በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ውይይቶች የቀረቡ ሐሳቦችና አመክንዮዎች
የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላት በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ

20 May 2020

ብሩክ አብዱ

በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ውይይቶች፣ ክርክሮችና ድርድሮች መሠረት ለመጣል መልካም ጅምር ይሆናል የተባለለት በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ለሁለት ጊዜ ያህል የተካሄደው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መድረክ፣ ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ለመካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 8 እና 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄዱ ሁለት ዙር ውይይቶች፣ የሕገ መንግሥት ምሁራንና ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅና ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ የተሳተፉ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ 

በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ያስተናገዷቸው ሐሳቦችና አመክንዮዎች ሲዳሰሱ

ምንም እንኳን አገሪቱ ያለችበት የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም እያሉ የሚከራከሩ ወገኖች ቢኖሩም፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅቱን እያፋጠነ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ይኼ ዝግጅት ከበጀት እስከ ቁሳቁስና የሰው ኃይል አቅርቦት የሚዘረጋ እንደሆነ በመናገር የድምፅ መስጫ ቀን የቆረጠው ምርጫ ቦርድ፣ የዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት ሆኖ የተከሰተውና በኢትዮጵያም ሰዎችን በማጥቃት ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል ምክንያት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ በምክንያትነት በመጥቀስ፣ የምርጫ ዝግጅቱን በተባለው ጊዜ ማገባደድ እንደማይቻልና ምርጫው በሕገ መንግሥታዊ ገደቡ መሠረት ማድረግ እንደማይቻል በማስታወቅ ተጠሪ ለሆነለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ የቀሩትን ሥራዎችና አማራጭ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳዎችን የያዘ ሰነድ ለፓርላማው ካስገባ በኋላ ምን አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ በርካቶች የተወያዩበት፣ አስተያየታቸውን ያጋሩበት፣ ጽሑፎችን ያስነበቡበትና ንግግሮች ያደረጉበት ሲሆን፣ መንግሥት አራት አማራጮችን አቅርቦ የተፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት ያስችላል ያለውን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መርጧል፡፡ ከዚህ ውጪ የተቀመጡት አማራጮች ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፣ ፓርላማውን መበተን ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አራዝሞ ማወጅ የሚሉት ነበሩ፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሥልጣን ገደቡ በአምስተኛ ዓመቱ የሚጠናቀቀው አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው ሲያበቃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የአስፈጻሚው አካልም አብሮ ሥልጣኑ ስለሚያበቃ፣ ምርጫ መደረግ ሲገባው በወረርሽኙ ሳቢያ በማይደረገው ምርጫ ሳቢያ የሚፈጠረውን የሥልጣን ክፍተትና መንግሥት አልባነት ለመፍታት ያስችላል የተባለውም፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ ተልኳል፡፡

መንግሥት ያቀረባቸው አራቱም አማራጮች አራት ሳይሆኑ፣ ‹የራሴን ሥልጣን እንዴት አራዝሜ ልቆይ› በሚል የተነሱ ስለሆነ አንድ አማራጭ ብቻ ነው የቀረበው በማለት መንግሥትና ተቃዋሚው በጋራ ተወያይተው የሽግግር መንግሥት ወይም ምክር ቤት ተቋቁሞ የምርጫ ዝግጅት ይደረግ ሲሉ የሞገቱ ቢኖሩም፣ መንግሥት የመረጠው አማራጭ የተመራለትና የትርጉም ሥራ ጥያቄ የቀረበለት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን በመጋበዝ በጽሑፍና በአካል ማብራሪያዎችን አስተናግዷል፡፡

ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመርያውን የባለሙያዎችን ውይይት ያደረገው ጉባዔው ሁለተኛውንና የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ አባላትን፣ የሕገ መንግሥት አፅዳቂ ምክር ቤት አባላትን፣ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎችንና ምሁራንን በማሳተፍ ሕገ መንግሥቱ ሲዘጋጅ የነበሩ አስተሳሰቦችንና አሁን ከተፈጠረው ችግር አንፃር በወቅቱ የተደረጉ ውይይቶች ከነበሩ ለመጠየቅ፣ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ውይይት አድርጓል፡፡ በእነዚህ ውይይቶች በዋናነት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ያስፈልጋል የሚሉ መደምደሚያዎች ተደምጠዋል፡፡ የተለዩና  መንግሥትም ሥልጣኑ ሳያበቃ ምርጫ ያድርግ የሚሉ ሐሳቦች ያልተደመጠባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ በዚህ ዘገባ በተለይ በሁለተኛው የውይይት መድረክ ላይ የተነሱ ሐሳቦችና ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡

በሁለተኛው መድረክ በዋናነት የተሳተፉት ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ የተሳተፉና ያፀደቁ እንዲሁም ሙያዊ ዕገዛ ያደረጉ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ በዚህ ረገድ ተሳትፎ ያልነበራቸው የተወሰኑ ባለሙያዎችም ከሕገ መንግሥት መርሆና ከምሰሶዎቹ አንፃር ትንታኔና ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

በጉባዔው ሰብሳቢ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና በጉባዔው ምክትል ሰብሳቢ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አረዳ፣ እንዲሁም የጉባዔው አባላት በሆኑት ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ ወ/ሮ ደስታ ገብሩና ወ/ሮ ዑባህ መሐመድ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡

የመጀመርያው ባለሙያና ተጠያቂ የነበሩት አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) የሕገ መንግሥቱን ፍልስፍናዊ መሠረት ተጠይቀው ያብራሩ ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ራስ ገዝነትንና የተገደበ የመንግሥት ሥልጣንን እንደሚያስከብር፣ ለሕዝብ ሉዓላዊነት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥና ሕዝብ በራሱ ቀጥተኛ ተሳትፎና በመረጣቸው ተወካዮች በተሰጣቸው ገደብና ሥልጣን ለሕዝብ ተጠሪ እንዲሆኑ ይጠይቃል በማለት፣ ለቡድንና ለግለሰብ መብቶች ዕውቅና የሚሰጥ፣ የመንግሥት ሥልጣን በአንድ አካል እንዳይከማች የሥልጣን ክፍፍልን የሚፈጥር፣ እንዲሁም ለሕዝቦችና ለብሔረሰቦች ከፍተኛ ነፃነት የሚሰጥ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥትን ለመተርጎም የሚያግዙ የተለያዩ ሥልቶችን ልምረጥና ልከተል ማለት እምብዛም እንደማይጠቅምና የተለያዩ ሥልቶችን ወደ ጎን በመተውና ተግባሩ ላይ የማይገቡ መሆናቸውን በመረዳት ተጨባጭ ሁኔታውንና ሕገ መንግሥቱን በተናጠል አንቀጾቹን ሳይሆን ሙሉ ሰነዱን በጠቅላላው በማየት የሚጠቅም ሐሳብ ላይ መድረስ ይበጃል በማለት፣ ወቅታዊ ጉዳይ ላይና ሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፊው ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ቅዳሜ (ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም.) ሐሳብ ያቀረቡ ባለሙያዎች ከኮሮና ወረርሽኝ መከላከያና መጠንቀቂያ በማዘጋጀት ሕዝቡን መንግሥት እንዲጠብቅ በማሳሰብ ባልተመረጠ መንግሥት ሥልጣንን ላልተገደበ ጊዜ አገሪቱ መተዳደር ከሌለባት በዓመት ወይም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይደረግ የሚል ሐሳብ እንደተረዱ፣ ይኼም ከሕዝብ ሉዓላዊነት ጋር እንደሚገናኝ እንደሚረዱና እንደሚስማሙበት በመግለጽ፣ ችግሮች ያሉበት አስተሳሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ፍቱን ክትባት ያልተገኘለት የኮሮና ወረርሽኝ ለዓመትና ለሁለት ዓመት የሚወገድ እንዳልሆነ ከግንዛቤ በማስገባት፣ በዚህ ጊዜ ምርጫ ይደረግ ከተባለ ወረርሽኙ እያለ ነው የምናደርገው ማለት ነው፡፡ ይሁንና አሁን ለአስቸኳይ ጊዜ መታወጅ ሰበብ የሆነው ወረርሽኝ እያለ አይደረግም ከተባለ ደግሞ ባልተመረጠ መንግሥት ለዓመታት እንመራለን ማለት ነው፤›› በማለት ይኼ ትልቅ ችግር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

‹‹ላልተወሰነና ለረዥም ለዚያውም በራሱ በመንግሥት በሚመረጥ ጊዜ፣ ባልተመረጠ መንግሥት እንተዳደራለን ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይኼ የሕዝብ ተቀባይነትን ማግኘት አለበት፡፡ ማናችንንም እንሠጋለን ሕዝብም፣ ክልልም፣ ዜጋም፡፡ አንዱ የሕገ መንግሥት መርሆ መንግሥት የሥልጣን ገደቡን ራሱ መወሰን አይችልም የሚል ነውና ይኼ ጥያቄ ሊፈታ ይገባል፤›› ሲሉ አንድርያስ (ፕሮፌሰር) አሳስበዋል፡፡ ስለዚህም ይኼ በመንግሥት መወሰኑስ በተቃዋሚዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኝ እንደሆነም ጠይቀዋል፡፡

