ከሲዳማ በኋላ የሚኖረው የደቡብ ክልል ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?
በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ክልልነት በይፋ ርክክብ በተደረገበት ወቅት

21 June 2020

ብሩክ አብዱ

የደቡብ ክልልን ሲያምሱ ከነበሩና የበርካታ አገራዊና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ትኩረት ሲስቡ ከነበሩ አንድ ደርዘን ያህል ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነው፣ የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት የተደረገውን ሕዝበ ውሳኔ ተከትሎ፣ ሲጠበቅ የነበረው ከነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጋር የሚደረገው የሥልጣን ርክክብ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡

ሕዝበ ውሳኔው ከመካሄዱ አስቀድሞ ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ሳያቀርብ በመቆየቱ ሲወቀስና ሲከሰስ የቆየው የደቡብ ክልል ምክር ቤት፣ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሥልጣን ርክክቡንም ለመፈጸም በወሰደው ጊዜ ምክንያት ጠንካራ ትችቶች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ በተለይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሔለን ደበበም ሆኑ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ መንግሥቱ ሻንካ፣ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ሒደቱን በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለማስረዳት ባለመፈለጋቸው የትችቶቹ መነሻ ሆነዋል፡፡

የሥልጣን ርክክቡ በመዘግየቱ ሳቢያም የ2013 ዓ.ም. የበጀት ድልድል ሲሠራ የሲዳማ ክልል የሥልጣን ርክክብ ባለመደረጉና በዚህም ሳቢያ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ለበጀት ድልድል የሚሆን ቀመር ማዘጋጀት ባለመቻሉ፣ የ2013 ዓ.ም. በጀት ለምክር ቤቱ ሲቀርብ፣ የሲዳማ የፓርላማ ተወካዮች የሕዝብን ድምፅ መናቅ ነው ሲሉ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡

ይሁንና ከ98 በመቶ በላይ የሆኑ የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ሲዳማ በክልልነት እንዲቋቋም በሕዝበ ውሳኔ ምርጫቸውን ካሳወቁ ከስድስት ወራት በኋላ፣ ምክር ቤቱ ሥልጣኑን አዲስ ለሚቋቋመው አሥረኛው ክልል አስተላልፏል፡፡ ምክር ቤቱ ለሥልጣን ርክክቡ ባዘጋጀው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት፣ ምርጫ ቦርድ ከ98 በመቶ በላይ ድምፅ ሰጪዎች ውሳኔውን እንደ ደገፉ በመግለጽ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሥልጣን ርክክብ መፈጸም እንደሚገባ በማተት፣ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጉባዔው የሥልጣን ርክክቡን እንደወሰነ አስታውሷል፡፡

የሲዳማ ብሔር አሥረኛው የኢትዮጵያ ክልል በመሆኑና የሥልጣን ርክክብ በመፈጸሙ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ላዳሞ፣ የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ፣ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ፣ እንዲሁም ሌሎች የክልሉና የዞኖች ባለሥልጣናትና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

የሲዳማና የደቡብ ክልል የሥልጣን ርክክብ መደረጉ ከሕዝበ ውሳኔው ቀጥሎ የሲዳማ ብሔር በክልልነት እንዲቋቋም የመጀመርያው ሒደት ቢሆንም፣ ካሁን በኋላ የሚጠበቁና መከናወን ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡ በሲዳማ ክልልና በነባሩ የደቡብ ክልል መካከል የሚኖሩ የንብረት ክፍፍልና በአዲሱ ክልል የሚኖሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች መብት ጉዳይ እንዴት እንደሚሆን በሕግ መደንገግ እንደሚኖርበት ካሁን ቀደም ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ይኼንን ለመግዛት የሚያግዙ የአናሳ ቁጥር ብሔሮች መብትና የንብረት ክፍፍልን የሚመለከት ሕግ ተዘጋጅቷል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ከተፈቱ በኋላ የሐዋሳ ከተማ ለሁለቱም ክልሎች መቀመጫ በመሆን፣ ለቀጣይ አሥር ዓመታት እንደሚያገለግል ከስምምነት የተደረሰበትና በጋራ የሚተዳደር ከተማ ቢሆንም፣ እንዴት በተግባር ሊውል እንደሚችልና የጎንዮሽ ግንኙነቶች እንዴት ሊመሠረቱ እንደሚገባ ግልጽ ስላልሆነ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሕገ መንግሥት ባለሙያውና በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ካሳሁን ይናገራሉ፡፡

