ትናንትና ከጤና ሚንስቴርና ከምርጫ ቦርድ ተብየው ኃላፊዎች መሰማት (hearing) እንደተረዳቹህት የጤና ሚንስትር ወረርሽኙ በዚህ ጊዜ በቁጥጥር ስር ይውላል! ብሎ መተንበይ የሚቻልበት ሁኔታ የለም!” በማለቱ፣ የምርጫ ቦርድ ደግሞ ሁለት የቢሆን ግምቶችን (scenarios) በማስቀመጥ “1ኛው. ኮቪድ በቁጥጥር ስር የሚውል ከሆነ ምርጫ ለማኪያሔድ በቁጥጥር ስር መዋሉ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ የሚቆጠር የዐሥር ወራት የዝግጅት ጊዜ ያስፈልገኛል፡፡ 2ኛው. ኮቪድ የማይጠፋ ከሆነና ነገር ግን ስርጭቱ ቀንሶ አዲስ ተለምዷዊ ሁኔታ (the new normal) ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሥቶ ከጥንቃቄ ጋር ምርጫ ማድረግ ይቻላል!’ ከተባለ ደግሞ ምርጫ ለማኪያሔድ ይሄ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ የሚቆጠር የዐሥራ ሦስት ወራት የዝግጅት ጊዜ ያስፈልገኛል!” በማለት አስታውቀዋል!!!

ጥያቄው የአገዛዙ ሕገመንግሥት አገዛዙ የሕዝብን ድምፅ ዘርፎ አሸነፍኩ!” በማለት ይዞት የነበረው ሥልጣን መስከረም 25,2013.. እንደሚጠናቀቅና አገዛዙ ከዚያች ቀን ጀምሮ በሕዝብ ባልተመረጠበት ሁኔታ ለአንድም ቀን ቢሆን በሥልጣን ላይ መቆየት የማይችል መሆኑን በማያሻማ መልኩ የደነገገ በመሆኑ የጤና ሚንስቴርና የምርጫ ቦርድ ተብየው የገለጹት ሁኔታ እስኪደርስ ድረስ የመንግሥት ሥልጣን በማንና በምን ሁኔታ ተይዞ ይቆይ???” የሚለው ነው!!!

አገዛዙ ኢፍትሐዊ በሆነ ሒደት ይሄንን የሦስት ቀን የመሰማትን (hearing) ሐሳብ በግብአትነት በመጠቀም በምንደኞቹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዳኞች ድጋፍ ሰጭ ጉባኤ ሕገመንግሥቱ ላይ ያልተጻፈ ነገር አስነብቦና አስወስኖ ሥልጣኑን ለማራዘም የቀረው ነገር ቢኖር ይሄንን የምንደኞች ቡድን ምርጫ እስኪከናወን ጊዜ ድረስ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የመቆየት ሕገመንግሥታዊ መብት አለው!” አስብሎ ማሳወጅ ብቻ ነው!!!

እንደሚመስለኝ እንደምታዩትም አገዛዙ ይሄንን ፍላጎቱን ከመፈጸም አንዳችም የሚያደናቅፈው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ተቃዋሚዎች እንዳይቃወሙና ሕዝብን ለተቃውሞ በመጥራት ጫና ማሳደርና ይሄንን የአገዛዙን ሕገወጥና ኢፍትሐዊ ጥረት ማስቆም እንዳይችሉም ከአራት ሰው በላይ መሰባሰብ አይቻልም….!” ብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጠናቀቅም እንደገና በማራዘም ከሕዝብ ሊቀርብ የሚችለውን ተቃውሞ አፍኖ እስከፈለገው ቀን ድረስ ለመድረስና ምርጫውን በራሱ እጅ አከናውኖ እንደለመደው የሕዝብን ድምፅ ዘርፎ አሸነፍኩ!” ብሎ በማወጅ ቀጣይ የአገዛዝ ዘመኑን ለመቀጠል አስቧል ወይም ተዘጋጅቷል!!!

ተቃዋሚዎችም ሕዝብን ለተቃውሞ ላለመጥራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሳይሆን ኮቪድ 19ኝን ወረርሽኝ ሰበብ የሚያደርጉ ይመስለኛል፡፡ ቁርጠኛና ሐቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲና ፖለቲከኛ ካለ ግን ኮቪድ 19 ከሚያደርሰው ጉዳትና አደጋ ይልቅ አገዛዙ በሕዝብና በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት፣ አደጋና ጥፋት ሽህ ጊዜ እጥፍ ይበልጣልና አገዛዙ ሕገወጥና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሥልጣኑን አራዝሞ ላልተወሰነ ጊዜ ሳይመረጥ ለመግዛት የሚያደርገውን ጥረት ሕዝብን ለተቃውሞና ለአድማ በመጥራት ለማስቆምና በግልጽና በሕዝብ ነጻ ተሳትፎ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ደጋፊ ባልሆኑና ከየትኛውም የጎሳ ፖለቲካ ጋር ባልወገኑ ገለልተኛ ምሁራን የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ በዚሁ የሽግግር መንግሥት የዲሞክራሲ ተቋማት ተገንብተው ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ተኪያሒዶ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣኑን እስኪይዝ ድረስ ይህ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን እንዲያሥተዳድር ለማድረግ ሕዝብን ይዞ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ መታገል ይኖርበታል!!!

እንዲህ ዓይነት ቁርጠኛ የአቋምና የመርሕ ተቃዋሚ ፓርቲም ሆነ ፖለቲከኛ አለን ወይ??? ነው ጥያቄው!!!

መልሱን ተቃዋሚ ነን፣ ፖለቲከኛ ነን!” ለሚሉትና ለሕዝቡ እተወዋለሁ!!!

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው ጥብቅ መልእክት ቢኖር ግን አገዛዙ በዚህ ሕገወጥና ኢፍትሐዊ መንገድ ሥልጣኑን ማራዘም ከቻለና ቀጣዩ ምርጫ እሱ በፈለገው ጊዜ በእሱ እጅ የሚካሔድ ከሆነ ሌላ ዙር የወያኔ/ኢሕአዴግ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሥርዓት ላይ እንደምትወድቅ ዕወቅ!!! ይሄ እንዳይሆን የምትፈልግ ከሆነ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመህ ይሄንን አረመኔ አገዛዝ ለመገላገል ከወዲሁ ተሟሟት!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው