቹን የሱማሌ “ክልል” መሪዎችን ትምህርት እንደማይቀበሉ ግልጽ አይደለም። ጥረታችን የጎሳ አባላት በሚያኮራ በጉብዝናቸው እንጂ በጎሳ ማንነታቸው እንዲጠቀሙ መሆን የለበትም። “አማራ፥ ትግሬ፥ ኦሮሞ፥ ጉሙዝ፥ ወላይታ፥ ጉራጌ፥ ወዘተ. ስለሆንኩ ተራ ይድረሰኝ” ማለት ክብር-አልባ ልፍስፍስነተን መቀበል ነው።
ሌላም አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሞላ ኩሽ የሚባሉ ሕዝቦች ነው። እነሱም በሰሜን አገዎች፥ በደቡብ ኦሮሞዎችና ሌሎች የሚባሉ ኩሻውያን ናቸው። ሰሜኖች ሴማዊ የተባሉት አግዓዝያን በሚባሉ አናሳ ሴማውያን አማካይነት በደረሰን የሴማውያን ባህል (በተለየ ቋንቋውና ሃይማኖቱ) እንጂ ዘራችን ሴማዊ ስለሆነ አይደለም። አንድ ሕዝብ ሥልጣኔውን በሌላ ሕዝብ ባህል አማካይነት ማዳበር በኢትዮጵያ የተጀመረ አይደለም። የብዙ አገሮች ሥልጣኔ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሴማውያን ሃይማኖት (በክርስትና)፥ በሌሎች አገሮች ደግሞ በዓረብኛ ቋንቋ በሴማውያን ሃይማኖት (በእስልምና) ዳብሯል።
የተለመደና የተወደደን የሕዝብ ባህል ለማስጠበቅ ሕግ ባይወጣም፥ አዲስ መሪ በመጣ ቍጥር የሕዝብን ባህል እሱን በሚያስደስተው ባህል የመለወጥ በብት የለውም። አንበሳን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አይቶ ከመግፋት ይልቅ፥ ጎልማማ፥ ኩሩ፥ ምሉአ-ግርማ ኢትዮጵያዊ ፍጡር መሆኑን ለማየት የሚከለክለን ምክንያት አይኖርም።