ሀብታሙ ግርማ
(በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር፤
ኢ–ሜይል፦ ruhe215@gmail.com)
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ከሰሞኑ በአክቲቪስቱ ናትናኤል መኮንን የፌስ ቡክ ገጽ ተለጥፎ ያነበብኩት በፕሮፌሰር መስፍን እና የአብን ከፍተኛ አመራር የሆነው ክርስቲያን ታደለ መካከል የተደረገ የቃላት ምልልስ የሚያሳይ ፖስት ነው፡፡ አንባቢ በዚህ ሊንክ ሊያገኘው ይችላል፦ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2860826690665766&id=812185372196585&ref=m_notif¬if_t=feedback_reaction_generic
ሁልጊዜም እንደምለው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በጥሩ የምሁር ተክለ–ስብዕናቸው የምሁርነት ልክን ያሳዩን ሰው እንደሆኑ ባምንም በፖለቲካ ተክለ–ስብዕናቸው ግን አይስማሙኝም። ምናልባት ፕሮፌሰሩ ያለፉበት ዘመን የተበላሸ የፖለቲካ ባህል የነበረው መሆኑ ተጽዕኖ አሳርፎባቸው ይሆናል።
ነገር ግን እኚህ ምሁር ለፖለቲካችን ያበረከቱትን በርካታ በጎ ተግባራትንም መርሳት ሃቃቸውን መውሰድ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የራሳቸውን ትግል አድርገው ብዙ ትሩፋትን አስገኝተውልናል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ አንዱ ገጽ የፖለቲካ ስልጣን የያዘው አካል በተገዳዳሪዎቹ ላይ የሚደርሰው የየዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆነ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር መስፍን በ1980 ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) በመመስረት እና ለረጅም አመታት በመምራት ለዜጎች የሰብዓዊ መብት መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
ኢሰመጉ ከሰራቸው ተግባራት መካከል የዝነኛውና ብርቅዬው ኢትዮጵያዊ የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስና ይመሩት የነበረው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) አባላት ላይ ይደርስ የነበረውን የግፍ እስር እና ስቃይ ለአለም ማጋለጡ እንዱ ነበር።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በማርቀቅ ሂደት ወቅት አንዱ አጨቃጫቂ ጉዳይ የሲቪክ መብቶች( የፖለቲካዊ መብቶች ጨምሮ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መብቶች) ከሰብዓዊ መብት ጋር የመጨፍለቅ አዝማሚያ የነበረበት መሆኑ ነው።
ይህ ነገር አንድም የህገ መንግስት እውቀት አለመኖር ሌላም ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ስልጣን ማደላደያነት ሰብዓዊ መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዳያገኝ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘዋሪዎች የተሸረበ ሴራ ነበር።
የሆነ ሆኖ ሰብዓዊ መብት ከሲቪክ መብቶች ተነጥሎ ለብቻ የመብት አይነት ተደርጎ እንዲወሰድና በህገ መንግስቱ እንዲካተት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር (በዚህ ረገድ የአቶ ክፍሌ ወዳጆ ሚናም ላቅ ያለ ነበር)።
በመሰረቱ የመናናቅ ፖለቲካ የ1960ዎቹ ትውልድ ስንክሳር ነው፤ ያ ትውልድ ብዙ በጎ ጎኖች ቢኖሩትም በፖለቲካ ባህል ረገድ ጥሎብን ያረፈው ጉድፍ ግን ለዚህ ትውልድ ዕዳ ሆኖ ዛሬም አለ። እንደ አቶ ታደለ በፖለቲካ ትግላቸው ራሳቸውን ከዚህ ሰንኮፍ አላቀው መጓዝ ይገባቸዋል። የወደፊቱ የፖለቲካ ቅኝት መደማመጥ እና መከባበር እንጂ መናናቅ እና መጠላለፍ መሆን የለበትም።
ከፖለቲካ አቃም አንጸር አቶ ክርስቲያን ታደለ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር የሰፋ ተቃርኖ ቢኖራቸውም ልዩነታቸውን በዚህ መልኩ በአደባባይ መግለጻቸውን አልወደድሁት፤ በሌላ በኩል ልጅ ከአባቱ ጋር ምንም ያህል ልዩነት ቢኖረው እንኳ አባትነቱን ሊክድ አይችልም፤ ልጅ አባቱን ማክበር አለበት፤ ይህን ክርስቲያን ታደለም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞች ያውቁታል።
ነገር ግን ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን የሆኑት መከባበር፣ ታላላቆቻችን ማድመጥና ከእነርሱ መማር ወዘተ እንዴት የፖለቲካ እሴቶቻችን ሊሆኑ እንዳልቻሉ ሁልጊዜ መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው።