
የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላት
24 June 2020
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኞ ሰኔ 15 ቀን ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለው ሴክሬታሪያት እንዲቋቋም መወሰኑን ባወጣው ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አስታወቀ፡፡ የዞኑ መስተዳድር ለወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሒደቱን በበላይነት እንዲመራ መወሰኑን ገልጿል።
የወላይታ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ፣ ጥያቄው የቀረበለት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው የወላይታ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ቢደነግግም፣ የክልሉ ምክር ቤት የወላይታን ክልል የመመሥረት ጥያቄን አጀንዳ አድርጎ ላለማቅረብ በማሰብ መደበኛ ስብሰባዎችን በተደጋጋሚ ሆን ብሎ እየዘለለ መቆየቱን ምክር ቤቱ አስታውሷል፡፡
ይህንን ኢፍትሐዊ አሠራር መነሻ በማድረግ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን፣ በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ በዋናነት የዞኑ መስተዳድር የሕዝቡን ክልል የመመሥረት ጥያቄን የመራበት ሒደት በጥልቀት የተመለከተ መሆኑንና እስካሁን ያለው ሒደት አመርቂ መሆኑን መገምገሙን በመግለጫው አስረድቷል፡፡
በዚህም መሠረት የወላይታ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 (3) መሠረት የጠየቀው የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን፣ የሚመሠረተው ክልል ስያሜ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የሥራ ቋንቋ ወላይትኛ (Wolaittatto Doona)፣ የክልሉ ርዕሰ ከተማ ወላይታ ሶዶ እንደሚሆን፣ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ለሆነ የሕዝብ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን በተከተለ መንገድ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የወላይታ ብሔር ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ይህ ጥያቄ በጊዜው ባለመመለሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰና የዞኑ መንግሥትም ሙሉ ጊዜውን በልማት ሥራ እንዳያውል እንቅፋት መሆኑን፣ ሒደቱም ወደ ፀጥታ ችግር ሳይሸጋገር የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ እንዲሰጥ ምክር ቤቱ መጠየቁን ገልጿል።
የወላይታ ብሔርን ወክለው በክልል ምክር ቤት ሲሳተፉ የነበሩ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላለመሳተፍ ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸው ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው ያለው ምክር ቤቱ፣ አባላቱ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት ለወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ነው በማለት አስታውሷል፡፡ ይህ የወላይታ ብሔር ተወካዮች ውሳኔ ለወላይታ ብሔር ያላቸውን ክብር የሚያሳይ ስለሆነ ምክር ቤቱ በአድናቆት ማየቱን፣ ነገር ግን እነዚህን ተወካዮች የክልሉ አስተዳደርና የክልሉ ምክር ቤት ጠርተው ማወያየት ሲገባቸው እስካሁን ድረስ ዝም ማለታቸው መላውን የወላይታ ሕዝብ አለማክበራቸውን ያሳያል ብሏል፡፡
‹‹የሕዝብ ውክልና የያዘ አካል ለክልሉ ምክር ቤት ያለውን ቅሬታ ለማሳየት መልቀቂያ ቢያስገባ፣ የሕዝቡ ተወካዮች ጠርቶ አለማወያየትና ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የወላይታ ሕዝብ በአገሪቱ ለመጣው ለውጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህም የፌዴራል መንግሥት እነዚህን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮችን ጠርቶ እንዲያነጋግር የዞኑ ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚወስናቸው ወላይታን የሚመለከቱ ማናቸውም ውሳኔዎች ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በወላይታ ዞን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት እንዳለባቸውና በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚወሰኑ የወላይታን ሕዝብ ጥቅም የሚጎዱ ማናቸውም ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ምክር ቤቱ መወሰኑን፣ የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅርን በሚመሩ አካላት ላይ የዞኑ ምክር ቤት እምነት ስለሌለውና ገለልተኛ ባለመሆናቸው፣ እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፖስት የሚመራ በመሆኑ የወላይታ ዞን የፀጥታ ሥራ በሕዝቡና በዞኑ የፀጥታ መዋቅር በትብብር መከናወን እንዳለበት፣ ድጋፍ በሚያስፈልግበትም ጊዜ ከፈዴራል የፀጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መሠራት እንዳለበት መወሰኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ወደፊት የሚመሠረተው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አዋጆችንና መመርያዎችን እንዲያዘጋጅ ሴክራቴሪያት እንዲቋቋም እንደተወሰነ፣ በተጨማሪም የዞኑ መስተዳድር እንዳስፈላጊነቱ ለወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሒደቱን በበላይነት እንዲመራ መወሰኑ በመግለጫው ተመልክቷል።
‹‹ቀጣዩ ሕዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ መወሰኑን፣ የወላይታና አጎራባች ሕዝቦች ትስስር ለዘመናት የቆየና በቀጣይ አብሮ የሚኖርና የሕዝቦች ትስስር ከመዋቅር በላይ በመሆኑ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ምክር ቤት ወስኗል።
‹‹ለመላው የወላይታ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ መብት በሚመለከተው የፌዴራል መንግሥት አካል ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ፣ እንደተለመደው ሁሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፤›› ሲል ምክር ቤቱ መግለጫውን ድምድሟል፡፡