
በትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን አባላት ለመምረጥ የሕዝብ ጥቆማ ከቅዳሜ ጀምሮ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ገብረሥላሴ ለቢቢሲ ገለጹ።
በትግራይ ክልል ስድስተኛ ዙር ክልላዊና አካባቢዊ ምርጫ ለማካሄድ አስፈፀሚ ኮሚሽን ለማቋቋም የክልሉ ምክር ቤት በወሰነው መሰረት ሕዝቡ የኮሚሽኑ አባላትን እንዲጠቁም ጥሪ ቀርቧል።
ከሕዝቡ ጥቆማ መሰብሰብ የተጀመረው ቅዳሜ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ ማክሰኞ ሐምሌ 7 2012 ዓ.ም መሆኑ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አገራዊ ምርጫ ከተራዘመ ወዲህ የትግራይ ክልል ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከክልሉ ጥያቄ ቢቀርብለትም በወቅቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንደማይችል ገልጾ ነበር።
ከዚህ በኋላ ክልሉ የራሱን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችለውን የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግ እንዲሁም የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጆች አጽድቋል።
- በቡራዩ በጎርፍ አደጋ 9 ሰዎች ሲሞቱ የደረሱበት ያልታወቁ እየተፈለጉ ነው
- ከሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ ዐቃቤ ሕግ እስካሁን ምን አለ?
- ትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም ምክክር እንደሚደረግ ተገለጸ
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ገብረሥላሴ ለቢቢሲ እንዳሉት እስካሁን ድረስ ከአገር ውጪና ውስጥ ከ300 በላይ ሰዎች ተጠቁመዋል።
የኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አሰፋ አክለውም ጥቆማ መስጠቱ እንደተጠናቀቀ በነጋታው ረቡዕ የተጠቆሙ ሰዎች ለክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ስማቸው ቀርቦ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውይይት ይደረግበታል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ አስር ሰዎች ተመርጠው ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ የኮሚሽኑ ኮሚሽነርና ምክትልን ጨምሮ አምስት አባላት እንዲፀድቁ ይደረጋል ብለዋል።
ህወሓት ከዚህ በፊት ከተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና፣ እንዲሁም የትግራይ ነጻነት ጋር በምርጫ ህጉ ላይ ተወያይተው ነበር።
እስካሁን ድረስ በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አረና ትግራይና፣ የትግራይ ዲሚክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅቶች በውይይቱ ላይ አልተሳተፉም።
ለትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን አባልነት ለመመረጥ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣ የክልሉ ቋንቋ የሚችል፣ የየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ፣ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ ሕገ መንግሥት ተገዥ የሆነ፣ ሥነምግባር ያለው፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ትምህርት፣ ልምድና አቅም ያለው ግለሰብ መሆን እንዳለበት ተዘርዝሯል።