Source: http://www.goolgule.com/bring-ethno-fascists-to-justice/
July 3, 2020 09:12 am by Editor

የፋሽስታዊው አመለካከት ያላቸው (ethno-fascists) የጸጋዬ አራርሳ፣ የህዝቄል ገቢሳ፣ መሰሎቻቸው፣ እንዲሁም የትግራይ ሚዲያ ሀውስ መርዘኛ፡ ሃሰተኛ ቅስቀሳዎችና ትርክቶች የብሄር ለብሄር፣ የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ከማድረሳቸው በፊት በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነው የተደራጀ፣ የተቀናጀ፣ የተናበበ ስራ መስራት ይገባል። ባልተናበበና በተበታተነ ሁኔታና እንቅስቃሴ ውጤት ለማምጣት እጅግ አዳጋች ይሆናል፣ ሁሉም ባለው መሰለፍ ይገባል፣ የመጣውን ኣደጋ ለመከላከል እንደ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በጋራ መቆም የግድ ነው። የፖለቲካ አመለካከት ወደ ጎን አድርጎ በአንድ ላይ፣ በጋራ መቆም ወሳኝ ይመስለኛል።
የሁላችንም ሀገር የሆነችው ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ አዝማዶች፣ ወገኖችና፣ ባጠቃላይም ህዝባችን የሚኖርባት ሀገረ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ሁኔታ ፍጹም ወደ አለተጠበቀ እጅግ አውዳሚ ሂደት ሊሸጋገር ይችላል። ለዚህ አደገኛ ሂደት ደግሞ በደምብ በተጠና፣ በተቀናጀ መልክ ቤንዚን የሚያርከፈክፉትን እነዚህ ፋሽስታዊ የኦሮሞ ጽንፈኞች፣ እንዲሁም ያጣውን ስልጣን ዳግም ለመፈናጠጥ ካልቻለ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሙሉ አቅሙ 24 ሰአት አየሰራ የሚገኘው የአሸባሪው የህወሃት ልሳን የሆነው የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ናቸው።



በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎችም ይህን እጅግ አደገኛ ሂደት በህግ እንዲታይና የህግ መሣሪያዎችን (Legal instruments) መፈተሽና መጠቀም ይገባቸዋል። የተቀነባበረ፣ የተደራጀ ስራ መስራት፣ በኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲሁም በመላው ህዝባችን ላይ የተጋረጠውን ከባድ ሰላም አደፍራሽ፣ ህዝብ ለህዝብ አጫራሽ፣ ሀገርንም ሊበትን የሚችል አደጋ ለመከላከል በጋራ መንቀሳቀስ፣ መናበብና፣ ተጽእኖ በሚፈጥር ሁኔታ መመከት፣ ማጋለጥ፣ በህግም እንዲጠየቁ ለማድረግ መንቀሳቀስ የሚገባው ጊዜው አሁን ነው።
ነአምን ዘለቀ