‹‹ክልሉም ሆነ ልምምዱ በኢትዮጵያ አዲስ እንደ መሆኑ መጠን አዳዲስ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፣ ሐዋሳም መንታ አገልግሎት ስለሚሰጥ የዚህ አካል ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቀጣዩ አዲስ ክልላዊ መንግሥት እንዴት ሊመሠረት ይችላል የሚለው እንደሆነ የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ሕገ መንግሥት ማርቀቅና ማፅደቅ፣ እንዲሁም ሦስቱን የመንግሥት አካላት ማዋቀር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ የመንግሥት ሦስቱ አካላት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ለማቋቋም ደግሞ በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይኼንን ለማድረግ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ማድረግ ስለማይቻል አሁን የሽግግር መንግሥት ማቋቋም መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይኼ የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥት ለማፅደቅና መንግሥታዊ መዋቅር ለመሥራት አይችልም፤›› በማለት ያክላሉ፡፡

ነገር ግን ውክልናን በተመለከተ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ተወካዮች ተመራጭ በመሆናቸው፣ ከክልሉ ምክር ቤት እንደሚለቁና በፌዴራል ፓርላማ ደቡብን በመወከል የተመረጡ የሲዳማ ብሔር ተወካዮች ሲዳማን በመወከል መቀጠል እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ክልል ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ራሱን የቻለ ሥራ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፣ የጋራ ሥልጣንና ሀብት አሰባሰብና አጠቃቀምን በተመለከተም መሠራት አለበት ይላሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ የሲዳማ ክልል ከተቋቋመ በኋላ የሚቀረው የደቡብ ክልል እንዴት ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ በርካቶችን የሚነጋገሩበት ጉዳይ ሲሆን፣ በተለይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የተቀረውን የደቡብ ክልል አደረጃጀት በአጀንዳነት ቢይዝም ሰፊ ውይይት ያልተደረገበት ጉዳይ መሆኑ ጥያቄዎች እያስነሳ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በአጀንዳነት ቢይዘውም በፌዴራል መንግሥት ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ በመግለጽ፣ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት እንዳልተደረገበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በደቡብ ክልል 12 ዞኖች በምክር ቤቶቻቸው የየራሳቸውን ክልል ለመመሥረት በማፅደቅ ለክልል ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅላቸው ያሳወቁ ቢሆንም፣ እስካሁን ከሲዳማ በስተቀር ሕዝበ ውሳኔ የተደራጀለት ዞን የለም፡፡

የደቡብ ክልል ምክር ቤትም በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የትኛውንም ጥያቄ አጀንዳ አድርጎ አልተወያየበትም፡፡ ነገር ግን 20 የቀድሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) አባላትንና የዩኒቨርሲቱ መምህራንን ያቀፈ ቡድን ተቋቁሞ በክልሉ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችላል ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች አቅርቦ ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህን ምክረ ሐሳቦች በርካቶች ተቃውመው እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር፡፡ ስለዚህም ያነሳናቸው በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ተቀባይነት ስላላገኙ ምላሽ ይሰጠን በማለት፣ ጥያቄዎቹን ያነሱ ዞኖች ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሠልፎች አድርገዋል፡፡

ከክልሉ በተጨማሪም እነዚህን የክልልነት ጥያቄዎች ለመመለስ ያዳግተኛል ያለው የፌዴራል መንግሥትም የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ 80 አባላት ያሉትን የሰላም አምባሳደሮች ቡድን አዋቅሮ መፍትሔ ሲሻ ነበር፣ ምንም እንኳን ይኼም እዚህ ግባ የሚባል ፍሬ ባያፈራም፡፡