የበሽታውን ክብደት ለመረዳት ከሌሎች አስቸኳይ ጉዳዮች አንፃር ማስተያየት እንደሚገባ በማስገንዘብ የኖቤል የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሸላሚ ህንዳዊው አማርትያ ሴን ካሳተሟቸው ከ100 በላይ መጻሕፍት በአንዱ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተከሰተውን ድርቅና ረሃብ አጥንተው ያስቀመጡትን መደምደሚያ አውስተዋል፡፡

እኚህ ጸሐፊ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ በማጥናት ረሃቡ የተከሰተው ነፃ ጋዜጠኝነትና ዴሞክራሲ ባለመኖሩ ነው በማለት እነዚህ መብቶች ባለመኖራቸው ሳቢያ በአጭሩ መቀጨት ሲቻል ሊቀጭ አልቻለም ነበር እንዳሉ የተናገሩት አንድርያስ (ፕሮፌሰር)፣ እንዲህ ያለ ችግር ሲከሰት የመንግሥትን ደራሽነትና ተጠያቂነትን የበለጠ ይጠይቃል ይላሉ ብለዋል፡፡

‹‹እኔ ወረርሽኙ ቢኖርም ነፃ ጋዜጠኝነት ይኑር ሳይሆን፣ እንዲያውም ወረርሽኙ ስላለ ነው የሚያስፈልገን፡፡ ደዌው ስለሚያስጨንቀን መንግሥትን ተጠያቂ ብናደርግ ይጠቅመናል እላለሁ፤›› ሲሉ ደምድመዋል፡፡

ይኼንን ለማብራራት ከቆይታ በኋላ የተመለሱት አንድርያስ (ፕሮፌሰር)፣ አሁን ያጋጠመውን ችግር ለመመለስ የሚያስችል ነጠላ አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ የለም  በሚለው ሐሳብ እንደሚስማሙና ከሌሎች መርሆዎች ጋር አያይዞ ካለው ችግር ጋር ለማስማማት መሞከር እንደሚሻል በመምከር፣ ‹‹እንደ አማርትያ ሴን የወሎ ድርቅ ድምዳሜ ነፃና ገለልተኛ ጋዜጠኛና ዴሞክራሲ አለመኖሩ ሕዝቡን አልበጀውም ቢባልም፣ አሁን ባለንበት ሁነታ ምርጫ ሀብትም ጉልበትም ስለሚጠይቅ ቶሎ ማድረግ ላይቻል ይችላል፡፡ ግን ገደብ ተበጅቶለት ለነፃ ምርጫ ከአሁኑ ዝግጅት መጀመር አለብን፤›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውን ሕገ መንግሥት በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉት ሌላው አስተያየት ሰጪ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፣ በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት ምርጫን ብቻ መነሻ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን መሆን እንዳለበት ውይይት መደረጉን እርግጠኛ ባይሆኑም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከተው ረቂቅ አንቀጽ ላይ ግን ምርጫ ላይደረግ እንደሚችል እንዲደነገግ አንድ አባል አውስተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ ይኼንን መደንገግ ምርጫን ላለማድረግ ቀዳዳ ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ምርጫን በአስቸኳይ አዋጅ ጊዜ የግድ ማድረግን የሚደነግግ እንዲሆን በተነሳ ሌላ ክርክር ሳቢያ ሁለቱም አስፈላጊ አይደሉም ተብለው በሕገ መንግሥቱ ሳይካተቱ እንደቀሩ ገልጸዋል፡፡

ምርጫ ባለመኖሩ የሚፈጠርን የሥልጣን ክፍተት በተመለከተም፣ ራሱን የቻለ ውይይት በዚህ ላይ ባይደረግም ያሉት ተወካዮች ተመራጭ በመሆናቸው ሌላ ተወካይ እስከሚመጣ ክፍተት አይኖርም የሚል ሐሳብ በውይይቱ እንደተነሳና ለዚህም ምክንያቱ የሥልጣን ገደብ አለቀ ማለት ክፍተት አለ ማለት እንዳልሆነ፣ የመመረጣቸውን ሁኔታ እንደማይለውጡበት፣ እንዲሁም የሚረከባቸው ተወካይ እስከሚመረጥ ድረስ በሥልጣን ቢቆዩ ብዙም ክፍተት እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡

