July 13, 2020

Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/107869

አጋርፋ፡- ሰኔ 23 በተፈጠረው ሁከት በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ የሚገኙ 38 የመንግሥት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን የባሌ ዞን ፖሊስ ምርመራ ዲቪዚዎን ሃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ከበደ አስታወቁ፡፡ በሁከቱ የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ኮማንደር ተስፋዬ በስፍራው ለሚገኝ የጋዜጠኞች ቡድን እንዳስታወቁት፣ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ

ሞት ምክንያት የድጋፍ ሰልፍ እንወጣለን በሚል ሰኔ 23 በተፈፀመ የሁከት ተግባር በባሌ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በሁከት ፈጣሪዎች የሰባት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ጠቁመው፣ ሰላሳ ስምንት የመንግሥት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አመልክተዋል። በንብረት ላይ የደረሰው ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እንደሆነም አስታውቀዋል። በአጋርፋ ወረዳ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አስታውቀው፣ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ሥራ የሚከናወነው በትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል። ከሁከቱ ጋር በተያያዘ በተከሰተው ዝርፊያና ቃጠሎ ምክንያት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክተዋል። የአርሶ አደሩ ንብረት የሆኑ ከብቶችና ሌሎች ንብረቶች ሳይቀር የተዘረፉና የወደሙ መሆናቸውን አመልክተው፣ የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል። አንድ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በወቅቱም በርካታ ቁሳቁሶች መያዛቸውን ጠቁመው ዘጠኝ ሽጉጥ፣ አራት ክላሽንኮቭ እንዲሁም ቤቶችንና ድልድዮችን ለማፍረስ የሚውሉ አራት መቶ ሰላሳ አራት ተቀጣጣይ ፈንጅ ግማሽ አካል መገኘቱንም አመልክተዋል። ይህ ተቀጣጣይ ፈንጅ አንዱ በፖሊስ ጣቢያ አንዱ በድልድይ ላይ ተጠምዶ የተገኘ ሲሆን ከአጠማመድ ችግር የተነሳ የታለመለትን አላማ ሳያሳካ መቅረቱን አመልክተው፣ በተደረገው ክትትልም የተቀጣጣይ ፈንጅ ግማሽ አካሎቹ በአንድ ግለሰብ ቤት መገኘታቸውን፤ ግለሰቡም ተይዞ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል። የወንጀሉ ሂደት ከባድና ውስብስብ እንዲሁም ወንጀሉ የተፈጠረባቸው ቦታዎች የተራራቁ መሆናቸውን ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በተቀናጀና በጥሩ ሁኔታ የማረጋጋት ሥራዎች እየተሠራ ነው። በዚህም የወንጀል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከማዋል ባለፈ የተዘረፉ የመንግሥት ተቋማትም ሆነ የግለሰብ ንብረቶች እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ከመንግሥት መሥሪያ ቤት የተዘረፉ አንድ መቶ አስር የጦር መሣሪያዎች መመለሳቸውን አመልክተው፤ ድርጊቱ የተፈፀመው በተወሰኑ የተደራጁ ቡድኖች ነው። የኦነግ ሸኔ አባላትም በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል። ከሁከቱ በኋላ የወረዳው አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ አብዱቃድር ኡስማን በበኩላቸው፤ የተፈጠረው ድርጊት በተደራጀ የጠላት ሴራ መሆኑን አስታውቀው፣ አለማውም ብሔር ብሔረሰቦችን አጣልቶ አገር ማፍረስና በአቋራጭ ወደ ሥልጣን የመምጣት ህልማቸውን እውን ማድረግ ነው ብለዋል። በዚህ ድርጊትም ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ሲቀሩ የወረዳው የመንግሥት መሥሪያ ቤት መውደማቸውን ጠቁመው፣ ከጉዳቱ ጋር በተያያዘም የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ ሦስት የወረዳው የካቢኔ አባላት እንዲሁም ዘጠኝ የፖሊስ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል። አሁን ያለው አመራርም የጠፋውን ንብረት እንደገና እንዲመለስ ለማድረግና የተጎዱትንም ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡም በራሱ ተነሳሽነት ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኙ አመልክተዋል። በወንድወሰን ሽመልስ