ከጥንስሱ በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ቡድን አባላት በሁሉም በደቡብ ክልል ባሉ ወረዳዎች ተዘዋውሮ ሕዝብን ለማወያየትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለካቢኔያቸው የመፍትሔ ሐሳብ ለመስጠት የታለመለት ቢሆንም፣ አባላቱ በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያ በሁሉም ወረዳዎች ተዟዙረው ውይይቶችን ማከናወን ሳይችሉ በመቅረታቸው፣ በዞን ደረጃ የተደረጉ ውይይቶች ላይ ተመርኩዘው ምክረ ሐሳቦችን አዘጋጅተዋል፡፡

እነዚህ ምክረ ሐሳቦች የሲዳማ ክልልን መውጣት ከግንዛቤ ሳይከቱ የደቡብ ክልልን በአራት የሚከፍሉ ናቸው፡፡ ደቡብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ኦሞቲክና የሲዳማ ክላስተር በሚል ይከፋፍላሉ፡፡ ነገር ግን የሲዳማ ብሔር ተወካዮች በቡድኑ ያልተካተቱ ሲሆን፣ አልተወከልንም በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ በጎፋ ዞን ውስጥ ያለ የቁጫ ብሔረሰብ ዓይነት ጥያቄዎች ተነስተው ያልተስተናገዱበትም መድረክ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ80ዎቹ አባላት መረጃ ለመሰብሰብ የተሰማሩ ግለሰቦች በአንዳንድ ዞኖች አትገቡም ተብለው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስተመጨረሻም የቀረበው ምክረ ሐሳብ የሕዝብን ጥያቄና ሐሳብ ያላካተተና ወካይነት የሌለው፣ እንዲሁም በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተንተራሰ ምደባ መደረጉን በመቃወም የወላይታ ተወካዮች ቡድኑን ለቅቀው ወጥተዋል፡፡

በስብሰባው ተሳትፎ ያደረጉት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ከበደ ከስብሰባው የወላይታ ተወካዮች የወጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ‹‹አንዱ ትልቁ የተሠራው ስህተት ቃለ ጉባዔውን ያፀደቁት በ80ዎቹ የሰላም መልዕክተኞች ስላልሆነ፣ የቀረቡት ምክረ ሐሳቦች የተንተራሱበት ቃለ ጉባዔ በእውነታ ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ስለዚህም የወላይታ ተወካዮች ይስተካከል ዘንድ በሕዝብ ውክልና ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲከናወን፣ እንዲሁም እንደ ወላይታ ያሉ ብሔሮች ለብቻቸው ክልል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ሳለ ከሌሎች ጋር አብረው በክላስተር ለመዋቀር ፍላጎት እንዳሳዩ ተደርጎ መቅረቡ ልክ አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር አቶ አሸናፊ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለዚህ ትልቁ ችግር አስተባባሪዎቹ ገለልተኛ አለመሆናቸው ነው፤›› ሲሉ ትችት የሚሰነዝሩት አቶ አሸናፊ፣ ‹‹አዝማሚያቸውም አስቀድሞ በደኢሕዴን የተጠናውን ጥናት የተቀበሉ ነው የሚመስለው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የሕገ መንግሥት ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን በበኩላቸው እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ከሕገ መንግሥቱ አንፃር መታየት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ በአንቀጽ 47 መሠረት ለብቻቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በጥምረት ክልል የመመሥረት መብት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች ስለሆነ በዚህ ሒደት የፌዴራል መንግሥት የሚኖረው ሚና በሕገ መንግሥቱ አልተገለጸም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

በመልክዓ መምድራዊ አቀማመጥ በደቡብ ያሉ ብሔሮች ክልሎችን ለማዋቀር የሚቻል ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን ያስከትላል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይኼ በበኩሉ የብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚሸረሽር ስለሚሆን ችግር ሊያስከትል ይችላል ይላሉ፡፡