ስለዚህም ትርጓሜ እንደ መዝገበ ቃላት መታየት የለበትምና የመተርጎሙ ሥራ ሥልጣን ለተሰጠው አካል እንዲተው በመግለጽ፣ ‹‹የገጠመውን ችግር ለመፍታት በትርጓሜ ሥልጣን ማራዘም የሚቻልበት ሁኔታ እርካታ (Satisfaction) ይሰጠኛል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ሐሳብ ሰጪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደርና የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ አባል የነበሩት አቶ ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ በሕገ መንግሥቱ ሥሪት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ ወቅትና ምርጫ ሲገጣጠሙ ምን ይደረግ የሚል ውይይት መደረጉን በማስታወስ ያስረዱ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት ላይ አምስት ጉዳዮች መነሳታቸውን አውስተዋል፡፡

የመጀመርያው በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 93 መሠረት የተዘረዘሩት እንደ አገር ሉዓላዊነት መደፈር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ መውደቅና በሽታ የመሳሰሉት ችግሮች ሲኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ውይይት ተደርጎባቸው፣ ለምሳሌ ድርቅ ቢነሳ ሰው ሠራሽ ነው የተፈጥሮ ችግር በሚል ሐሳብ ‹‹የመሳሰሉት›› የሚል ሐረግ ተጨምሮ፣ እነዚህ ሲከሰቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያስችላል ተብሎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡  ይሁንና ‹‹የመሳሰሉት›› ማለት መቋጫ የሌለው ችግር ነው ተብሎ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚታገዱ መብቶች የትኞቹ ናቸው የሚል እንደሆነ በመግለጽ፣ ረቂቁ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የፖለቲካዊ ሥልጣን እስከ ማገድ ድረስ ይደርስ ነበርና ተለይተው ይቀመጡ የሚለው እጅግ አከራካሪው ጉዳይ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና አሁን በፀደቀው ሕገ መንግሥት ውስጥ ያሉ አንቀጾች በረቂቁ እንዳልነበሩ አሳስበዋል፡፡

ሦስተኛው ጉዳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወታደራዊ ተቋማት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል የሚለው ጉዳይ ሲሆን፣ በዚህ ሳቢያ ወታደራዊ ኃይሉ ከሥልጣን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳብቦ ሕገ መንግሥት እስከ መቀየርና ማሻሻል ሊደርስ ይችላል በሚል አስተሳሰብ የጋለ ክርክር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ በአራተኛነት የገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆይበት ጊዜና የሚራዘምበት የጊዜ ገደብ ሲሆን፣ አንዴ ከታወጀ በኋላ ከተራዘመ ለስድስት ወራት በምክር ቤት ይራዘማል ተብሎ እንደነበር፣ ኋላ በፀደቀው ሕገ መንግሥት አራት ወራት ተብሎ እንደወጣ ገልጸዋል፡፡ ይኼም ለአስቸኳይ ጊዜ ምክንያት የሆነው ጉዳይ በቶሎ እንዲፈታና ደጋግሞ ማወጀ እንዳይለመድ ለመከለካል ነው ብለዋል፡፡

አምስተኛው የአምባሳደሩ ነጥብ አሁን እንደ ተከሰተው ዓይነትና ያልተገመተ ሁኔታ ያገናዘበ ውይይት ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ከምርጫ ጋር ቢገጣጠም ምን ይሆናል ሲሉ አንድ የሕግ ባለሙያ በወቅቱ መጠየቃቸውን በማስገንዘብ፣ እነዚህ ሁኔታዎች እጅግ ያልተለመዱ (Extremely Extraordinary) በመሆናቸው ሊያጋጥሙ በማይችሉ (Exceptional) ሁኔታዎች ድንጋጌ ማስያዝ አያስፈልግም የሚል ውይይት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ተዓማኒነት እንዲኖረውና የሥልጣን ቅብብሎሹ መልክ ባለው መንገድ በተገደበ ጊዜ በሚደረግ ምርጫ እንዲኖር የታሰበበት እንደሆነ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የሥልጣን ክፍተት ይኖራል ብለው አስበው እንደማያውቁ በመጠቆም፣ በሕገ መንግሥቱ እንደ ተተለመው አግባብነቱን ለመፍታትና ለመተርጎም የሚያስችሉ አንቀጾች ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡ ስለዚህም መተርጎም ይችላል ሲሉ አክለዋል፡፡  

