13 ሀምሌ 2020, 09:05 EAT

ከ30 ዓመታት በላይ በእስልምና መርሆች ስትተዳደር የነበረችው ሱዳን፤ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ ከመፍቀዷ በተጨማሪ ሐይማኖት የመቀየር መብትን ጨምሮ በርካታ ለውጦችን ይፋ አደረገች።
የሱዳን ፍትህ ሚንስቴር ሰዎች ለፈጸሙት ‘ኢ-ሞራላዊ ተግባር’ በአደባባይ እንዲገረፉ የሚያዘው ትዕዛዝ እንዲቆም መታወጁንም አስታውዋል።
የፍትህ ሚንስትሩ ነስረዲን አብዱለባሪ “የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ሕጎችን በሙሉ እናስወግዳለን” ብለዋል።
ቀደም ሲል ሱዳን የሴት ልጅ ግርዛትን ሕገ ወጥ ድርጊት በማለት ከልክላለች።
በአዲሱ ሕግ መሠረት ሴቶች ጉዞ ለማድረግ ከወንድ የቤተሰብ አባል ፍቃድ ማግኘት አይጠበቅባቸውም።
አዲሶቹ ሕጎች የትኞቹ ናቸው?
ከዚህ ቀደም በሱዳን የአልኮል መጠጥ መጠጣት አይፈቀድም ነበር። አሁን ግን ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አልኮል በቤታቸው መጠቀም ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ሙስሊሞች ባሉበት ቦታ አልኮል ሲጠጡ ቢገኙ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተነግሯል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ግን አሁንም ቢሆን አልኮል መጠጣት አይፈቀድላቸውም ሲሉ የፍትህ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
ሙስሊም ያለሆኑ ግሰቦች አልኮል ከመጠቀም ባሻገር፤ መሽጥ እና ከውጪ ማስገባት ይችላሉ ተብሏል። የሱዳን መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰኩት 3 በመቶ የሚሆኑ ሙስሊም ያልሆኑ ሱዳናውያንን መብትን ለመጠበቅ ነው ብሏል።
በሱዳን እስከ ዛሬ ድረስ የእስልምን ሐይማኖትን የሚቀይሩ ሰዎች የሞት ቅጣትን ጨምሮ ከባድ ቅጣት ይጣልባቸው ነበር።
እንደማሳያ እአአ 2014 ሜሪያም ይህያ ኢብራሂም የተባለችው ሴት ክርስቲያን ወንድ ካገባች በኋላ በስቅላት እንድትቀጣ ተፍርዶባት ነበር።
በወቅቱ ነብሰ ጡር የነበረችው ሜሪያም ምንም እንኳ የፍርድ ውሳኔው ሳይፈጸምባት ከሱዳን መውጣት ብትችልም በርካቶች መሰል ሕጎች ተፈጻሚነታቸው እንዲቆም ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች የማኅበረሰቡን ሞራል የሚጥስ ተግባር ፈጽመዋል ተብለው በአደባባይ እንዲገረፉ የሚያዘው ሕግ እንዲቀር ተወስኗል።
እአአ 1980ዎች የተጣለው ጥብቅ የእስልምና ሕጎች በሱዳን ለረዥም ጊዜ ለቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት ከዚያም ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን እንድታገኝ ምክንያት ነበር።
አብዛኛው ደቡብ ሱዳናውያን የክርስትን ወይም ሌሎች ባህላዊ እምነቶች ተከታይ ናቸው።