በትግራይ ከመስከረም በፊት ምርጫ ማካሄድ የማይቻል ከሆነ ሕዝብ እንዲወስን እንደሚደረግ ሕወሓት አስታወቀ
የሕወሓት ሊቀ መንበርና የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)

17 May 2020

ዮሐንስ አንበርብር

በትግራይ ከመስከረም በፊት ምርጫ እንዲካሄድ ክልሉን የሚያስተዳድረው ሕወሓት መወሰኑን፣ ነገር ግን ምርጫውን ማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ የክልሉ ሕዝብ እንዲወስን እንደሚደረግ የፓርቲው ሊቀመንበር ገለጹ።

በሥልጣን ላይ የሚገኘው የትግራይ ክልል መንግሥት የሥልጣን ዕድሜ መስከረም 2013 ዓ.ም. እንደሚያበቃ የተናገሩት የድርጅቱ ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ አሁን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው ተራዝሞ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ፓርቲያቸው ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በትግራይ ክልል ከመስከረም ወር በፊት ምርጫ እንዲካሄድ ሕወሓት መወሰኑን ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። ይህ ውሳኔ የፓርቲያቸው የፖለቲካ አቋም ብቻ ሳይሆን፣ ክልሉ መንግሥት መሪ ከመሆኑ አንፃር የትግራይ ክልላዊ ብሔራዊ መንግሥት አቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ሰዓት ዓርብ ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት የክልሉ ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የለም። ‹‹ይህ ውሳኔያችን ለክልላችን ነው፤›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ እግረ መንገዳቸውንም ለፌዴራል መንግሥት የሕወሓትንና የክልሉን መንግሥት አቋም እያስታወቁ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንንም ሲያጠናክሩ ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. በኋላ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሥልጣን ስለማያበቃ ቅቡልነትም ሆነ ሕጋዊነት እንደማይኖራቸው፣ ስለሆነም በአገር አቀፍ ደረጃም ምርጫ ለማካሄድ አለመፈለግ አደገኛ ነው ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት በኮሮና ወረርሽኝና ለመከላከል ሲባል የሕዝብ ደኅንነትን ለመጠበቅ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት፣ በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረውን አጠቃላይ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል መወሰኑ ይታወሳል።

ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁ በሕዝብ የተመረጡ ምክር ቤቶች ምርጫ ተደርጎ እስኪተኩ በሥልጣን መቆየት ይችሉ እንደሆነ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ማቅረቡ አይዘነጋም።

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ነው ብሎ በግልጽ ደንግጓል። ይህ ሥልጣንም ለአምስት ዓመታት የሚያገለግል ነው ተብሎ በሕገ መንግሥትቱ በግልጽ ተተርጉሞ ተቀምጧል። ሕገ መንግሥቱ በዚህ ምክንያት ምርጫ ሊራዘም ይችላል የሚል አንቀጽ ቢኖረው ማየት ይቻላል፣ ከዚህ ውጪ ግን ሕገ መንግሥትን የማክበርና ያለማክበር ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ የፓርቲያቸውን የፖለቲካ አቋም ልዩነት አስታውቀዋል። ሕወሓት በትግራይ ክልል ምርጫ እንዲራዘም እንደማይፈልግ የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ሳንመረጥ በሥልጣን መቀጠል አንፈልግም፤›› ብለዋል።

በመሆኑም ከመስከረም በፊት በትግራይ ክልል ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን፣ አፈጻጸሙም የአገሪቱን ሕጎች መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ተናግረዋል። ይኼንን ለመተግበርም ምርጫውን የሚያስፈጽም ምርጫ ቦርድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በሕወሓት ውሳኔና ከትግራይ ክልል ምርጫን አስመልክቶ ለምርጫ ቦርድ የቀረበ ጥያቄ መኖሩን ለቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በስልክና በጽሑፍ መልዕክት የቀረበው ጥያቄ መልስ አላገኘም።

በ2012 ዓ.ም. በፀደቀው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162 አንቀጽ 7 (ሀ) ሥር ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ፣ ምርጫውም የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት በመምረጥ እንደሆነ ተደንግጓል።

በንዑስ አንቀጽ (ለ) ሥር ደግሞ፣ ‹‹ጠቅላላ ምርጫ በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል። ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ እንዲካሄድ ልናደርግ ይችላል፤›› የሚል ድንጋጌ ሠፍሯል።

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ከዚህ ጋር በተገናኘ መሆኑ በግልጽ ባይታወቅም፣ ‹‹ምርጫ ማድረግ አይቻልም ከተባለ ግን የክልሉ ሕዝብ እንዲወስን ምክክር እናደርጋለን፤›› ብለዋል። ምርጫ ማድረግ የማይቻል ከሆነ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምን ይሁን ብሎ የሥልጣን ባለቤት ከሆነው ሕዝብ ጋር በክልል ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን ምርጫው የኮሮና ቫይረስ ከሚያደርሰው ጉዳት በልጦ አለመሆኑን፣ በትግራይ ክልልም እስከ ነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ የቫይረሱ ሥርጭት ምን ደረጃ እንደሚያደርስ እንደማይታወቅ ገልጸዋል። ነገር ግን ምርጫ ይካሄድ የሚለው ውሳኔ የቫይረሱ ሥርጭትን በመታገል በጥንቃቄ ምርጫ ለማካሄድ እንደሆነ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ለብቻ ምርጫ ለማካሄድ የሚቻልበት የሕግ አግባብ ስለመኖሩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት መምህሩ አደም ካሴ (ዶ/ር)፣ ሕወሓት ቀደም ብሎ ካወጣው መግለጫ ምርጫ በወቅቱ ለማካሄድ ራስን በራስ የማስተዳደር መንግሥታዊ ድንጋጌን መጥቀሱን በማስታወስ፣ ይህ መብት በአስቸኳይ ጊዜ ባይገደብም መፈጸም የሚችል አለመሆኑን ይገልጻሉ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይገደቡ ተብለው በሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሱት አምስት አንቀጾች መካከል ሁለቱ የአንቀጽ 39 (1) እና (2) መሆናቸውን የገለጹት አደም (ዶ/ር)፣ እነዚህን መብቶች ወደ መሬት አውርዶ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችለው የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሦስት ግን በአስቸኳይ አዋጅ መገደብ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(1) ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መንገድ ያለገደብ የተጠበቀ እንደሆነ የሚደነግግ መሆኑም፣ ይህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይገደብ መሆኑን እንደሚያመላክት ያስረዳሉ።

በአንቀጽ 93(3) ሥር ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡና ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን እንደሚያጠቃልል ተደንግጓል።

ይህ አንቀጽ ራስን በራስ ለማስተዳደር መብት መተግበሪያና ተቋማዊነትን መመሥረቻ ቢሆንም፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገደብ የሚችል በመሆኑ የትግራይ ክልል ውሳኔ ተፈጻሚነት ከሕግ አንፃር የሚቻል እንዳልሆነ አደም (ዶ/ር) አስረድተዋል።