13 ጁን 2020 – BBC Amharic

ከመጠን ያለፈ ውፍረት የልብ ህመምን፣ ካንሰርንና የስኳር ህመምን ለመሳሰሉ የተለያዩ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ይታወቃል።
በተቸማሪም ከመጠን ያለፈ ውፍረት በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እያስጨነቀ ለሚገኘው ኮቪድ-19 ያለን ተጋላጭነት ከፍተኛ ሊያደርገው ከመቻሉ በተጨማሪ በጠና መታመምንም ሊያስከትል እንደሚችሉ ይነገራል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ለምንድነው?
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለኮሮረናቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚያደርግ ሳይሳዊ ማስረጃ አለ?
እንግሊዝ ውስጥ 17ሺህ የሚሆኑ በኮቪድ-19 ምክንያት ሆስፒታል የሚገኙ ታማሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው ታማሚዎች ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የመሞት እድላቸው በ33 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
አንድ ሌላ ጥናት ደግሞ በተመሳሳይ ከፍተኛ ውፍረት የሚታይባቸው ሰዎች በቫይረሱ የመሞት እድላቸው በእጥፍ ከፍ ያለ እንደሆነ አስቀምጧል።
በተጨማሪም ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡት እንደ የልብ በሽታ፣ ካንሰርና ታይፕ [አይነት] 2 የስኳር በሽታን የመሳሰሉ ህመሞች ሲጨመሩበት ደግሞ ተጋላጭነታቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል ይላሉ ተመራማሪዎች።
እንዲሁ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከፍተኛ ክትትል ክፍል ውስጥ ከገቡ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች መካከል 34.5 በመቶ የሚሆኑት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሲሆን 31.3 በመቶዎቹ ደግሞ እጅግ በጣም ወፍራም የሚባሉ ናቸው።
የዓለም ውፍረት ፌደሬሽን እንዳስታወቀው በመላው ዓለም ያለውን የውፍረት ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው መሆናቸውን መገመት ይቻላል ብሏል።
በአሜሪካ፣ በጣልያን እና በቻይና ውስጥ የተደረጉ ጥናቶችም ይህንኑ ነው የሚያሳዩት።
በቅርቡ በተሰሩ ጥናቶች መሰረት ደግሞ የእድሜ መግፋት፣ ወንድ መሆንና ከመጠን ያለፈ ውፍረት መኖር ለኮቪድ-19 ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ተጋላጭ ያደርጋል።
ውፍረትና ኮሮናቫይረስን ምን ያገናኛቸዋል?
ከፍተኛ ውፍረት አለ ማለት በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ የስብ ክምችት አለ ማለት ነው። ስብ ደግሞ ሰውነታችንን ልፍስፍስና ደካማ ያደርገዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሳምባችንም አቅሙ ይቀንሳል ማለት ነው።
ሳንባችን ደካማ ሲሆን ወደ ደችማን ውስጥና በአጠቃላይ ወደ ሰውነታችን ኦክስጂን ለማድረስ ይቸገራል። ይህ ሲሆን ደግሞ የደም ዝውውር ይታወካል፤ ልባችንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባል።
“ሰዎች ከመጠን በላይ ውፍረት ካላቸው ሰውነታቸው ከሌሎች በተለየ ከፍተኛ ኦክስጂን እፈልጋል። ስለዚህ ኦክስጂን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት መሀል ሰውነታቸው በእጅጉ ይጎዳል” ይላሉ በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ናቪድ ሳታር።

ልክ እንደ ኮሮናቫይረስ አይነት የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ ወረርሽኞች ሲከሰቱ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች በብዛት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች ናቸው።
“ነገሮች እየባሱ ሲሄዱ ሳንባቸው ለመላው ሰውነታቸው ኦክስጂን ማድረስ ይሳነዋል” ብለዋል ፕሮፌሰር ናቪድ።
ለዚህም ነው በከፍተኛ ክትትል ክፍል ውስጥ ሕክምና ከሚደረግላቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው የሚሆኑት ይላሉ ባለሙያዎቹ።
ሳይንቲስቶች አገኘነው ባሉት መረጃ መሰረት በስብ ውስጥ የሚገኝ ‘ኤሲኢ2’ የሚባል ኤንዛይም አለ። ይህ ኤንዛይም ቫይረሱ በቀላሉ ወደ ሰውነታችን እንዲገባ ያደርጋል።
ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው ሰዎች በቀላሉ በቫይረሱ የሚያዙትና ሕመሙን ከሚያጠናባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ሁሉ ተጋላጭነቶች በተጨማሪ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ በሽታን የሚዋጉ ሴሎች አቅም ከመጠን በላይ በወፈሩ ሰዎች ውስጥ ደካማ ነው።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሁሌም ቢሆን ይዞት የሚመጣው ተጨማሪ የጤና ጠንቅ አል። ከካንሰር እስከ የልብ በሽታ፣ ከኩላሊት መድከም እስከ ስኳር ድረስ በርካታ በሽታዎችን ያስከትላል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቀነስና ከመጀመሪያውም እንዳይከሰት ለማድረግ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ መመገብና ያልተቋረጠ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ወሳኝ ነው።