ሌላው አስተያየት ሰጪ በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ላይ ሕዝብ ያወያዩት ተሰማ ጋዲሳ (ዶ/ር) ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን በውርስ፣ በንጥቂያ (በጉልበት) እንዳይተላለፍ እንደሚገድብና በምርጫ እንዲሆን ማድረጉን፣ ይኼም በየአምስት ዓመታት መከናወን እንዳለበት በመግለጽ፣ አሁን ያለውን ዓይነት የምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መገጣጠም በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ውይይት ወቅት መነሳቱን በመጠቆም፣ ምርጫ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አንቀጽ 54 እና አንቀጽ 55 አስገዳጅ ድንጋጌዎች ሆነው ለዚህ ክፍተት ላለመስጠት ዓላማ እንደነበረው ያሳያል ብለዋል፡፡

ለዚህ መፍትሔውም ሕገ መንግሥቱ የግድ በምሉዕነቱ መታየት እንዳለበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ስለሚገድብ፣ እንዲሁም ምርጫ ከእነዚህ መብቶች አንዱ ስለሆነ እንደሚራዘም በማስታወቅ፣ ሥልጣኑን ግን ማን ይዞ ይቀጥል የሚለው ዋና ጥያቄ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በምርጫ ቦርድ በጋራ በትብብር ይወሰን ብለዋል፡፡ ስለዚህም በአንቀጽ 60 መሠረት መንግሥት ሕግ ሳያወጣ ለምርጫ ቢዘጋጅ ብለዋል፡፡

ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1987 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥቱ ጸሐፊ የነበሩት ተስፋዬ ሐቢሶ (አምባሳደር)፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበሩት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ማርቲን ኤለንና ሳሙኤል ሐንቲንግተንን በጉዳዩ ላይ ሲያወያዩ፣ ‹‹ተራማጅ ሁኑ፣ ፖለቲካዊ ትክክለኛነት የሌለውን ሐተታ እንዳታስቀምጡ፣ ሕገ መንግሥት ቢኖራቸውም ከጥቂት አገሮች በስተቀር ሕገ መንግሥታዊነት የለምና አስፈጻሚው አካል ከሕገ መንግሥቱ በላይ ይፈራል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥት አሻሽላችሁ ሂዱ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያኔ ቢቀናቀኑም ልክ አይሆኑምና ቅድሚያ ለሕዝቡ ደኅንነት መሆን አለበት፤›› ብለውኛል በማለት ተናግረዋል፡፡

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ጸሐፊዎች (ራፖርተር) አንዷ የሆኑትና የሰብዓዊ መብት፣ የአስተዳደርና የሕግ ምሁር የሆኑት ወ/ሮ መስከረም ገስጥ፣ ሕገ መንግሥት መነሻውም ግቡም ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ እንደሆነ በማስመር፣ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም መነሻው የሰብዓዊ መብት ማዕቀፍ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በሕገ መንግሥት ከሚወሰዱ ግንዛቤዎች አንዱ በምርጫ ተቀባይነት አግኝቶ የመጣ መንግሥት አለ የሚለው ነው በማለት፣ በመደበኛው መንገድ መመረጥና ለሌላው ማስረከብ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከዓላማው የሰብዓዊ መብቶችን ለመጠበቅ ስለሆነ፣ አሁን ያለውን ልዩ (Exceptional) በሆነ መንገድ ማስቀጠል ይሻላል፡፡ ነገር ግን ለምርጫ ዝግጅት እየተደረገ ይሁን በማለት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሚያስኬድ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በዚህ መንገድ ሥልጣን ላይ የሚቆይ መንግሥት መደበኛ የሆነ የሕግ ማስከበርና ሌሎች ተግባራትን ከማከናወን በዘለለ ሕጎችን ባያወጣና ሌላ ዕርምጃዎችን ባይወስድ ይመረጣል ብለው፣ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያላቸው ፋይዳ እየታየ እንዲሆንና ምርጫም በቶሎ እንዲደረግ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይኼ ውይይት ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚቀጥል ሲሆን፣ በሐሙሱ መድረክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የጤና ሚኒስቴር አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡

በርካቶች ይኼ ሒደት ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሒደት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመግለጽ፣ አሳታፊና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ አግባብ መታየቱ ይደነቃል ያሉ ሲሆን፣ ለየት ያሉና በተቃራኒው የቆሙ ድምፆች አለመሰማታቸው ቅር እንደሚያሰኝና ሒደቱንም ጎደሎ እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