
10 June 2020
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስወገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡ በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር፣ ለአካባቢውም ሆነ ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ሊሆን ይችላል ያለውን አደጋ ለመቀልበስ የበኩሉን እንዲወጣ ክልሉ በጻፈው ደብዳቤ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ገዥው መንግሥት በያዘው አካሄድ መጓዙን የሚቀጥል ከሆነ አደጋው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ወደ ፖለቲካዊ፣ የደኅንነትና የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ሊያሰምጥ ይችላል በማለት ክልሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቅርቧል፡፡
በአገሪቱ የተጋረጠውና አጠቃላይ ቀጣናውን ወደ አለመረጋጋት ሊከት ይችላል በማለት የዘረዘራቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግን አፍርሶ በብልፅግና ፓርቲ መተካት፣ የሕገ መንግሥት ጥሰትና ምርጫን ማራዘም የሚሉት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው ብሏል፡፡
ኢሕአዴግን አፍርሶ በብልፅግና ፓርቲ የመተካቱ ሒደት ደም አፋሳሽ ያልሆነ መንግሥት ግልበጣ ሊባል እንደሚችል አስታውቆ፣ ‹‹እንደ ሕወሓትና ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች ብልኃት የተሞላበት አካሄድ ባይሆን ኖሮ፣ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ የሥልጣን መቆናጠጥ ወደ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያመራ ይችል ነበር፤›› ሲል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረበው ባለ አሥር ገጽ አቤቱታ አስታውቋል፡፡
‹‹ይህ ሥልጣን የተቆናጠጠው ኃይል ይህን ብስለት የተሞላበት ፖለቲካዊ አካሄድን እንደ ድክመት በመቁጠር፣ በከፍተኛ ዋጋ የተገነባውን ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ማፈራረሱን ቀጥሎበታል፤›› ሲል የትግራይ ክልል ከሷል፡፡
በዚህም ምክንያት በግልጽ የክልል መንግሥታትን በማፈራረስና ባለሥልጣናትንና ኃላፊዎችን እንዳሻው በመሾም፣ በማንሳትና በመፐወዝ መጠመዱን ክልሉ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘንድሮ መካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ምርጫ በብቸኝነት እንዲራዘም በመወሰን፣ ሕገ መንግሥቱን ማዛባቱን ቀጥሏል ሲልም አክሏል፡፡
አሁን እየተካሄደ ያለው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሒደት፣ የራስን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት የተደረገና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ የጣሰ መሆኑን ገልጿል፡፡
‹‹በሥልጣን ላይ ያለው አካል በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ የሥልጣን ዘመኑን ማራዘም እንደሚችል የሚከራከርበትም ሆነ የሚያስረዳበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ አቋምም ሆነ ባህርይ የለውም፤›› በማለት የሚወቅሰው የትግራይ ክልል፣ በሥልጣን ላይ ያለው አካል ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕገ መንግሥቱን የሚጠቅሰውና ዋቢ የሚያደርገው በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚጠቅመው ከሆነ ብቻ ነው ብሎ፣ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ የሚለውን ስሞታ ደግሞ አሰምቷል፡፡
ያለፉትን ሁለት ዓመታት ለምርጫ መዘጋጀት ሲገባ መባከኑን የሚገልጸው የትግራይ ክልል፣ ‹‹አሁን ደግሞ ኮሮናን እንደ አሳማኝ ምክንያት በመጠቀም ከእነ አካቴው ምርጫውን ሰርዞታል፡፡ በዚህም ሳቢያ የፌዴራል መንግሥቱ ተዓማኒነቱን አጥቷል፤›› ብሏል፡፡
እነዚህን ሁሉ ጥፋቶች በተመለከተ ሥጋቱንና የመፍትሔ አቅጣጫውን በተደጋጋሚ ለሕዝብ እንዲደርስ አድርጌያለሁ የሚለው የትግራይ ክልል፣ ‹‹በፌዴራል መንግሥት ጆሮ ዳባ›› መባሉን አስታውቋል፡፡
‹‹አገሪቱ ከገጠማት ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመታደግ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ከብልፅግና ፓርቲና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት የድርሻውን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ያስታውቃል፤›› ሲል በደብዳቤው አሥፍሯል፡፡
ሆኖም እንዲህ ያለ ድርድር የተደረሰበት ፍኖተ ካርታ ባለመኖሩ የተነሳ፣ የክልሉ መንግሥት በትግራይ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲከናወኑ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ክልላዊ ምርጫውም በሕገ መንግሥቱ መሠረትና የኮሮና ወረርሽኝን መከላከልን ወደ ጎን ሳይደረግ የሚከናወን እንደሚሆንም አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