April 29, 2020

Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/104417

ጌታቸው ኃይሌ
ፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን የሚቀጥለው ምርጫ ርቱዕ እንደሚሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ገብተዋል። ፈሪሀ እግዚአብሔር ስላለባቸው መጨረሻው እንደ መለስ ዜናዊ ቃል እንደማይሆን አምነናል። እግዚአብሔርን መፍራታቸውን ተማምነን ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብለን አምነናል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ፥ “ሳይቦካ ተቦካ” እንዲሉ፥ ምርጫው ሳይጀመር ርትዕነቱን በግላጭ እያበላሸው ነው። የፓርቲው መሪ የመንግሥትን ሥልጣን በመጠቀም ሕዝቡ ሙሉ ተስፋውን እፓርቲው ላይ እንዲጥል አድርገውታል። የመሪውን ሥልጣን በመፍራት ብልጽግና ፓርቲን እንጂ ሌሎቹን ከመስማት ተቆጥቧል። ለምሳሌ፥ የአቶ እስክንድር ነጋ ሰዎች ለእውነተኛ ፓርቲያቸው ቢሮ የሚሆን ቤት ለመከራየት ቢሞክሩ አከራይዋ በመፍራት፥ “ቤቴን ለናንተ አላከራይም” እንዳለች ሰምተናል።  ይኼ ደግሞ በተዘዋዋሪ ቢሆንም፥ ቃልን ከማጠፍ ብዙ አይለይም። በጓሮ ገቡ ፊት ለፊት ሁሉም አንድ ነው። እንዲህ ያለ ስሕተት የሚፈጸመው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚያደርጉትን እያወቁ ከሆነ፥ ቃልን ባለመጠበቅ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ያወዳድራቸዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ችግሩ ችግር መሆኑን አይተው፥ ሊያስወግዱትና ቃላቸውን የሚጠብቁ መሆናቸውን ለሕዝብ ለማሳየት፥ እኛም እንድናምናቸው ከፈለጉ መፍትሔ የሚሆን የሽማግሌ ምክር ልስጣቸው። በይፋ ወጥተው የሚቀጥለው ምርጫ ርቱዕ እንዲሆን የሕዝቡን እርዳታ በሚቀጥሉት ቃላት ዓይነት ይጠይቁ።

ፓርቲዎች ሁሉ የሚወዳደሩት ቢያሸንፉ ምን እንደሚያደርጉ በጽሞና አዳምጣችሁ የወደዳችሁን፥ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይህ ነው የምትሉትን የሚያሰማችሁን ምረጡ። ኢትዮጵያ የትላልቅ መሪዎች እናት ስለሆነች፥ የምትመርጡት ፓርቲ መሪም አገሪቱን ከማንም በማያንስ ደረጃ ይመራታል። ሁለተኛም በምርጫ ጊዜ ማስወገድ ያለብን ትልቁ ደንቃራ የመንግሥትን መሪ በመፍራት መምረጥ ነው። ፍርሀት የዲሞክራሲ ጠላት ነው። ዲሞክራሲን ለማንገሥ የሚደረገውን ጥረት ፍርሀት እንዳያበላሽብን ተግተን ዘብ መቆም ይኖርብናል። ፍርሀትን እምቢ በሉት፤ እውነትን እሺ በሉት። ሊሰብካችሁ የሚመጣውን በአክብሮት ተቀበሉት። ማማረጥ የምትችሉት የማማረጥን ዕድል በመጠቀም ነው። ምርጫና ገበያ አንድ ናቸው። ሻጪውን ፈርቶ ሸቀጡን የሚገዛ የለም። በምርጫ ጊዜ የሚፈራውና የሚከበር ሕዝብ እንጂ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች አይደሉም። ሕዝብ ቀጣሪ፥ ፓርቲዎች ለመቀጠር ተለማማጮች ናቸው።

ይህንን ሐሳቡን ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ለማቅረብ ያህል ጻፍኩት እንጂ፥ ሐሳቤን ከተቀበሉ፥ አማርኛውን ለማሳመር ማንም አይወዳደራቸውም።

በአጋጣሚው የተያያዘ ጉዳይ ለማንሣት፥ የምርጫው ጊዜ ከተራዘመ፥ የእርዝማኔውን ዘመን መንግሥት የሚያስተዳድረው ኀይል (የብልጽግና ፓርቲ ማለቴ ነው) ሙሉ ሥልጣን (mandate) የለውም። ሥልጣኑ ባለቤቱ በምርጫ አሸንፎ እስኪመጣ ድረስ እረኝነት ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ የዕለት ተለዕት የሚካሄደውን አልፎ ባለቤት ሊያደር ያለበትን ሥራ መሥራት አይችልም።