‹‹ይኼ የሚደረገው በብሔር ብሔረሰቦቹ ተነሳሽነት ከሆነ ችግር የለውም፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፣ ‹‹ውሳኔ መስጠት የሚችለው ደግሞ ሕዝቡ ነው፡፡ ይኼ የሚወሰነው ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች መፍትሔዎችን አነሳስቶ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ነገር ግን የመጨረሻው ውሳኔ የብሔሩ ስለሆነ በፈለገበት መንገድ ሊወስን ይችላል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም ‹‹መንግሥት የአማካሪነት ሚና ነው ሊኖረው ነው የሚገባው፡፡ አለበለዚያ ከላይ የሚጫን ከሆነ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው የሚሆነው፤›› ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

ከክልል መመሥረት ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥት የሚኖረው ሚና መብቶቹን ማክበር፣ ማስተባበርና አስፈላጊ ጉዳዮችን ማሟላት ብቻ እንደሆኑ የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፣ መንግሥት ብሔሮች እኔ ለብቻዬ ነው ክልል መመሥረት የምፈልገው ካሉ ያንን መቃረን አይችልም ይላሉ፡፡

ይሁንና በክላስተር ክልል ለማቋቋም የሚፈልጉ ብሔሮች ቢኖሩም፣ የክልልነት መቀመጫን በተመለከተ እየተነሱ ያሉ ክርክሮች ካሁኑ መሰማት ጀምረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም የደቡብ ምዕራብ ክልል በሚለው ሥር እንዲካተቱ በምክረ ሐሳብ የተቀመጡት ዳውሮ፣ ኮንታ፣ ሸካ፣ ካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች ሲሆኑ፣ የክልል መቀመጫን በተመለከተ ክርክሮች እየቀረቡ ነው፡፡ በተለይም በካፋ ዞን ዋና ከተማ ቦንጋና በቤንች ሸካ ዞን ዋና ከተማ ሚዛን አማን ከተማ በማኅበራዊ ወትዋቾች መካከል የሚታዩ ክርክሮች ማሳያ ናቸው፡፡

ነገር ግን ዞኖች በጥምረት ክልል ለመመሥረት ከተስማሙ የሚነሱ የማዕከልነት ጥያቄዎች ሊመለሱባቸው የሚችሉበት መንገድ እንዳለም ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ይገልጻሉ፡፡ አንደኛው መንገድ እንደ ደቡብ አፍሪካ የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈጻሚና የሕግ ተርጓሚ የመንግሥት አካላትን በተለያዩ ከተሞች ማድረግ ነው፡፡ ‹‹ከወጪ አንፃር እንዲህ ያለው መፍትሔ ከባድ ቢመስልም፣ የተለያዩ ቡድኖችን ፍላጎቶች ሚዛናዊ በመሆነ መንገድ ለማስተናገድ ያስችላል፤›› ይላሉ፡፡

ሌላው አማራጭ ተንቀሳቃሽ (Rotating) ዋና ከተሞች እንዲኖሩ ማድረግ ሲሆን፣ ለአሥርና ለአሥራ አምስት ዓመታት አንድ ከተማን የክልል አድርጎ ቆይቶ ወደ ሌላ እያዛወሩ ማስማማት ነው፡፡ ይኼኛው ግን የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መገንባት ስለሚፈልግ ወጪው ከፍተኛ ይሆናል ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከላትን በመለየት ማዋቀር እንደሚቻልም በአማራጭነት ያስረዳሉ፡፡

አሁን የደቡብ ክልል ቅርፅ ምን እንደሚሆን በግልጽ መተንበይ ባይቻልም ቅሉ፣ የክልልነት ጥያቄ እያቀረቡ ካሉ ዞኖች መካከል ገሚሱ ለብቻችን ክልል እንመሥርት የሚሉ ሲሆኑ፣ የተቀሩት ከአጎራባቾቻቸው ጋር በጥምረት ክልል ለመመሥረት የወሰኑ ናቸው፡፡